Wednesday, 21 October 2020 00:00

ወታደራዊ ትዕይንት፣ የመስከረም ውበት፣ የትምህርት መራቆት

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(0 votes)


           መስከረም፣ በመልካም ተስፋና በብሩህ መንፈስ የደመቀ ልዩ ወር እንዲሆን ማን መረጠው? ይበዛበታል ማለቴ አይደለም፡፡ አይበዛበትም፡፡ መራጭ አያሻውም ማለቴም አይደለም፡፡ በተፈጥሮው፣ ከሌሎች የተለየ ብርሃናማ ወር ነው፡፡ ለበዓላት የተመረጠ ድንቅ የፌሽታ ወርም ነው፡፡ በተፈጥሮም የተዋበ፣ በጥበበኞችም የተመረጠ ነው -የመስከረም ክብር፡፡
በተፈጥሮ የአደይ አበባ ሲፈነዳ፣ “ኢዮህ አበባዬ” የሚለው ዜማም በጥበበኞች ይፈልቃል፡፡ የተፈጥሮና የአእምሮ ህብር፣ የእውነታና የእውቀት ጋብቻ ነው መስከረም።
በአንድ በኩል፣ ልምላሜ የሚደምቅበትና አበቦች የሚፈኩበት ብሩህ የመስከረም ወር፣ የወደፊቱንም ተስፋ ይፈነጥቃል። በክረምት የተዘራው፣ ለምልሞና አብቦ መልካም ፍሬው በመስከረም ይበረክታል። አዝመራው እንደሚበዛም፣ የምስራቹን በመስከረም ወር ከወዲሁ እንመለከታለን። በእውን የሚታይና የሚጨበጥ የኑሮ ተስፋን የሰነቀ፣ ያማረ የተፈጥሮ ውበትንም የተጐናፀፈ ነው - የመስከረም ተፈጥሮ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከተፈጥሮው ጋር በሚመጥን ሁኔታ፣ የመስከረም ሰው ሰራሽ ገጽታውም፣ ድንቅና ውብ ነው፡፡ ለበዓላት ተመርጧል፡፡ ጥበበኞች፣ መስከረምን ለማድመቅና ለማክበር መምረጣቸው፣ ከመስከረም ተፈጥሮ ጋር ይጣጣማል። የበዓላትና የውበት፣ የደስታና የድግስ፣ የጭፈራና የፍንደቃ ወር አድርገውታል፡፡ የመስከረም ወር ተፈጥሮና የዜማ እልልታ፣ ውስጡና መልኩ ገጥሟል፡፡
ትምህርትስ? ውስጡና መልኩ ተስማምቷል?
የትምህርት ዝንባሌና የእውቀት ጉጉት የሌለው ስልቹ ልጅ ይኖራል፡፡ ነገር ግን፣ በመስከረም ወር ትምህርት እስኪከፈት፣  ይቸኩላል፡፡ መስከረም ሲጠባ፣ በአንዳች ብሩህ ስሜት፣ ለትምህርት የማይቁነጠነጥ ተማሪ የለም ማለት ይቻላል፡፡
ለአብዛኞቹ ልጆች፣ መስከረም ትምህርት ሲከፈት፣ ፌሽታ ነው፡፡ አዲሱ ዓመት፣  ከአምና ካቻምና የተለየ፣ እንደ አበቦች የፈካ ዓመት የሚሆን ይመስላቸዋል፡፡ መሆንም ነበረበት፡፡ አጓጊ የእውቀት ዓመት እንዲሆንላቸው ምን ያህል እንደሚመኙ አይታያችሁም? ደብተር መጽሐፋቸውን አሳምረው ለማዘጋጀት ሲሯሯጡ ተመልከቱ። ውድና ድንቅ የእውቀት ጉጉት፣ ሳይበርድ ሳይበረዝ፣ አብሯቸው እንዲሰነብትና እንዲዘልቅ እንመኝላቸው፡፡ ነገር ግን፣ ምኞት ብቻ አይበቃም፡፡
ከመመኘት አልፈን ምን ማገዝ እንችላለን? በዚህ፣ በዚህ ትምህርት ሚኒስቴርና የየክልሉ የትምህርት ቢሮዎች፣ ቁምነገር አትጠብቁ። በተለይ ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ፣ የአቅማቸውን ያህል እውቀትን ለማሰናከል እንጂ ለማገዝ የሚሞክሩ አልሆኑም፡፡ ይሄ፣ ድብቅ ሚስጥር አይደለም፡፡ “ስራችን፣ መረጃንና እውቀትን ማንቆርቆር አይደለም” እያሉ በይፋና  በተደጋጋሚ ነግረውናል - የትምህርት ባለስልጣናት፡፡
እውቀትን ምንኛ እንደጠመዱት! እውቀትን ከማንቋሸሽ ሱስ ቢላቀቁና፣ ወደ ህሊናቸው ቢመለሱ ምን አለበት? እውነተኛ መረጃንና እውቀትን፣ በቅጡ ማስጨበጥ፣ ለአስተማማኝ ብቃትም ሁነኛ መሰረት መገንባት፣ ዋናው የትምህርት ዓላማ ነው፡፡
ይህንን መካድና ማስካድ፣ የብዙ ሚሊዮን ህፃናትን ህይወት መቀለጃ ማድረግ፣ አቻ የለሽ ጥፋት እንደሆነ አይረዱትም? በረዥሙ ማሰብ የምንችል ከሆነ፣ “እውቀትን የሚያንቋሽሽ ትምህርት”፣ ቁጥር አንድ የአገር አደጋ እንደሚሆንብን መገንዘብ አያቅተንም፡፡
ፊደልን ከማስያዝ ጀምሮ መሰረታዊ የማንበብና የመፃፍ እውቀትን ማስጨበጥ፣ የትምህርት ዓላማ አይደለም? አንድ ሁለት ብሎ ቁጥርን ከማስያዝ ጀምሮ፣ የመደመርና የማባዛት ስሌቶችን ማሳወቅስ፣ የትምህርት ዓላማ አይደለም? የትምህርት ሚኒስቴር ሰዎች፣ ይህን እውነት ቢገነዘቡ፣ ስንት የአገር ችግርን ለማቃለል በቻሉ ነበር፤ ለብሩህ ዘመን ፋና አብሪ፣ ለስልጣኔ ታሪክም መንገድ መሪ መሆን በቻሉ ነበር። አሁን ግን፣ የትምህርት ባለስልጣናት፣ በአመዛኙ፣ የእውቀትን መንገድ የሚዘጉ፣ አቅጣጫ የሚያስቱ ሆነዋል፡፡ ወደ ህሊና መቼ እንደሚመለሱ እንጃ፡፡ እስከዚያውስ? እስከዚያው ድረስ፣ እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ የለብንም፡፡
ሁሉም ወላጅ፣ በየፊናው ልጆቹን ለትምህርትና ለእውቀት ማበረታታት አለበት፡፡ ሌላስ? በቅጡ የተዘጋጁ የመማሪያ መፃሕፍትን አፈላልጐ ለመግዛት መጣር፣ የወላጅ ኃላፊነት ነው፡፡
ግን፣ በቅጡ የተዘጋጁ ጥሩ የመማሪያ መፃሕፍትን፣ ከቀሽም ዝርክርክ መፃሕፍት ለይቶ ማወቅ እንዴት ይቻላል? “በትምህርት ሚኒስቴርና በትምህርት ቢሮ የሚታተሙ መፃሕፍት አይሆኑም፡፡ ጥሩ የመማሪያ መፃሕፍት ከእነዚህ ይለያሉ” ብለው መልስ የሚሰጡ ይኖራሉ፡፡ አባባላቸው፤ ከሞላ ጐደል ስህተት አይደለም፡፡ ነገር ግን፣ ይሄ አባባል፣ በቂ መልስ አይደለም፡፡ ዘዴዎች ያስፈልጋሉ፡፡
ሁለት ዘዴዎች አሉ፡፡ አንዱ ዘዴ የባለሙያዎች ነው፡፡ ሌላኛው ለወላጆች የሚጠቅም ዘዴ ነው፡፡
የመማሪያ መጽሐፍን ለመምረጥ፣ አሪፉን ከቀሽሙ ለመለየት፣ ትክክለኛ የሙያ መመዘኛዎች አሉ፡፡ የመጽሐፉ ይዘት፣ ከነምልዓቱ፣ ቅደም ተከተሉም ከነተጓዳኙ ጋር፣ ተብጠርጥሮ ይፈተሻል፡፡ የአቀራረብ ዘዴውም፣ ግልጽነቱና መሳጭነቱ፣ ልቅም ተደርጐ ይመረመራል፡፡ አሪፍና ቀሽሙም ይለያል፡፡ የትምህርት ባለሙያዎች፣ እዚህ ላይ ነበር ፋይዳቸው፡፡ በሙያዊ መመዘኛ አማካኝነት፣ መፃሕፍትን በዝርዝር ፈትሸው፣ አንጥረውና አጣርተው፣ አሪፍና ቀሽም መፃሕፍትን ለመለየት ይረዳሉ፡፡ ነገር ግን፣ አብዛኛው ወላጅ፣ በራሱ  አቅም ምንም መላ የለውም ማለት አይደለም፡፡  
ወላጆች፣ ለልጆች መማሪያ መጽሐፍ መምረጥ ይችላሉ
ወላጆች ቀለል ያሉ ጠቃሚ ዘዴዎችን መጠቀም ይችላሉ፡፡ አንደኛ ነገር፣ አብዛኞቹ ወላጆች፣ ለልጆች የመማሪያ መጽሐፍ ሲገዙ፣ አንብበው መሞከር አያቅታቸውም፡፡
ግንዛቤ ለመጨበጥ መጽሐፉ ይረዳል? ወይስ ግራ ያጋባል?
መጽሐፉ  በቂና ግልጽ ምሳሌዎችን ያቀርባል?
ነጥብ በነጥብ፣ ደረጃ በደረጃ፣ ወደ ግልጽ የጽንሰ ሃሳብ ግንዛቤ የሚመራ ነው?
ያለ አስተማሪ፣ መጽሐፉን አንብቦ መረዳት ይቻላል? ይህን ለማረጋገጥ፣  ወላጆች፣ ራሳቸው አንብበው መሞከር አለባቸው፡፡
እያንዳንዱ አረፍተነገርና አንቀጽ፣ እዚህና እዚያ ሳይረግጥ፣ ወዲህና ወዲያ ሳይዝረከረክ፣ በተጓዳኝና በቅደም ተከተል፣ እርስ በርስ በተዋደደ መንገድ፣ ሙሉውን ምዕራፍ ይገነባል? የመጀመሪያው ምዕራፍ፣ ለቀጣዮቹ ምዕራፎች አስተማማኝ የግንዛቤ መሰረት እየሆነ፣ አንዱ በሌላው ላይ እየገነባ ይቀጥላል?
ብዙ ሺ ጥያቄዎች፣ በጥራትና በቅደም ተከተል፡፡
እያንዳንዷን የእውቀት ቅንጣት፣ በሁሉም ገጽታዎቿ ለማገናዘብና ከራስ ጋር ለማዋሃድ የሚያስችሉ፣ በቂ ምሳሌዎችን ይዟል? ብዙ ጥያቄዎችና መልመጃዎች በመጽሐፉ ውስጥ ተካትተዋል?
የጥያቄዎች ጥራትና ብዛት፣ የአሪፍ መጽሐፍ መለያ ናቸው፡፡ በጥንቃቄ የተዋቀረ፣ የጥያቄዎች ቅደም ተከተልም፣ የምርጥ መጽሐፍ አንድ ባሕርይ ነው። የመጀመሪያዎቹን ጥያቄዎች መስራትና መለማመድ፣ ቀጣዮቹን ጥያቄዎች ለማገናዘብና ለማስላት ጥሩ መንደርደሪያ መሆን አለበት፡፡ ይህንም ለማረጋገጥ በተግባር ሞክሩ፡፡
በአጭሩ፣ ወላጆች፣ በራሳችሁ አቅም፣ አሪፍና ቀሽም የመማሪያ መፃሕፍትን ለመለየት መጣር ይገባችኋል፡፡ እንዴት? መጽሐፉን፣ ያለ አስተማሪ፣ ከመነሻው፣ አንድ በአንድ እያነበባችሁ፣ ባነበባችሁት መሰረት ጥያቄዎችን አንድ በአንድ እየሰራችሁ ሞክሩት፡፡ ለዚህ የምታጠፉት ጥቂት ጊዜና ጉልበት፣ በጭራሽ አይቆጭም - ለልጆቻችሁ ጥሩ የመማሪያ መጽሐፍ ለመምረጥ ይረዳችኋልና፡፡
ቢያንስ ቢያንስ፣ ሁለት ነገሮችን ለማስተዋል መሞከር ይኖርባችኋል፡፡
በመማሪያ መጽሐፉ ውስጥ የተካተቱት ጽሑፎችና ማብራሪያ ምስሎች፣ ልቅም ተደርገው በጥንቃቄ የተዘጋጁና  ለግንዛቤ የሚመቹ ናቸው ወይ? ይህንን ለማየት መሞከር፣ አንድ ቁምነገር ነው፡፡
ሁለተኛው ቁምነገር፣ በመማሪያ መጽሐፍ ውስጥ፣ በርካታ ሺ ጥያቄዎችና መልመጃዎች፣ በስርዓትና በጥንቃቄ መካተታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የሂሳብ መማሪያ መጽሐፍ ውስጥ፣ በእያንዳንዱ ንዑስ ምዕራፍና ከዚያም በየምዕራፉ፣ ብዙ ጥያቄዎች ከሌሉ፣ ጥሩ የመማሪያ መጽሐፍ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ፣ በርካታ ሺ ጥያቄዎች ሊኖሩት ይገባል፡፡ የካምብሪጅ የመማሪያ መፃሕፍት ምርምር ተቋም፣ እነዚህን መመዘኛዎች አጉልቶ ያመለክታል፡፡
በአጠቃላይ፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የየክልሉ ቢሮዎች፣ ወደ ህሊና እስኪመለሱ ድረስ፣ ወላጆች ይህችን ታክል የድርሻቸውን መጣር ይችላሉ፡፡ መጣር ስለሚችሉም፣ መጣር ይገባቸዋል - ፋይዳ አለውና፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር እና ቢሮዎች፣ እውቀትንና መልመጃ ጥያቄዎችን በጥላቻ እየተመለከቱ፣ የመማሪያ መፃሕፍትን እያራቆቱ፣ በቅራቅንቦ ከማጨቅና በዘፈቀደ ከማዝረክረክ አባዜ እንዲላቀቁም እንመኝላቸው፡፡
ከዚያም፣ ለመፃሕፍት ህትመት የተመደበውን በጀት ከመግለጽና የመፃሕፍትን ሽፋን ከማድመቅ ባሻገር፣ ውስጣቸውም የእውቀት ግንዛቤን በሚያስጨብጥ ይዘት የተሟሉ እንዲሆኑ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ እውቀትን ለማስረጽና ከራስ ጋር ለማዋሃድ የሚጠቅሙ፣ ብዙ ሺ ጥያቄዎችንና መልመጃዎችን፣ በጥራትና በስርዓት ማሟላትም የግድ ነው፡፡ በቅጡ የተዘጋጁ የመማሪያ መፃሕፍት እንዲኖሩ መጣር፣ የእያንዳንዱ ባለሙያ ኃላፊነት ነውና፡፡
የትምህርት ይዘቱና መልኩ፣ ውጤቱና እርከኑ፡፡
የትምህርት ዘርፍ፣… የሂሳብ፣ የሳይንስ፣ የቋንቋ፣ እየተባለ በፈርጅ “ተጐዳኝቶ የሚፈረጀው”፣ አለምክንያት ለወግና ለስም ያህል ብቻ አይደለም፡፡ የ1ኛ ክፍል፣ የ2ኛ፣ የ3ኛ፣ የ9ኛ ክፍል፣ የ10ኛ፣ ተብሎ፣ በእርከን፣ ቀዳሚና ተከታዩ፣ በትምህርት ደረጃ “ተሰናስሎ የሚደራጀውም”፣ እንዲሁ ለመልክና ለወግ ያህል ብቻ አይደለም። በዘርፍና በእርከን፣ በቅጡ ያልተፈረጀና ያልተደራጀ፣ የዘፈቀደ ትምህርት፣ “ኦና ትምህርት” እንደማለት ነው፡፡ “የቅራቅንቦ ክምር” ብቻ!
ነገሮችን በዓይነት ከፋፍሎ እየፈረጀ፣ ግን ደግሞ በተጓዳኝ እያዋሃደ ነው የሰው አእምሮ እውቀትን የሚያዳብረው፡፡
ነጥብ በነጥብ፣ ደረጃ በደረጃ፣ ቀስ በቀስ፣ በእርከን እየተራመደ፣ ግን ደግሞ ቀዳሚውን ከተከታዩ ጋር እያስተሳሰረ ነው፤ የሰው አእምሮ እውቀትን የሚገነባው፡፡
ይሄ፤ ውስጣዊ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው - ድንቅ የሰው ተፈጥሮ፡፡ ከዚህ ውስጣዊ ተፈጥሮ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት - የትምህርት ውጫዊ ገጽታ፡፡ እንዴት?
ሁሉንም ነገር፣ በደፈናው ጥቅልል አድርጐ ማወቅ ብሎ ነገር የለም፡፡ በአንድ ጊዜ አጠናቅቆ ማወቅ የሚባል ነገርም የለም።  
እውቀትን መጨበጥና መገንባት፣ በዘፈቀደ ወይም በደፈናው ሳይሆን፣ በፈርጅ ተጐዳኝቶ፣ በእርከን የሚደራጅ መሆን አለበት፡፡
ፊደል ቆጥሮ፣ ማንበብና መፃፍ መጀመር የ1ኛ ክፍል ትምህርት ነው፡፡ አንድ ሁለት ብሎ መቁጠር፣ የመደመርና የማባዛት ቀላል ስሌትም፣ በ1ኛ ክፍል ላይ መከናወን ይገባዋል፡፡ ከዚያም ወደተከታዩ እርከን ይሸጋገራል ወደ 2ኛ ክፍል፡፡
አሁን እንደምናየው ግን፣ ግማሽ ያህሉ፣ ማንበብና መደመር ሳያውቁ፣ ይሻገራሉ። እውቀት ሳይጨብጡ ከክፍል ክፍል መሸጋገር፣… “ከ1ኛ ወደ 2ኛ ክፍል መሸጋገር” ብሎ መናገር ትርጉም ያጣል፡፡ የ9ኛ ክፍል ፊዚክስ፣ የ10ኛ ክፍል ሂሳብ የተሰኙት ነገሮችም፣ ስም ብቻ ሆነው ይረክሳሉ፡፡ ትርጉም አልባ ስያሜ፣ ይዘት የለሽ “መያዣ”፣ ውስጠ ባዶ ቅርጽ፣ መደበኛ ስራ የሌለው የደንብ ልብስ፣…እንደማለት ይሆናሉ፡፡
ይሄ የመርከስና የመክሰር ጐዳና ነው። በእርግጥ፣ ውጫዊው ቅርጽና መልክ፣ መጠሪያ ስምና መለያ ምልክት፣ ሽፋንና ልብስ፣ ክብር ይገባቸዋል፡፡ ለዚህም፣ ውጫዊው መልክና ቅርጽ፣ ከውስጣዊው ይዘትና መዋቅር፣ መነጠል የለበትም። ስያሜውና ምልክቱ፣ እውኑን ምንነት ከማስተዋልና ከመገንዘብ የተዋደደ እንጂ የተጣላ መሆን አይገባውም፡፡ የመስከረም ደማቅ በዓላት፣ ከውብ የመስከረም ተፈጥሮ ጋር የተስማሙ መሆናቸውን አስታውሱ፡፡ ውስጡም ውጪውም መዋደድ አለባቸው። ስያሜው ምንነትን፣ እርከኑ እውቀትን የሚመሰክር መሆን ይኖርበታል፡፡
ውጫዊው መለያ ልብሱና አኳኋኑም፣ ውስጣዊውን ምንነት የሚያሳዩ ገጽታዎች መሆን ይገባቸዋል፡፡
በዚህም ነው፤ ወታደራዊ የሰልፍ ስነስርዓትና ትርዒት፣ በ“ማርሽ ሙዚቃ ታጅቦ”፣ በጥራት ተዘጋጅቶ ሲቀርብ፣ መልካም ትርጉምና ስሜት የሚኖረው። ወታደራዊ ሰልፍ፣ ውጫዊ ገጽታ ነው፡፡ ትዕይንት ነው፡፡ ግን ውስጣዊውን ምንነትና ብቃትን አውጥቶ ያንፀባርቃል፡፡
የወታደራዊ ሰልፍ ትርጉም - ውበት ወይስ ዛቻ?
በአዲስ ዓመት ዋዜማ፣ የወዳጅነት ፓርክ ምረቃ ላይ የቀረበውን አይታችኋል - የክብር ዘብ ወታደራዊ ትዕይንት፡፡ ከዚያም የፖሊስ “ወታደራዊ” ትርዒት አይተናል፡፡ በእርግጥ፣ “ፖሊስ” የሚለው ስም፣ “ወታደራዊ” በሚል ቅጽል ሲታጀብ፣ ትንሽ ግር ይላል፡፡ ለምን?
በአንድ በኩል፣ የፖሊስ ስራ፣ “ህግና ስርዓትን የመጠበቅ ስራ ነው” ማለት ይቻላል፡፡ ከስርቆት እስከ ድብድብ፣ ከመኪና አደጋ እስከ ድብቅ ግድያ ድረስ፣  ወንጀሎችን መከላከልና መርምሮ ለህግ ማቅረብ፣ የፖሊስ ዋና ስራ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ፣ ከባድ የህልውና ስራዎች፣ እንደሆኑ አይካድም፡፡ ከዚህ አንፃር፣ የፖሊስ ስራዎች፣ “ከወታደራዊ” ጉዳዮች ጋር ብዙም ላይቀራረቡ ይችላሉ፡፡
በሌላ በኩል ግን፤ “ወታደራዊ” የፖሊስ ስራዎችም አሉ፡፡ ሁከቶችንና ዓመፆችን መግታት፣ እንዲሁም፣ የውንብድና ቡድኖችን፣ የትጥቅ አመፀኞችንና ወታደራዊ የሽብር ድርጅቶችን መከላከልና ማስወገድ - የፖሊስ ተገቢ ስራ ነው፡፡ ይህን ስናስብ፣ የፖሊስ “ወታደራዊ የውጊያ ገጽታ”፣ ያን ያህልም ግር የሚያሰኝ አይሆንብንም፡፡
ለነገሩ፣ ፖሊስ፣ ከአላማውና ከስራው ባሕርይ የተነሳ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ የጦር መሳሪያ የሚታጠቅ ሃይል ነው፡፡ እነዚህን የፖሊስ ሥራዎችና ባሕርያት፣ “የፖሊስ ምንነትና ውስጣዊ ተፈጥሮ” ብለን ልንገነዘባቸው እንችላለን፡፡
ጥያቄው ምንድነው?  ወታደራዊ ሰልፍ፣ ለምን አስፈለገ? የሚል ነው ጥያቄው፡፡ ለመከባበሪያ፣ ለማስጠንቀቂያ፣ ለማስፈራሪያ፣ ሊያገለግል ይችላል - እግረመንገድ፡፡ እና፣ በስርዓት ተሰልፎ፣ የደንብ ልብሱን አስተካክሎ፣ ተራንና ረድፍን ጠብቆ፣ እንቅስቃሴን አስተባብሮና ፍጥነትን ለክቶ፣ እርምጃን አሳምሮ ማሳየት፣ ምን ይፈይዳል?  ከፖሊስም ሆነ ከወታደር መደበኛ ምንነትና አላማ፣ ከመደበኛ ስራና አሰራር ጋር ምን ግንኙነት አለው?
የወታደርም ሆነ የፖሊስ መነሻ አላማ፣ “ሕግና ስርዓትን ማስከበር” ነው፡፡ የእለት ተእለት ስራውና መድረሻ ውጤቱስ? አላማውን ከማሳካት ውጭ፣ ሌላ ስራና መድረሻ ሊኖረው አይገባም፡፡ መነሻውና መድረሻውን የሚያገናኝ የአሰራር መንገዱስ? "ሕግና ስርዓትን ማክበር ነው” መንገዱ፡፡
በአጭሩ የፖሊስና የወታደር መለያ ተፈጥሮ ምንድነው ቢባል፣ መልሱ “ሕግና ስርዓትን ባከበረ መንገድ፣ ህግና ስርዓትን ማስከበር” የሚል ነው፡፡
የዚህን ትርጉም ተመልከቱ፡፡
የፖሊስና የሌላ ሰው ልዩነት - የትዕዛዝና የነፃነት!
ማንኛውም ሰው፣ “ወንጀል አትስራ፣ ከዚያ ውጭ እንደ ምርጫህ” በሚል መርህ ኑሮውን መምራት ይችላል፡፡
ፖሊስና ወታደርስ? “ወንጀልን አትስራ፣ በህግ የተከለከሉ ነገሮችን አትፈጽም።” የሚል መርህ በቂ አይደለም፡፡ “በህግ የተፈቀደልህን ስራ፣ በተፈቀደልህ ህጋዊ ስርዓት መሠረት ብቻ ትፈጽማለህ” የሚል መርህ ይጨመርበታል፡፡  ይሄ፣  ትክክለኛው የፖሊስና የወታደራዊ ሃይል መርህ ነው፡፡
ለማንኛውም ሰው፣ “ከወንጀል በቀር፣ ሁሉም የተፈቀደ ነው፡፡ በህግ ያልተከለከለ ሁሉ፣ የተፈቀደ ነው፡፡ የሚበጅህን መምረጥ፣ ነፃነትህ ነው” የሚል መርህ አለ፡፡
ለመንግስት ሲሆንስ፣ ለፖሊስና ለወታደር ሲሆን፣ “በህግ የፈቀደልህንና የታዘዝከውን ብቻ ስራ፡፡ በህግ ከተፈቀደልህ ነገር በስተቀር ሁሉም ክልክል ነው” ይላል - መርሁ። በሌላ አነጋገር፣ ከወታደርና ከፖሊስ ጋር  “ህግና ስርዓት” ሁሌም ጐልቶ ደምቆ መታየት ይኖርበታል፡፡ “የአሰራር ደንብና መመሪያ”፣ የሁልጊዜ መንገዳቸው መሆን አለበት፡፡ ከመስመር ሳይወጣ፣ ግራ ቀኝ ሳይዛባ፣ አቅጣጫውንና መንገዱን በትክክል ይዞ መራመድ አለበት፡፡
ህግና ስርዓት፣ ደንብና መመሪያ የሌለው የጦር ወይም የፖሊስ ኃይል፣ ያሻውን ነገር መፈፀም ስለሚችል፣ ለዜጐችና ለአገር እጅግ አደገኛ ይሆናል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡
ስርዓትና ደንብ ከሌለው፣ በዘፈቀደ የሚፈነጭና የሚንጋጋ ከሆነ፣ ወንጀልን የመግታትና ተዋግቶ የማሸነፍ ብቃት አይኖረውም፡፡ እንዲያውም፤ ድሮ ድሮ፣ የጦር ሠራዊት የሰልፍ ስርዓት ለትርዒት ብቻ አልነበረም፡፡ ውጊያውም በሰልፍ ነበር። “ቀስትህን አንሳ፣ አነጣጥር፣ ወርውር”…ውጊያው በጥብቅ ደንብና መመሪያ ነው፡፡ ዛሬም፣ ዋና ባህርይው አልተቀየረም፡፡ “የጦር ሃይል አሰላለፍ” የሚል አባባል፣ የውጊያ ዝግጅትና ስርዓትን ይገልፃል፡፡
ምናለፋችሁ! ህግና ስርዓት፣ ደንብና መመሪያ፣ የፖሊስም የጦር ሃይልም ዋና ባሕሪይ ነው፡፡
ከትክክለኛ አላማቸውና ከኃላፊነታቸው ውልፍት እንዳይሉ፣ ያገለግላል - ህግና ስርዓት፡፡
ኃላፊነታቸውን የመፈፀምና አላማቸውን የማሳካት የተሟላ ብቃት እንዲጐናፀፉም ያደርጋል - ህግና ስርዓት፡፡ ይሄ ውስጣዊ ምንነትና ባህርይ ነው፡፡
በዘፈቀደ መፈንጨትም ሆነ መፍዘዝ የለም፡፡
ከመንገዱ ውልፊት ሳይል በስርዓት ይራመዳል፡፡
ከመስመር ሳይወጣ፣ ግራ ቀኝ ሳይዛባ፣ ቅደም ተከተልን አሟልቶ፣ ፍጥነቱንና ልኩን ጠብቆ፣ ከመነሻ ወደ መድረሻው፣ በብቃት ይራመዳል፡፡
ይሄ የመንታ ገጽታ ትርጉም አለው፡፡
አንድም፣ ወታደራዊ ሰልፍ ወይም ስርዒት ነው፡፡ ሁለትም፣ የፖሊስና የወታደር መደበኛ ሥራም ነው፡፡ ውስጣዊው አላማና ውጫዊው ገጽታ እንዲህ ተጣጥመው መዋሃድ ይገባቸዋል በህግና ስርዓት መስራት፣ እንዲሁም በህግና ስርዓት መራመድ፡፡


Read 7895 times