Monday, 12 October 2020 08:44

ቤተ ክርስቲያኒቱ ለጃንሜዳና መስቀል አደባባይ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጣት ጠይቃለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

ቤተ ክርስቲያኒቱ በዩኔስኮ የተመዘገቡት የጥምቀትና የመስቀል ደመራ በዓላት ማክበሪያ ለሆኑት ጃንሜዳና መስቀል አደባባይ የባለቤትነት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጣት ጥያቄ አቅርባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ምላሽ እየተጠባበቀች መሆኑ የታወቀ ሲሆን፤ ጃንሜዳ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ተፀድቶ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተመላሽ ይደረጋል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የበዓላት ማክበሪያና አብያተ ክርስቲያናት ይዞታዎችን የሚከታተል ኮሚቴ አቋቁማ ሠፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኗን ለአዲስ አድማስ ያስረዱት የኮሚቴው አባል አቶ ግርማ ተክሉ፤ በተለይ  በአላት በስፋት የሚከበርባቸው ጃንሜዳና መስቀል አደባባይ ታሪካዊ ይዞታቸውን እንደጠበቁ ለማቆየትና የቤተ ክርስቲያኒቱን የባለቤትነት መብት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ሲከናወን አስቀድሞ የከተማ አስተዳደሩ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር ተመካክሮ ፕሮጀክቱን መጀመሩንና የአደባባዩን ይዞታና የመስቀል ደመራ አከባበርን በማያውክ ደረጃ እየተከናወነ መሆኑን የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሙያዎች ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፤ መ/ር ግርማ፡፡ ጃንሜዳን በተመለከተም በጊዜያዊነት ለአትክልት ተራነት የመዋሉ ጉዳይ እንዲያበቃና ለቀጣይ የጥምቀት በዓል አከባበር ከወዲሁ ዝግጁ እንዲደረግ ኮሚቴው ባቀረበው ጥያቄ መሰረት፣ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ተፀድቶ ተመላሽ እንደሚደረግ ታውቋል።
በመስቀል አደባባይ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በአልም ሆነ በጃንሜዳ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በዩኒስኮ የተመዘገቡ አለማቀፍ ቅርሶች እንደመሆናቸው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለቱም የበዓላቱ ማክበሪያ ስፍራዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጣት መጠየቋንም መምህር ግርማ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
“ሁለቱ ብሔራዊ በዓላት የቤተክርስቲያኒቱ ብቻ አይደሉም፤ የሁሉም ሆነዋል” ያሉት መ/ር ግርማ፤ የከተማ አስተዳደሩ ለእነዚህ በአላት ማክበሪያ ቦታዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በንጽህና መጠበቅ ይገባዋል ብለዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ የባለቤትነት መብት የምትጠይቀው ;ቦታዎቹ የኔ ናቸው፤ ሌሎች መጠቀም የለባቸውም; ከሚል እሳቤ ሳይሆን ባለቤትነቷን ብቻ ለማረጋገጥ ነው፤ ቦታዎቹ አሁን እየሰጡ ያለውን ሌሎች አገልግሎቶች ትቃወማለች ማለት አይደለም ብለዋል - መ/ር ግርማ፡፡
ጃንሜዳ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያኑቱ ባልተረዳችው መንገድ ለኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሰጠቱንና ይህ ተገቢ ባለመሆኑ የቦታው ባለቤትነት ለቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲመለስ ጥያቄ መቅረቡንም ነው መ/ር ግርማ ያስረዱት፡፡
የቦታውን ባለቤትነት ለቤተ ክርስቲያኒቱ በመመለስ ስፖርት ኮሚሽን ግን ቦታውን እንዲጠቀምበት ማድረግ ይገባል ያሉት የኮሚቴው አባል፤ ለከተማ አስተዳደሩም በዚህ አግባብ ጥያቄው መቅረቡን አስታውቀዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ የተቋቋመው የይዞታ ጉዳይን የሚከታተለው ኮሚቴ፤ ከጀንሜዳና ከመስቀል አደባባይ በተጨማሪ በአዲስ አበባና አጐራባች የኦሮሚያ ዞን የሚገኙ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች ይዞታን እንዲረጋገጥ ጥያቄ እያቀረበ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአዲስ አበባ አጐራባች በሆኑ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ 6 የክብረ በዓላት ቦታዎችን ጨምሮ 78 ቦታዎች ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ ጥያቄ ማቅረቧን መ/ር ግርማ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ ባለቤትነቷ እንዲረጋገጥላት ጥያቄ ካቀረበችባቸው 78 የአዲስ አበባ ቦታዎች መካከል ለ38 ምላሽ መሰጠቱንና ቀሪዎቹ 40 ያህል ቦታዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥባቸው ግፊት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፤የኮሚቴው አባል፡፡
ኮሚቴው በሀገር አቀፍ ደረጃም የሚንቀሳቀስ ሲሆን በደቡብ ክልል ከ3 መቶ በላይ ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ማስገኘቱን፣ በድሬደዋና በሀረርም አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበዓላት ማክበሪያ ቦታዎች የይዞታ ይከበር ጥያቄ መመለሱን መ/ር ግርማ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡

Read 8565 times