Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 04 August 2012 10:13

እንደ አፍ አይቀናም!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አንድ ወዳጄ ነው፡፡ አሁን ሳይሆን ድሮ፡፡ አሁንማ ዳያስፖራ ሆኗል፡፡ ዳያስፖራ ብቻ ሳይሆን ፖለቲከኛ፡፡ የዳያስፖራ ፖለቲከኛ ደግሞ አያድርስባችሁ! ከአምስት ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ወደ አገሩ ለእረፍት የመጣው ዳያስፖራ (በ5 ዓመት ብቻ ዳያስፖራ ይኮናል እንዴ?) ሲተገትገኝ ሰነበተ - በዳያስፖራ የፖለቲካ ቋንቋ! “እዚህ አገር እኮ ተቃዋሚ ፓርቲ የለም!” አለኝ በቁጣ፡፡ ቁጣውን ወደ ጐን ገለል አድርጌ አሁን ያሉትን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አነበነብኩለት፡፡ ኢዴፓ፣ አንድነት፣ ራዕይ፣ መኢአድ፣ መድረክ፣ መኢዴፓ፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ ወዘተ… በማለት፡፡ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው …“ሰው ጥራ ቢሉት ራሱ መጣ” ብሎ ተረተብኝ (ዳያስፖራ ተረት ይችላል እንዴ?) ቢያናድደኝም ንዴቴን ከቁም ነገር ጋር አልቀላቅልም ብዬ ራሴን አረጋጋሁና ማስረዳት፣ ማብራራት፣ ማግባባት ያዝኩ… (ሰው አግኝቼ!) “ይኼውልህ ዳያስፖራ ወንድሜ …

እነዚህ የዘረዘርኩልህ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከስንት ዓመት ጀምሮ በተቃዋሚ ፓርቲነት ተመዝግበው ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው ናቸው … ህዝቡም በተቃዋሚነታቸው ነው የሚያውቃቸው” አልኩት (ልፋ ቢለኝ እኮ ነው!) ዳያስፖራዉ የለበጣ ፈገግታ እያሳየኝ “አንተም እኮ ፎማሊቲውን ካሟላህ ቦርዱ ፈቃድ ይሰጥሃል… ቁም ነገሩ ፈቃዱ አይደለም… በተቃዋሚነታቸው ምን ሚና ተጫወቱ ነው … ቢሮ ከፍተህ መጐለት እኮ ፋይዳ የለውም… ትግሉ የታለ? Where is my beef?… ይቅርታ አድርግልኝና ለእኔ ሁሉም የኢህአዴግ ተለጣፊዎች ናቸው … የገዢው ፓርቲ አሻንጉሊቶች! ተሳሳትኩ?” አለኝ - እየጮኸ፡፡ እንደ አንዳንድ የኢህአዴግ ደጋፊዎች መጮሁን እንዲተው አሳሰብኩትና ወደ ምላሼ ገባሁ፡፡

(ካልጮሁ ኢህአዴግን የደገፉ የማይመስላቸወ ቲፎዞዎች እንዳሉ ልብ ይባልልኝ!) “አዎ የተሳሳትክ ይመስለኛል … የምታወራው እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ ተቃዋሚዎች ከሆነ … በእርግጥም ተሳስተሃል…ምክንያቱም የተቃዋሚዎችን እንቅስቅሴ ካንተ ይልቅ እኔ በቅርብ አውቀዋለሁ … ምናልባት አንተ አሜሪካ ያሉ ተቃዋሚዎችን ታውቅ ይሆናል …” ዳያስፖራው ከአሜሪካ ቢመጣም የሰው መብት አያከብርም፡፡ ሃሳቤን እንድጨርስ እንኳ አልፈቀደልኝም፡፡ “ኖኖኖ… ዘመኑ እኮ ሰልጥኗል! በሶሻል ሚዲያ፣ በዌብሳይት እያንዳንዷ የአገር ቤት ወሬ ትደርሰናለች… ለነገሩ እዚህ አገር እኮ ነፃ ፕሬስም የለም በቅርቡ አንዱን ጋዜጣ አግደውታል… በተረፈ ግን ፈሪ ነው የተሰበሰበው … ታጋዮቹንማ ኢህአዴግ ለስደት ዳርጐአቸዋል … ፍራንክሊ ነው የምልህ ፍሪ ፕሬስ የለም … ከ97 በኋላ ታሪክ ሆኗል … ሳንሱር ተመልሶ መምጣቱንም ሰምተናል … ተሳስቼአለሁ?” አለኝ - በድል አድራጊነት ስሜት፡፡ በንዴት ጭስስ … ብዬ ቢወጣልኝ በወደድኩ፡፡ ግን ለጊዜው የመናደድ እንኳን ዕድል እንደሌለኝ አውቄአለሁ፡፡ አሁን ጊዜው ይሄን ዳያስፖራ የመመከት ነው - በመረጃና በማስረጃ የተደገፈ ምላሽ በመስጠት (አንዴ ፈርዶብኝ የለ!) ሆኖም ግን ለጠየቀኝ ጥያቄ ምላሽ ሳልሰጠው እሱው ቀጠለ - ዲስኩሩን፡፡ “ማይ ዲር… እኔና ጓደኞቼ በሰው አገር ተሰደን ያለነው ወደን ይመስልሃል? Come on! ጭንቅለትህን አሰራው እንጂ … እዚህች አገር ላይ ነፃነት ስለሌለ እኮ ነው … ህዝቡን ደሞ ታውቀዋለህ … ከነፈሰው ጋር ነው የሚነፍሰው … ተቃዋሚው ተለጣፊ … ፕሬሱ ፈሪ … ማን ተጠቀመ? ገዢው ፓርቲ!” አለና የታሸገ ፕላስቲክ ውሃውን አንደቀደቀ (ሲያንሰው ነው!)

ለዚህ ሰው ምንም ዓይነት መልስ መስጠት ወይም ለማሳመን መሞከር ከንቱ እንደሆነ የገባኝ በጊዜ ነው - ሳልደክም! ለእሱስ ቢሆን የአየር ሰዓት ሳገኝ አይደል፡፡ “ጀነሬሽኑ እኮ ወኔው ተሰልቧል! ልፍስፍስ እኮ ነው የሆነው… ትውልዱ ሞራሉ ላሽቋል… I am sorry to say it … But መሬት ላይ ያለው ሪያሊቲ ይሄ ነው… ብሎጌ ላይ ፖስት ያደረግሁትን አላየህም!” (የብሎግ ታጋይ አልኩ በልቤ!) እንደምንም ተቆጣጥሬው የነበረው ንዴቴ ድንገት ገነፈለ፡፡ ደሜ ተንተከተከ፡፡ “ጀነሬሽኑ ምን ይሁንልህ… ይሙትልህ …. ለምን አንተ አገርህ ላይ ሆነህ አትታገልም … ለምን ተቃዋሚ ፓርቲ መስርተህ በደንብ አትቃወምም… ወይም ደግሞ ነፃ ጋዜጣ መስርተህ ጀግንነትህን አታሳየንም! ወንድ ነኝ ያለ እዚሁ ይታገል!” አምባረቅሁበት፡፡

“Yes! That is it! ይሄንን ዓይነት ቁጡነት ነው የምፈልገው … እምቢ ለነፃነቴ የሚል ትውልድ ነው የናፈቀኝ … ፈዛዛ ደንጋዛ ወጣት የሌለ ያህል ነው… ቆይ ምንድነው የምትለኝ … ድግሪ ይዞ ኮብልስቶን አንጥፍ ሲባል አሜን ብሎ የሚቀበል ጄኔሬሽን ኢትዮጵያ ታበቅላለች? እርግማን እኮ ነው … ተሳሳትኩ?”

ዳያስፖራው ሙሉ በሙሉ ከስህተት ተድቦልቡሎ እንደተሰራ ቢሰማኝም እንዲያ ልለው አልፈለግሁም፡፡ ግን ውስጤ በብሽቀት እየተንተከተከ ነበር፡፡ በዚህ መሃል ነው አንዲት ነገር ብልጭ ያለችልኝ፡፡

“ይኼውልህ ወንድሜ፤ እናንተ ዳያስፖራዎች እንደ አንዳንድ ቅንጡ ሞጃዎች ናችሁ!” አልኩት (ያበጠ ይፈንዳ ብዬ፡፡)

“What do you mean! ቅንጡ ሞጃዎች ስትል?” አለኝ ዓይኑን አፍጦብኝ፡፡

“ቅንጡ ሞጃዎች  … ቀብር የሚሄዱት የቤት ሠራተኞቻቸውን አስከትለው ነው”

“So? ከእኛ ጉዳይ ጋር ምን ያገናኘዋል?” ጠየቀኝ - ዳያስፖራው፡፡

“ሠራተኞቹ የሚከተሉት እኮ ጃንጥላ ለመያዝ አይደለም …” አልኩት

“እኔ ምንስ ይዘው ቢከተሉ ምን አገባኝ! It is not my business” አለኝ - በንዴት ጦፎ፡፡

“ምን መሰለህ … ለቅሶ ሲጀመር ሞጃዎቹ ወይዛዝርት፤ የራሳቸውን ሳይሆን የሠራተኞቻቸውን ደረት ነው የሚመቱት … ለዚህ ነው የሚያስከትሏቸው” አስረዳሁት፡፡

“እና… ምን ለማለት ፈልገህ ነው?” የፊቱ ገጽታ ተለዋወጠብኝ፡፡

“እናንተም እንደ ቅንጡ ሞጃዎች እየሆናችሁ ነው … ለናንተ ነፃነት ትውልዱ እንዲታገል … ለናንተ ዓላማ ትውልዱ እንዲሞት ትፈልጋላችሁ” አልኩት ፍርጥም ብዬ (ይሞታል ታዲያ!)

“Never! Never! አልተግባባንም ማለት ነው … እኔ ሎካሉ ለብቻው ይታገል አላልኩም … ወኔውና ሞራሉ ይነቃቃ እንጂ … Join እናደርገዋለን … Support እንሰጠዋለን የጋራ አገራችን እኮ ናት … አየህ my dear … እኛ የዲሞክራቷን የአሜሪካ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል፣ የዲሞክራሲ ኤክስፒሪያንስ … ሼር እያደረግን ግንዛቤ እንፈጥራለን… ትውልዱን ኢንስፓየር እናደርጋለን … ተሳሳትኩ እንዴ?” አለኝ - በተለመደች ስታይሉ፡፡

“እንደ አፍ አይቀናም!” ብዬ ጥዬው ተነሳው፡፡

“Oh, my God! ይሄ እኮ ነው ችግራችሁ… ኋላ ቀርነት ያጠቃችኋል … ዲስከሽን አትወዱም …” በማለት ጠረጴዛውን በቡጢ ደበደበ፡፡ እኔ ግን ርቄአለሁ፡፡

ሌላ ቀን ነው፡፡ አንዱን የኢህአዴግ ቀንደኛ ካድሬ ወዳጄን አገኘሁትና ስለ ዳያስፖራው ሳጫውተው “ሰበብ ፈልጌ ለትንሽ ቀናት ወህኒ ቤት ላስከርችመው እንዴ!” አለኝ - ለማሰር እየጐመዠ፡፡

“የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ አሉ ስል ተረትኩበት፡፡

“ከምሬ እኮ ነው… ትንሽ ቢታሽ እኮ ሌላ ጊዜ አፉን አይከፍትም!”

“ያምሃል? ህግና መንግስት ባለበት አገር ዝም ብዬ ላሳስረው ትላለህ?” ተቆጣሁት፡፡

“አሸባሪ ሳይሆን አይቀርም ብዬ እኮ ነው… ተይዞ ቢመረመር ከጀርባው ማን እንዳለ ያወጣ ነበር”

ወዳጄን ድሮም ሳውቀው ካድሬ ነበር፡፡ ግን እንዲህ ጭፍን አልነበረም፡፡ እንግዲህ ምን እንደነካው የሚያውቀው ኢህአዴግ ብቻ ነው፡፡ ከሁሉም የማሳዝነው ግን እኔ ነኝ፡፡ ወዳጆቼን በየሰበቡ እያጣሁ ነው፡፡ ይብላኝ ለነሱ እንጂ በቅርቡ ዳያስፖራና ካድሬ ያልሆኑ ሰዎች ፈልጌ ወዳጅነት መመስረቴ አይቀርም፡፡ የማስታወቂያ ወጪዬን ስፖንሰር የሚያደርገኝ ካገኘሁ ደግሞ ጋዜጣ ላይ “ክፍት የጓደኝነት ማስታወቂያ” ማውጣቴ አይቀርም - “ከሃይማኖትና ከፖለቲካ ነፃ የሆኑና አደርባይነት የማያጠቃቸው ሁለት ጓደኞች ይፈለጋሉ” የሚል፡፡ በነገራችሁ ላይ ከአሜሪካ መጥቶ አንድ ሁለት ቀን እኔን ሲነዘንዝ፣ ሁለት ሳምንት ሙሉ፣ ቀን እየተኛ ሌሊት ሲጨፍር የሰነበተው ዳያስፖራ፤ ወደ ስደት አገሩ ተመልሷል (መረጃው ለካድሬው ወዳጄም ጭምር ነው!)

የእኔና የዳያስፖራው ንትርክ አምዱን ፈጀው አይደለ! እስቲ በቀረችን መጠነኛ ቦታ ደግሞ ሌሎች አጀንዳዎችን ዳሰስ ዳሰስ እናድርግ፡፡

ምሽት ላይ ነው፡፡ እተከራየኋት አንዲት ክፍል ቤት ውስጥ ቁጭ ብዬ ኢቴቪ ላይ አፍጥጬአለሁ፡፡ የስፖርት ጋዜጠኛው የለንደን ኦሎምፒክ ወቅታዊ ወሬዎችን ለተመልካቾች እያደረሰ ነው - በምስል እያስደገፈ፡፡ በመሃል ግን ከለንደን ዘሎ ወጣና የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን (መንገደኞች ይበዛሉ) ያነጋግር ገባ፡፡

ጋዜጠኛው ምን እየጠየቃቸው እንደሆነ አይሰማም፡፡ ነዋሪዎች ግን የአገራችን የአትሌቲክስ ቡድን ከለንደን ምን ያህል ወርቅ፣ ብርና ነሐስ ይዞ መመለስ እንዳለበት በየተራ ይናገራሉ፡፡ (ይወስናሉ ማለት ይቀላል) አንደኛው ስድስት ወርቅ ከቡድኑ እጠብቃለሁ ሲል፤ ሌላው አምስት ይላል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ሦስት … ትዕዛዝ ይሁን ምኞት ወይም ህልም አይታወቅም፡፡  ሁሉም የሚሉትን ሳዳምጥ ቆየሁና “እንደ አፍ አይቀናም!” አልኳቸው - በሆዴ፡፡ እኔ የምለው ግን… እንዲህ ያለው ጥያቄ ለማነው መቅረብ ያለበት?... ጋዜጠኛውስ ቢሆን እንዲህ ያለ እርባና የሌለው ጥያቄ ይዞ መንገደኛ የሚያስቸግረው ለምንድነው?

ሌላ በኢቴቪ መስኮት የታዘብኩትን ጉዳይ ደግሞ ላጋራችሁ፡፡ አንድ ገበሬ (አርሶ አደር) በአንድ በሬና በአንድ አህያ መሬቱን ሲለው ይታያል - ሲያርሰው፤ ሲፈነቃቅለው፡፡ በኋላ ዲስኩር ጀመረ (ምነው አርፎ ቢያርስ!) ዲስኩሩ ምን መሰላችሁ? ምርቱን በቀጣዩ ዓመት በእጥፍ እንደሚያሳድግ የሚያበስር ነው፡፡ ይታያችሁ በትራክተር ወይም በሌላ ዘመናዊ መንገድ (መሳሪያ) አላለንም … በዚያው በሬና አህያ ነው፡፡ (እንደ አፍ አይቀና ማለት ይሄኔ ነው፡፡) ለአትሌቲክስ ቡድናችን ድል እመኛለሁ፡፡ አንድ የረሳኋትን ቁምነገር ልንገራችሁና ልሰነባበት፡፡ በለንደኑ ኦሎምፒክ በማካሄደው የተኩስ ውድድር ቻይናዎች ድል እንደቀናቸው ስሰማ በጣም በጣም ተቆጨሁ! (ያ ሁሉ የአገሬ ተኳሽ የት ገባ - ፉከራ ብቻ!)

በ3ሺ ሜ. መሰናክል አገራችንን ወክሎ የተወዳደረው አትሌት ገና በማጣሪያው ወድቆ መሰናከሉን አያችሁልኝ (አይፈረድበትም) “ካልጠገቡ አይዘሉ፤ ካልዘለሉ አይሰበሩ” የሚል ተረት እየሰማ እኮ ነው ያደገው!

 

 

Read 5127 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 10:32