Monday, 19 October 2020 00:00

መንግስት ህግ የማስከበር ስራን አጠናክሮ እንዲቀጥል ኢህአፓ ጠየቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  “ፀረ ሠላም ሃይሎችን በጽናት እታገላለሁ” ያለው ኢህአፓ፤ ሀገራዊ ሰላምን የማረጋገጥና የዜጐችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው የተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮችን የሚመራው መንግስት፤ የጀመረውን ህግ የማስከበር ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በአጥፊዎች ላይም ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በቤኒሻንጉል ጉሙዝና  በኦሮሚያ መሽገው የዜጐችን ህይወት የሚቀጥፉ ህገ ወጥ ታጣቂ ቡድኖች ላይ ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ህግ የማቅረብ፣ በወንጀል ድርጊት ያልተሳተፉትን አጣርቶ ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው እንዲመለሱ የማድረግ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድም ኢህአፓ ጠይቋል፡፡
በሀገሪቱ በተደጋጋሚ ለሚፈፀሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችና የዜጐች መብት ጥሰት መንስኤው ህገ መንግስቱ ነው ያለው ኢህአፓ፤በኢትዮጵያ ውስጥ በገዥው ፓርቲና አጋሮቹ ለሚፈፀሙት ግፎች ሁሉ የመጀመሪያ ተጠያቂው ህገ መንግስቱና ግዛቱ ስለሆነ አስቸኳይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጠይቋል - በመግለጫው፡፡
የተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮችን የዳሰሰው ኢህአፓ፤ ከምርጫ በፊት በአፋጣኝ የብሔራዊ ምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ፣ በመላ ሀገሪቱ ሠላምና መረጋጋትን የማስፈን ተግባርም እንዲከናወን ሀሳብ አቅርቧል፡፡
በኮቪድ-19 ምክንያት በርካቶች በኑሮውድነትና በስራ ማጣት እየተንገላቱ መሆኑን፤ በ2012 በተከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሚሊዮኖች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን የጠቀሰው የፓርቲው  መግለጫ፤መንግስት የዜጐችን ኑሮ በማሻሻልና ለወጣቶች የስራ እድል በሚፈጥሩ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲያተኩር አሳስቧል፡፡ የሸቀጦች የዋጋ ግሽበትም ከሁለት አሃዝ በታች የሚወርድበትን የኢኮኖሚ አማራጭ እንዲተገብርም ኢህአፓ ጠይቋል፡፡
በደንቢዶሎ የታገቱ ተማሪዎችም ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠውና መንግስት እውነቱን ለቤተሰቦቻቸው እንዲያሳውቅ ጥሪ ያቀረበው ኢህአፓ፤ ሀገራዊ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠርና የፖለቲካ ቁርሾን በማስወገድ፣ዘላቂ ሠላምና እድገት የሰፈነባት ሀገር እንገንባ የሚል ጥሪ አስተላልፏል፡፡ 

Read 10565 times