Monday, 12 October 2020 09:12

ኢዜማ በመሬት ወረራና የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላ ጉዳይ ውይይት እንዳላዘጋጅ ተከልክያለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

የፍትሐ ብሔር ክስ በከተማ አስተዳደሩ ላይ አቅርቧል

          ኢዜማ በቅርቡ ምርመራ አድርጐ ሪፖርት ባቀረበበት ከአዲስ አበባ የመሬት ወረራና ህገወጥ የኮንዶሚኒየም እደላ ጋር በተያያዘ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለማካሄድ ያቀበደውን ውይይት በከተማ አስተዳደሩ እንደተከለከለ የገለፀ ሲሆን ይሄን ተከትሎም በከተማ አስተዳደሩ ላይ የፍትሐ ብሔር ክስ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡
“ለሀገር ሠላምና ለህዝብ ደህንነት መከበር መቆማችንን የምንናገረውንም ሆነ የምንሠራውን ሌሎች እንዲወስኑልን ከመፍቀድና ህገመንግስታዊ መብታችንን አሳልፎ ከመስጠት ጋር በፍፁም ሊምታታ አይገባውም” በሚል ርዕስ ትናንት በጽ/ቤቱ መግለጫ የሰጠው ኢዜማ፤ በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ የፖለቲካና ማህበራዊ ችግሮችን ፓርቲው በውይይት ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት በመንግስት አካላት እንቅፋት እየገጠመው መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
ፓርቲው ከአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ወረራና ኢ-ፍትሐዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላ ጋር በተያያዘ ም/ከንቲባዋ ጋር አንድ ጊዜ ተወያይቶ በድጋሚ ለመወያየት ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ የከተማ አስተዳደሩ ለውይይቱ ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን አስታውቋል፡፡
ይሄም ሳያንስ ኢዜማ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ውይይት እንዳያዘጋጅ የከተማ አስተዳደሩ ማስጠንቀቁን አመልክቷል፡፡
ኢዜማ ለመስከረም 15 ቀን 2013 ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ ይዞት የነበረው እቅድ የከተማ አስተዳደሩ የበዓላት ተደራራቢ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ ቀጠሮ እንዲዝሪምለት ጠይቆ፤ ፓርቲውም ጥያቄውን ተቀብሎ ለመስከረም 28 ማራዘሙን፤ ነገር ግን በቀጠሮው ቀን ውይይቱ ይደረጋል ተብሎ ሲጠበቅ የከተማ አስተዳደሩ ምንም አይነት ውይይት ማካሄድ እንደማይቻል ማሳወቁን  አመልክቷል - ፓርቲው በግለጫው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ መስከረም 27 ከቀኑ 8፡30 ላይ ለኢዜማ ባደረሰው የስብሰባ ክልከላ ማሳወቂያ ደብዳቤው፤ “የማጥራት ስራውን አስተዳደሩ ባላጠናቀቀበት ወቅት ውይይት መጥሪት ሌላ አተካራ የሚፈጥርና ምናልባትም ወደ ግጭት የሚወስድ በመሆኑ የጠራችሁት ውይይት እንዲሠረዝ እንድታደርጉ እናሳስባለን” የሚል መሆኑም ጠቁሟል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ድርጊት የፓርቲውን ህገ መንግስታዊ መብት የተጋፋና ሀገሪቱ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር የምታደርገውን ሂደት በእጅጉ የሚጐዳ መሆኑን የገለፀው ኢዜማ፤ ነገሩን በሰከነ መልኩ ለማየትና ውዝግብ ላለመፍጠር ሲል ውይይቱን ማቋረጡን አስታውቋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የውይይት ክልከላውን ትዕዛዝ የከተማ አስተዳደሩ እንዲያነሳና ከዚህ በኋላም እንዲህ ያለ ድርጊት እንዳይፈፀም ኢዜማ ለፍ/ቤት የፍትሃብሔር ክስ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ውይይት እንዳይደረግ ያስተላለፈው ትዕዛዝ ህገወጥና የፓርቲውን መብት የተጋፋ መሆኑን አውቆ ይቅርታ እስካልጠየቀ ድረስም ኢዜማ ከከንቲባ ጽ/ቤቱ ጋር የጀመረውን ውይይት እንደሚያቋርጥ አስታውቋል፡፡
ኢዜማ በህገወጥ የመሬት ወረራና በጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላ ዙሪያ ውይይት ለማድረግ አቅዶ የነበረው በመሬት ወረራው ተጐጂ ከሆኑ አካላት፣ ከከተማው ፖሊስና የደህንነት አካላት፣ እንዲሁም “ከአዲስ አበባ ዙሪያ ያለ በቂ ካሣ ተነስተን በስማችን ለሌሎች አካላት ቤቶች ተሰጥቷል ከሚሉ አርሶአደሮች ጋር እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል፡፡


Read 9816 times