Sunday, 18 October 2020 00:00

የኮርማዎች ውጊያ - አራት ወጎች

Written by  ተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(1 Vote)

  ዛሬ ስለ በሬዎች ውጊያ ነው የማወጋችሁ። (መቼም ስለ አሰቃቂው የሰዎች ውጊያ ከማውራት ይሻላል) ዘና እንደምትሉበት እምነቴ ነው፡፡
ወግ-1. መቼም የገጠር ልጆች የምታውቁት ታሪክ ነው - ኮርማ በሬዎች እርስበርስ የመዋጋት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ ሁለት ኮርማዎች ጎን ለጎን ከቆሙ ወይም ከተቀራረቡ ከሁለቱ በጉልበት በላጩ ማን እንደሆነ ሳይለይ በሰላም አይቆዩም። ገና እንደተያዩ “አሁን እኔና አንተ ብንዋጋ ማን ያሸንፋል?  ... እንዋጋና ይዋጣልን ወይስ እንደማሸንፍህ ታምናለህ?” የሚባባሉ ነው የሚመስለው።  “አሁን ምን ያጣላናል? ምንስ ጉልበታችንን ያፈታትሸናል?” ብለው ራሳቸውን አይጠይቁም። (እንኳን እነሱ የሰው ልጅስ መች ይጠይቃል!)
የሚገናኙበት ቦታ የግጦሽ መስክ፣  የእርሻ ማሳ፣ ክትባት መውሰጃ፣ ውሃ መጠጫ፣ የጤፍ ውቂያ አውድማ፣ ገበያ (ሰንጋ ተራ)፤ ሌላ ቀርቶ ወደ ቄራ የተጫኑበት መኪና፤ ሊሆን ይችላል። ሁሌም፤ “ማን ያሸንፋል?” ይባባላሉ። ስፍራ ቢጠባቸው እንኳ ይጎሻሸማሉ። እርግጥ ነው፤ አልፎ አልፎ ፍፁም ሰላማዊ የሆኑ፣ ውጊያም ሆነ ልፊያ የማይማርካቸው በሬዎችም ይገኛሉ።
አዲስ አበባ ውስጥ፤ በርካታ ሰዎች ባሉበት (ለምሳሌ፤ ለቅሶ ቤት) ይህን ትዝብቴን ሳወራ ወንዶች ምንም አይመስላቸውም። ምክንያቱም ሁሉም በልጅነታቸው፤ ሁለትም ሆኑ ሶስት፤ የየቡድናቸው ዓለቃ ለመሆን በየቀኑ “ይዋጣልን” ሲባባሉ፣ ቆመው ሲደባደቡ፣ ታግለው መሬት ላይ ሲንደባለሉ ይውሉ እንደነበር ያስታውሳሉ። እኔም አልፌበታለሁ፡፡ ሴቶች ግን አልገባ ብሏቸው በመገረም ይጠይቁኛል። “እንዴ!? ከመሬት ተነስቶ ... መዋጋት (መጣላት) ለምን አስፈለጋቸው?” ይሉኛል። “የወንዶች ዓለም እንዲያ ነው” እላቸዋለሁ። ይገረማሉ።
ወግ-2. “ሰላማዊ” በሬዎችን እርስበርስ ማዋጊያ ቀላል ዘዴ አለ፡፡ የመዋጋት ሀሳብ ያልነበራቸው፤ ምናልባትም የማይተዋወቁ ኮርማ በሬዎችን ለማዋጋት ይቻላል። ዘዴው፤ በአካል ተመጣጣኝ የሆኑ በሬዎችን፤ ይበልጡንም የየቡድኖችን ንጉሦች፤ ከያሉበት እየነዱ አምጥቶ ማቀራረብ ነው - አለቀ!  
ለውጊያ የሚታሰቡት በሬዎች ተነድተው የሚመጡት ከየራሳቸው ወገኖች ጋር መስክ ላይ በሰላም ከተኙበት ወይም ግጦሽ ላይ ከነበሩበት ሊሆን ይችላል።  
በሬዎቹ፤ መጀመሪያ ላይ ከዘመዶቻቸው መካከል ተነድተው ሲወጡ በእንቢተኝነት አንገታቸውን ቆልምመው ወደ መጡበት ለመመለስ ይሞክራሉ፤ ወዴት እንደሚሄዱ አያውቁምና። ነገር ግን የአንድ በሬ እምቢ ባይነት የሚቆየው እንደሱ ከወዲያኛው ቡድን እየተነዳ የሚመጣው በሬ ከርቀት አይቶት እስኪያገሳ ድረስ ነው። ያኛው ካገሳ፣ ይህኛውም በማግሳት ምላሽ ይሰጣል። ዘዴው ያለው እዚህ ላይ ነው፤ አንዱ ያንዱን የፉከራ ድምጽ እንዲሰማ ማድረግ። ከዚያ ማጠጋጋት። ድምጽ እንዲሰማሙ ማድረግ።
በሬዎቹ ሲጠጋጉና የሁለቱም ፉከራ ሲቀጥል፤ ሁለቱም እውነትም ወራሪ የመጣባቸው፣ የተደፈሩ ይመስላቸዋል። ራሳቸውን ለመከላከል ብሎም ለማጥቃት ይዘጋጃሉ። ከዚያ፤ ነጂ ሳያስፈልጋቸው ተቀራርበው ውጊያ ይገጥማሉ። የውጊያው ባለቤትም ራሳቸው ይሆናሉ። የገቡበትን ውጊያ ለማቆም ቢያስቡ ራሱ አይችሉም፤ ምክንያቱም “እኔ ባቆም እሱ ይወጋኛል” በሚል ይፈራራሉ። በዚያ ላይ በተዋጉበት ጊዜ ውስጥ እርስበርስ መጎዳዳታቸው ስለማይቀር የማሸነፍ፣ ጥቃትን የመመለስ (የመበቀል) ፍላጎትና እልህ ይኖራቸዋል። በተዋጉ፣ በደሙና በቆሰሉ ቁጥርም ለመዋጋት በቂ ምክንያቶችን እያገኙ ይመጣሉ።
ውጊያው አድካሚ ከመሆኑ የተነሳ ጫንቃ ለጫንቃ ተደጋግፈው ለደቂቃዎች ሊቆዩ ይችላሉ። አዋጊዎቹ መደሰት ካለባቸው የበሬዎች እንደዚያ መሆን ግድ ነው።
ወግ-3. ኮርማ በሬዎችን ማዋጋት ግድ ሆኖ ከተገኘ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች አሉ። በአካል ግዙፍ የሆኑ ኮርማ በሬዎች ውጊያ ብዙ ውበቶች ያሉት ትዕይንት ነው። ለዚህም ነው ከልጅ እስከ አዋቂ ከብቦ የሚመለከታቸው። አንድ ህፃን ልጅ፤ ከሰሌዳ ላይ ፊደል መጠቆሚያ በሚያህል ጭራሮ ጀርባውን እየመታ፤  ሲለው ደገፍ ብሎት ጭራውን እየቆለመመ፤ ጠጠር እየወረወረ፣ የሚነዳው በሬ፤ ባላጋራውን ኮርማ በሬ በአንድ ቀንዱ ብቻ ከመሬት ሰቅስቆ አንስቶ ቀጥ አድርጎ ሲያቆመው መመልከት ያስደንቃል። የበሬዎችን አቅም ብቻ ሳይሆን የውጊያ ቴክኒካቸውን ማስተዋልም ያስደስታል። ሲዋጉ የሚሰማው ድምጽ ራሱ አስገራሚ ነው - ኳ! ጓ! ግም! ዱፍ!
ይህን ውብ ትዕይንት ለመመልከት፤ በተጨማሪም እየተወራረዱ፣ እየተበሻሸቁ ለመዝናናትም ነው ሰዎች ማዋጋቱን የሚወዱት - ይብላኝ በማያውቁት “ምክንያት” ለሚፈጣፈጡት ምስኪኖች!
አዋቂዎች፤ በሬዎች የሚዋጉበት ቦታ በሬዎችን ለአደጋ የማያጋልጣቸው - ሜዳማ፣ ድንጋይ፣ የአፈር ጓል፣ ጋሬጣ ያልበዛበት፣ ወደ ገደል አፋፍ ያልተጠጋ - መሆኑን በቅድሚያ ያጣራሉ። በዚያ ላይ በሬዎቹ ከተሸናነፉ በኋላ “ነገም” በድጋሚ ሊጋጠሙ እንደሚችሉ ስለሚያስቡ፣ የማይመች ሁኔታ ካለ ግጥሚያውን ታግሰው ለማሳደር ይችላሉ። ልጆች ግን የሚታያቸው ጊዜያዊ ደስታቸው ብቻ ነው። ሌላ ቀርቶ፤ ለራሳቸውም ደህንነት አይሰጉም። ተሸንፎ የሚሮጥ ኮርማ “አይን የለውም” - ሊዳምጣቸውም ይችላል፡፡
የገጠር ልጆች፤ የበሬዎች ውጊያ ትዕይንት “አክሽን ፊልማችን” ነበር። የምናወራላቸው ኮከብ ተዋናዮቻችን (ስታሮች) ደግሞ በሬዎቻችን ነበሩ።
ወግ- 4. በማን ግዛት ማን ያገሳል? መዘዘኛው የሁለት በሬዎች ውጊያ - እውነተኛ ታሪክ ይኸውላችሁ፡-
አንድ ምሽት ላይ እንዲህ ሆነ።  አቶ ባያብል ደስታ የሚባሉ ሰውዬ ሰፈራቸው ውስጥ ካለ ጠጅ ቤት ቁጭ ብለው እየጠጡ ነው። በድንገት፤ የመንደርተኛቸው የአቶ ብርሃኔ ተመስገን ኮርማ በሬ (ማኅተቤ ይባላል) አገሳ። እሱን ተከትሎ የአቶ ባያብል በሬ (“አባት” ይባላል) አገሳ። በሬዎቹ ምላሽ ተሰጣጡ፡፡ ተኩስ ተለዋወጡ እንደ ማለት በሉት፡፡
አንድ ይህን ሁኔታ የታዘበ ሰው በመገረም፤ “አቶ ባያብል፤ የአቶ ብርሃኔ በሬ ሲያገሳ የእርስዎ በሬ ያገሳል። ትርጉሙ ምንድን ነው?” አላቸው።
“ዝም በል፤ አፍህን ያዝ" ብሎ መልስ እየሰጠው ነው” ብለው መለሱ፤ አቶ ባያብል። “ንጉሡ የኔ በሬ ነው፤ ነገር ፍለጋ ካልሆነ ለምን ያገሳል? ... አይነጋ መስሎት ነው?”
ሰውየው ሌላም ጥያቄ አቀረበላቸው። "የእርስዎ በሬና የአቶ ብርሃኔ በሬ ቢጋጠሙ የትኛው የሚያሸንፍ ይመስልዎታል?”  
አቶ ባያብል ቆጣ ብለው መለሱ፤ “የኔ በሬ፤ አባት ነዋ!” አሉ ኮራ ብለው። "አባት ጨዬ በረሃ ገደል ውስጥ ይከተዋል” በእርግጠኝነት ተናገሩ።
ይህ ወሬ ከአቶ ብርሃኔ ጆሮ ደረሰ። ሰውየው በቁጣና በንዴት ተንቀጠቀጡ አሉ። ሳይውሉ ሳያድሩ፤ ቃላቸውን በፊርማቸው ያፀኑበትን ደብዳቤ ጽፈው ለአቶ ባያብል ላኩላቸው።
መልዕክቱ የሚለው እንዲህ ነው፤ “ያልከውን ሰምቻለሁ። ያንተ በሬና የኔ በሬ በሽማግሌ ፊት ጨዬ በረሃ ላይ ይጋጠሙ። ያንተ በሬ ካሸነፈ የወርቅ ሀብል አንገቱ ላይ አደርግለታለሁ።”
አቶ ባያብል የአቶ ብርሃኔን ደብዳቤ አንብበው እንዳበቁ፣ አጭር ምላሽ ያሰፈሩበትን ደብዳቤ ላኩላቸው። “እኔ ደግሞ ያንተ በሬ ካሸነፈ፤ ቤልጅግ ጠመንጃዬን አንገቱ ላይ አንጠለጥልለታለሁ” ብለው ቃላቸውን አፀኑ።
ነገሩ የምር ሆነ። የአገር ሽማግሌዎች ተሰየሙ። ተወራራጆቹ ለቃላቸው ማስከበሪያ ወርቅና ጥሬ ብር አስያዙ።  
በርካታ ወጣቶች፣ አዋቂዎችና አዛውንቶች በተመልካችነት በታደሙበት ሁለቱ በሬዎች ይዋጉ ዘንድ እየተነዱ እንዲጠጋጉ ተደረጉ። አባትና መኅተቤ፤ ቀደም ሲልም ይተዋወቁ ነበርና፤ ብዙም ሳይፎክሩ ውጊያ ገጠሙ።
ውጊያው ሶስት ቀናትን ፈጀ።  ይህም የሆነው በሬዎቹ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ እንዲጋጠሙና ከምሽቱ አንድ ሰዓት ሲሆን በሰዎች አማካይነት እንዲገላገሉ እየተደረገ ነበር።
በሶስተኛው ቀን ማብቂያ ላይ የሁለቱ በሬዎች ውጊያ ተፈጸመ። የአቶ ባያብል በሬ የአቶ ብርሃኔን በሬ አሽቀንጥሮ ከገደል ከተተው - ሰውየው እንዳሉት።
ሽማግሌዎች ውርርዱን መደምደም ነበረባቸው። የአቶ ባያብል በሬ ቃል የተገባውን የወርቅ ሀብል ተሸለመ። ባለቤቱ አቶ ባያብል ደግሞ ፎክረውና አቅራርተው ሲያበቁ፤ በሬያቸው ስላላሳፈራቸው፤ ይልቁንም ስላኮራቸው፤ ተጨማሪ ሽልማት አደረጉለት። ማምሻውንም ቤተዘመድና የኩነቱ ታዳሚዎች የደስደስ ጠጡ። የበሬዎችን ውሎ የሚመለከቱ ወጎችን ተለዋወጡ።
የሁለቱ በሬዎች ውጊያ ታሪክ በዚህ አያበቃም፤ ብዙ አስደሳችና አሳዛኝ ነገሮች በሁለቱ ሰዎች ቤተሰቦች መካከል ተከስተዋል። ባለበሬዎቹ፤ ከመጠነኛ መቀያየም በኋላ የጋብቻ ዝምድና መስርተዋልም ይባላል። ታሪኩን ያጫወቱኝ ሰው በህይወት አሉ። ቦታው ምሥራቅ ጎጃም ነው፤ ጉንደወይን ወረዳ፤ 012 ቀበሌ፡፡
እና፤ እንደነገርኳችሁ ነው፡፡ በሬዎችን ለማዋጋት ቀላል ነው - ማጠጋጋት፣ ድምጽ ለድምጽ እንዲሰማሙ ማድረግ፣ ከዚያ ሲፈሳፈሱ መመልከት፡፡ መዝናናት፡፡ በእነሱ ውጊያ መደሰት፡፡ ጊዜን ማሳለፍ፡፡ ብዙ ነገራችን እንዲሁ ነው፡፡
የነገ ሰው ይበለን!!

Read 3416 times