Print this page
Friday, 16 October 2020 19:54

በበረሃ አንበጣ ሰብላቸው የወደመባቸው አርሶ አደሮች ምን ይላሉ ?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 

በበረሃአንበጣሰብላቸውየወደመባቸው

 አርሶአደሮችምንይላሉ ?

#በዚህ ዓመት የምናገኘው ምርት ለሶስት ዓመት ይበቃናል እያልን በጉጉት ስንጠብቅ ነው የቆየነው፡፡ ያላሰብነው ጠላት መጥቶ ባዶ አስቀረን እንጂ; ይላሉ በድንገተኛ የአንበጣ መንጋ ሰብላቸው የወደመባቸው  አርሶ አደሮች፡፡ የአንበጣ መንጋው በሰብላቸው ላይ ባደረሰው መጠነ ሰፊ ጉዳት ክፉኛ ቢያዝኑም፤ ከእነአካቴው ተስፋ ግን አልቆረጡም፡፡ “ፈጣሪ ያመጣው ችግር ነው፤ መንግስት ከጐናችን ከቆመ የችግር መውጫ መላ አይጠፋም” ባይ ናቸው፤ የጉዳት ሰለባ የሆኑት አርሶ አደሮች፡፡

አርብቶ አደሮችም የእንስሳት መኖ ወድሞባቸው ተክዘዋል፡፡ ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮችም ውሏቸውን በአንበጣ መንጋ ከተጐዱ አርሶ አደሮች ጋር ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ችግሩ በተከሰቱባቸው ሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎ ወረባዶ ወረዳና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ባቲ ወረዳ ከሰሞኑ ተገኝታ የደረሰውን ጉዳት የተመለከተችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ አርሶ አደሮችን አነጋግራ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች፡፡

አይናችንእያየአጨብጭበንባዷችንንቀርተናል

ጌታነህ ውዱ እባላለሁ፡፡ አሁን ያገኛችሁን ሸዋ ሮቢት ዙሪያ ነው፡፡ አንበጣው ከታች ከአፋር በኩል ነው የመጣብን፡፡ ወደዛ ራቅ ብሎ ባለው አካባቢ ከ8 ቀን በላይ ሆኖታል፡፡ ጠቅላላ አውድሞ ሲያበቃ ወደኛ ተዛመተ፡፡ ለመከላከል በርካታ ነገሮችን ብናደርግም አቃተን፡፡ አንበጣው በጣም ብዛት አለው፡፡ እስኪ በፈጠረሽ እይው… በላያችን ላይ ሲሄድ ደመና ይሰራል እኮ! አሁን ዛሬ ጠዋት 3፡00 ላይ ተነሳ፣ ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ህዝቡ እንደምታይው ትግል ላይ ነው፡፡ ጅራፍ እናጮሃለን፤ በሃይላንድ እቃ ጠጠር ከትተን እናንኳኳለን፣ ቆርቆሮ እንቀጠቅጣለን… አቃተን፤ ጥይት ሁሉ ተኩሰን ተኩሰን ጨርሰናል፡፡ ወደ እኛ ገና መግባቱ ነው ማታ ብርድ ስለማይወድ እህሉም ላይ የእንስሳቱም መኖ ላይ አርፎ ሲበላ ያድርና ሙቀት ሲነካው ይነሳል፡፡ አኛ አቅማችን እያለቀ ሰው እየተዳከመ ነው፡፡ ገና ሰሞኑን  ወደኛ በመግባቱ የመንግስት አካል ገና ወደ እኛ አልደረሰም፡፡ በብዙ ቦታ ስለተከሰተ ያንን ረጨን፣ ይሄንን ተከላከለልን ሲሉ በሌላ ቦታ አንበጣው ቀድሞ ያወድማል፡፡ ይህን ነገር መንግስትም አልቻለውም መሰለኝ፡፡ እኔም ይሄው አራት ጥማድ መሬት ላይ የዘራሁት ማሽላና ማሽ አይኔ እያየ እየተበላ ነው፡፡ ከዛሬ ነገ ደረሰልን ስንል ባዶ እጃችንን አጨብጭበን መቅረታችን ነው፡፡ መንግስት እንደሚያደርግ ያድርገን እንጂ መቼስ ምን እናደርጋለን… አንዴ ያመጣብንን፡፡ ሌላ የምለው የለኝም፤ መንግስት ይድረስልን፡፡

መንግስትዘላቂመፍትሔይሰጠን፤በመስኖእንጠቀም

አብዱ ሀሰን ሙሄ እባላለሁ፡፡ የ65 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ነኝ፡፡ ማሽላ፣ ሰሊጥና ማሽ ዘርቼ ነበር፡፡ በ10 ገመድ መሬት ሙሉ እህል ነው ውድም አድርጐ የበላብኝ፡፡ በኃይለስላሴ ጊዜ እኔ ልጅ ሆኜ አንድ ጊዜ አንበጣ ተከስቶ ነበር አስታውሳለሁ ግን እንደዚህ ይህን ሁሉ አገር አላወደመም ነበር፡፡ የዛን ጊዜ የነበረው አንበጣ አንዴ ያርፍና በአካባቢው ከሁለት ቀን በላይ አይቆይም፡፡ የዘንድሮው ለጉድ ነው፡፡ ምን አይነት መዓት እንዳመጣብን አናውቅም፡፡ እሱ አላህ ይድረስልን እንጂ፡፡ አንበጣው በአየር ቢረጭ በምን ቢደረግ ከአቅም በላይ ሆነ እንጂ መንግስት ሌት ተቀን ሊታደገን ሞክሯል፡፡ ያው አንዷም አውሮፕላን እዛ ማዶ ወደቀች፤ ይህንኑ አንበጣ ለማባረር መድሃኒት ስትረጭ፡፡ መድሃኒት እርጩ ተብለን በኬሚካል ብንል ብንል ምንም መፍትሔ አላገኘንም፡፡ ይሄው እዚህ ከ12 ቀናት በላይ ቆይቶ፣ የኛን አራባቴ ቀበሌንና ይሄን ዙሪያውን ጋራ በመለስ አውድሞ ሐሙስ እለት ሲጠግብና የሚበላው ሲያጣ ለቅቆ ሄደ እንጂ እኛን አሸንፎን ነው የቆየው፡፡

እንግዲህ መንግስትን የምንጠይቀው አንድ ዘላቂ ነገር ነው፡፡ እዚያ ማዶ የሚታይሽ ቦታ “ተኪኖ” ይባላል፡፡ ሶስት የውሃ ጉድጓድ ለመስኖ ብሎ አውጥቷል፡፡ በአፋጣኝ መስመሩን ከዘረጋልን ይሄንን ባዶ የቀረ እገዳ አጭደን ለከብት ሰጥተን፣ እንደገና ብናርሰው ቶሎ ቶሎ ለምግብነት የሚውሉ እህሎች ስላሉ እነሱን ዘርተን መጠቀም እንችላለን፡፡ ለመስኖ ተብሎ ከአመታት በፊት ተቆፍሮ ያለ አንዳች ጥቅም ተቀምጧል፡፡ እኛ ብንጠቀምበት ግን አመቱን ሙሉ ማምረት እንችላለን፡፡ ከራሳችን አልፎ ለሌላም እንተርፋለን፡፡ “አይ ስንዴና ዱቄት አቀርባለሁ” ካለ፤ ይህን ሁሉ ህዝብ አይችለውም፡፡ እንደሚመስለኝ ትልቁ ነገር ለጊዜያዊ የሚሆን ጦም ከማደር የሚያድነን ነገር ሰጥቶ፣ ከዚያ መስኖውን ማስፋፋት ነው ያለበት፡፡ አሁን እሸት ነበር ለልጆች እየቆረጥን የምናበላው፤ ባዶ እጃችንን ቀርተናል፤ ስለዚህ አስቸኳይ የእለት ቀለብ ግዴታ ያስፈልገናል፤ ዘላቂ መፍትሔ ነው ዋናው ነገር፡፡

ባዶመሬትአይንአይኑንለማየትመጥቼነውያገኘሽኝ

ዘሀቡ ሰይድ እባላለሁ የዚህ የአረባቴ ቀበሌ ኗሪ አርሶአደር ነኝ፡፡ የዘራሁት ማሽላ በሙሉ በአንበጣው ወድሟል፡፡ ደረሰልን ብለን ስንጠብቅ ይሄው እንግዲህ እንዲህ ሆነ፤ አላህ ያመጣው ነው፡፡ አሁን እዚህ ያገኘሽኝ ቆረቆንዳውን አጭጄ ለከብቶች ለመውሰድ ነው፤ እንደገናም እንደዛ በደንብ ይዞ የነበረ መሬት ባዶ መቅረቱ ህልም ህልም ነው የሚመስለኝ፡፡ ከዚህ ዝም ብዬ እየመጣሁ አየዋለሁ (እንባቸው በአይናቸው ግጥም አለ) የእንስሶቹን ቀለብ እኮ ነው አብሮ አመድ ያደረገብን ምን ቁጣ እንደመጣብን አላውቅም፡፡ እኔ ለልጆቼ ምን እንደምሰጣቸው አላውቅም፡፡ የሰባት ልጆች እናት ነኝ፡፡ አብዛኞቹ ገና ለስራ አልደረሱም፤ ተጨንቄያለሁ፡፡ ግራው ገብቶኛል፡፡ እርግጥ ከትላንት በስቲያ የመንግስት ኃላፊዎች መጥተው አይዟችሁ ከጐናችሁ ነን ብለው አጽናንተውናል፡፡ እነሱን ተስፋ አድርገን እጃችንን አጣጥፈን ተቀምጠናል፤ እኛ ምኑንም አናውቀው፤ መንግስት እንዳደረጉ ያድርገን ነው የምለው፡፡

በሴትነቴያፈራሁትማሽላናሰሊጥድራሹጠፍቷል

ፋጦ ፈንታው ዳምጠው እባላለሁ፡፡ ሶስት ገመድ መሬት ላይ ሰሊጥና ማሽላ ዘርቼ ጥሩ ይዞልኝ ነበር፡፡ ሁሉም ባዶ ሆኗል፡፡ መንግስት በአየርም በሰውም መድሃኒት እየረጨ አንበጣውን ለማጥፋት ብዙ ታግሏል፡፡ እኛም እሳት አንድዱ ቆርቆሮ ምቱ እየተባልን ያላደረግነው ነገር አልነበረም፡፡ ምን ዋጋ አለው፡፡ አንበጣው ሃይል አጠራቅሞ ባለጉልበት ሆኖ አንዴ ለጥፋት መጣ፤ በምን አቅማችን እንቻለው! ለከብቶቹ የሚሆነውን ብትይ… ዛፉን ብትይ ምኑን አስቀረልን፡፡ አሁን እዚህ የመጣነው ቆሮቆንዳውን ለመውሰድ ነው፡፡ ድጋሚ መጥቶ ካረፈ፣ ይህንኑ አገዳውን ያወድምብንና ከብቶቻችን ጦም ያድራሉ ብለን አሁንም ስጋት አለን፡፡

አምስት ልጆች አሉኝ፡፡ ባሌም በረሃ ገብቷል፡፡ እኔ እንደምታይኝ ያቅሜን ስታገል ከረምኩ አገኛለሁ ስል እንዲህ አይነት መዓት መጣ፡፡ ባሌ ህይወታችንን ለመቀየር ጅቡቲ ነው ያለው፡፡ ይሁን እንጂ እኔ አርሼ ከማገኘው ላይ ትንሽ መደጐሚያ ነበር ጣል የሚያደርግልኝ፡፡ አሁን ድንግርግር ብሎኛል፡፡ አንቺው እስኪ ተይኝ፡፡ ደሞኮ የራሴ መሬት የለኝም፡፡ ሶስት ገመድ መሬት ተጋዝቼ (የእኩል እያረስኩ ነበር) አሁን እሱም ባዶ ቀረ፡፡ መሬት ስለሌለንና እንደሰው አርሰን ልጆቻችንን ለማሳደግ ስላቃተን ነው ጅቡቲ በረሃ ገብቶ የሚሰቃየው፡፡ አሁን መንግስት ቃል በገባው መሰረት እንዲደግፈን እንፈልጋለን፤ ያለበለዚያ ማለቃችን ነው፡፡ ይህንኑ ነው የምለው፡፡

ጤፉንገለባየማጭደውለከብትነው

ኑርዬ በለቴ አህመድ እባላለሁ፡፡ የዚሁ የኢረባቴ ቀበሌ ኗሪና የ71 አመት አዛውንት ነኝ፡፡ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ሰሊጥና ማሾ ዘርቼ በጥሩ ሁኔታ ይዞልኝ ነበር፡፡ እሸትም መብላት ጀምረን ነበር፡፡ ይሄው ጤፉንም ፍሬ ፍሬውን እየላገ ሙልጭ አድርጐ በልቶ፣ ማሽላውንም ቆረቆንዳውን አስቀርቶ ቁጭ አድርጐናል፡፡ አሁን ይሄ ምን ሊረባ ታጭደዋለህ ትይኛለሽ! አንበጣውኮ የእኛንም የእንስሳቱንም ጉሮሮ ዘግቶ በልቶ ጠግቦ ነው የሄደው፡፡

የጤፉን ገለባ ለከብቶቼ ነው የማጭደው፡፡ እስኪ ተመልከቺው፡፡ አንዲት ፍሬ ለመሀላ የለውም፡፡ ምንም ነገር፡፡ 17 ገመድ መሬቴ ላይ ያለው ትያለሽ… ከሌላ ሰው ተጋዝቼ (የእኩል) አርሼ የዘራሁት ትያለሽ አንዱም አልቀረም፡፡ በዚህ የአዛውንት እድሜዬ ተሰድጄ አልሰራ… ይህን ላድርግ አልል… በጣም አዕምሮ የሚነካ ነገር ነው የገጠመን፡፡

መንግስት በአየር በምድር ኬሚካል እየረጨ፣ በጣም ታግሏል፡፡ ጉዳዩ ስር የገባ ጠላት ሆነበትና ከቁጥጥር ውጪ ሆነ እንጂ… በጣም ጥሮ ነበር፡፡ እኛም ቆርቆሮ በማንኳኳት የታጣቂን ዝናር በመተኮስ፣ እሳት በማቀጣጠል ሌት ተቀን ባዝነናል፡፡

ዞሮ ዞሮ አላለልንም… ምን እናደርጋለን… ከማዘን በስተቀር፡፡ የመጣብን ጠላት የሚገፋ አልሆነም፡፡ አንበጣው አሸንፎ በልቶ ሲጨርስና የሚበላው ሲያጣ ነው በራሱ ጊዜ ነቅሎ የወጣው፡፡ እኛ እንግዲህ ክረምቱን ጨለማውን ወቅት ወጣን፤ ብርሃን አየን ብለን ስንደሰት ወዳላሰብነው ጨለማ ገብተናል፡፡ ቀሪው ድጋፍ ከመንግስት ይጠበቃል፡፡

 

 

 

Read 4769 times Last modified on Friday, 16 October 2020 20:05
Administrator

Latest from Administrator