Monday, 19 October 2020 00:00

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ሃብታቸውን ባላስመዘገቡ ባለስልጣናት ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ ሊወስድ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(6 votes)

 - ሃብታቸውን ያላስመዘገቡ የመንግስት ባለስልጣናት ዝርዝር ደርሶለኛል ብሏል
       - በ3 ወራት ውስጥ አለአግባብ የተመዘበሩ ከ412 ሚ. ብር በላይ የመንግስት ንብረት እንዲመለሱ ተደርጓል
                    ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ሃብታቸውን የማስመዝገብ ግዴታቸውን ባልተወጡ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል። ሃብታቸውን ያላስመዘገቡ የመንግስት ባለስልጣናት ስም ዝርዝር ከስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንደደረሰውና ለእነዚሁ ባለስልጣናት ሀብት የማስመዝገቢያው ጊዜ በመጠናቀቁ፣ በቅጣት ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ደብዳቤ መፃፉን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ ላይ አመልክቷል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በሰጠው በዚሁ መግለጫው፤ መንግስት ያወጣውን ህግና መመሪያ ተከትለው ሃብታቸውን በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያስመዘገቡ ባለስልጣናት የመኖራቸውን ያህል የተላለፈውን ሃብት የማስመዝገብ ግዴታ ችላ ብለው ባሳለፉ ባለስልጣናት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡
የፀረ ሙስና ኮሚሽን በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ቀርበው ሃብታቸውን ያላስመዘገቡ የመንግስት ባለስልጣናትን ስም ዝርዝር ልኮልናል ያሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፤ ለእነዚህ ባለስልጣናት ግዴታቸውን እንዲወጡ የሚጠይቅ ደብዳቤ ልከንላቸዋል ብለዋል፡፡ የተላለፈውን ጥሪ ተቀብለው በተሰጣቸው ዕድል በማይጠቀሙ ባለስልጣትና ላይ ህግ  የማስከበር እርምጃዎችን በቅርቡ መውሰድ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ዶ/ር ጌዲዮን እንደተናገሩት፤ ባለፉት 3 ወራት ብቻ 33ሺ714 መዝገቦችን አቅርበው ክርክር ያደረጉ ሲሆን በወንጀለኞች ላይ ክስ መስርተው ቅጣታቸውን እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር በኢኮኖሚ ወንጀል በፍ/ቤት ጥፋተኛ የተባሉ ተከሳሾች በወንጀል ያገኙትን ሀብት እንዲወረሱ ያደርጋል ብለዋል፡፡ እስከአሁንም ድረስ ያለአግባብ የተመዘበረ 412 ሚሊዮን ብር የመንግስት ንብረት እንዲመለስ መደረጉንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የህግ ስርዓቱን ለማዘመን በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ የገለፁት ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ፤ የንግድ ህጉ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉና ስነስርዓት ህጉን እንዲሁም የግልግል ዳኝነት ህጉን ጨምሮ የተለያዩ ህጐች እየወጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ህጐችም በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት ላይ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍቱ እንደሚሆኑ ዶ/ር ጌዲዮን አስታውቀዋል፡፡
ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በተፈጠረው የሰዎች ሞትና የንብረት ውድመት፤ በፌደራል በ114 መዝገቦች ከሶስት ሺህ በለይ ተጠርጣሪዎችን፣ በኦሮሚያ ዳግም ከሁለት ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱን ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የደረሰውን የንፁሀን ግድያ የሚያጣራ ቡድን ወደ ስፍራው ተልኮ ምርመራው መጀመሩንም ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ገልፀዋል፡፡

Read 11270 times