Print this page
Monday, 19 October 2020 00:00

ጃንሜዳ - ከአድዋ ድል እስከ አትክልት ተራ (1888-2012)

Written by  ይትባረክ ዋለልኝ
Rate this item
(0 votes)

 ሕዝባዊ ቦታዎች የአንድን ማህበረሰብ ማህበራዊ ህይወትን የሚያሳዩ በህዝቡ የሚከበሩና የሚወደዱ ቦታዎች ናቸው። በእነዚህም ህዝባዊ ቦታዎችም አማካኝነት ሕብረተሰቡ ስብሰባዎችን እርቆችን ሐይማኖታዊ ከበራዎችን ፖለቲካዊ ሁነቶችን ስፖርታዊና የመዝናኛ ክንዋኔዎችን ወዘተ ይከውኑበታል። ህዝባዊ ቦታዎች ለህብረተሰቡም የላቀ አካላዊና መንፈሳዊ እርካታን ስለሚሰጡ እጅግ የሚከበሩ የሚወደዱና የሚዘወተሩ ቦታዎች ናቸው። በሐገራችን ውስጥ በሕዝብ ዘንድ የሚከበሩ የሚወደዱና የሚዘወተሩ  ህዝባዊ ቦታዎች አሉ። ከነዚህ ህዝባዊ ቦታዎች (Urban Public space) መካከል በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኝው ጃንሜዳ አንዱና ብቸኛው ነው።
ጃንሜዳ ስያሜውን በ 1895 ዓ.ም ያግኝ አንጂ ከአዲስ አበባ ምስረታ በኋላ ባሉት ጥቂት አመታት ጀምሮ ሕዝባዊ ቦታ በመሆን ለከታማው ነዋሪ አገልግሎት እየሰጠ ዛሬ ድረስ ዘልቋላ። እኔም በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ለናቱ ስለሆነው ሕዝባዊ ቦታ “ጃንሜዳ” ታሪካዊ ፖለቲካዊ ሐይማኖታዊ ስፖርታዊ ኪነጥበባዊ ባህላዊና ሕዝባዊ ክንውኖችን  ሁነቶች ላይ በመንተራስ ለአመታት ከቃረምኩትና በመጽሐፍ ለመደጎስ ካሰናዳሁት ጽሁፍ እየቆነጠርኩ ታሪኩን ለአንባቢያን እንዲመች አድርጌ በተከታታይ ለማካፈል ወደድኩ። እነሆ!
የሕዝባዊ ቦታና - ጃንሜዳ
ስለ ኢትዮጵያሕዝባዊ ቦታ (public place) ጥናት ካደረጉ የፎክሎር ባለሙያዎች መካከል የባህርዳር ዩንቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን ተሾመ አንዱ ናቸው። “ፎክሎር”በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ስለ ሕዝባዊ ቦታ (public place)  ምንነት እንዲህ ይሉናል፤” አንድ ማህበረሰብ በሚኖርበት አካባቢ ውስጥ ያለና ልዩ ማህበራዊ ዋጋ የሚሰጠው የሃገረሰባዊ ውክልና ዘርፍ። በማህበረሰቡ ባህል መሰረት የተለያዩ ሐይማኖታዊና ማህበራዊ ስርዓቶች የሚከወንባቸው እንዲሁም ታሪካዊ ድርጊቶች የተፈጸመባቸው ሕዝባዊ ቦታዎች ልዩ ክብር ይሰጣቸዋል። በመሆኑም እንደነዚህ አይነት ቦታዎች በአካባቢው ካሉ ሌሎች ቦታዎች በተለየ መልኩ የማህበረሰቡን ባህል እምነት ፍልስፍና ወዘተ ይገልጻሉ። “ህዝባዊ ቦታዎች በተለያየ የምህንደስና ጥበብ የተገነቡ (ቤተ ክርስቲያን ገዳም መስጊድ ቤተመንግስት ሐውልት የመቃብር ስፍራ የንግስ ቦታዎች) ወይም ምንም አይነት ምህንድስና የሌለባቸው (የገበያ ስፍራዎች የሽምግልና ስርዓት የሚካሄድበት ቦታ ጦርነት የተካሔደበት ሥፍራ በዓለ ታቦት የሚወጡበት የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች የሚካሄዱበት ቦታ ነው።” ይሉናል፡፡
“......... በአዲስ አበባ ከተማም ታዋቂ ከሆኑ ሕዝባዊ ቦታዎች መካከል ጃንሜዳና መስቀል አደባባይ እንደሚጠቀሱ ያሰፍራሉ - መምህሩ።
የጃንሜዳ መቼና በማን
ጃንሜዳ እንደ ሌሎቹ ጥንታዊና ቀደምት ዘመናዊ ሐገሮች ውስጥ እንደሚገኙት ታሪካዊና ህዝባዊ ቦታዎች ሁሉ ከአንድ መቶ አመት በላይ ብዙ ህዝባዊ ክንውኖችን ያስተናገደ ቀደምትና ታሪካዊ ሕዝባዊ ቦታ ነው። ስለ ጃንሜዳ ትርጓሜ ደስታ ተክለወልድ በአማርኛ መዝገበ ቃላታቸው ውስጥ እንዲህ አስቀምጠውታል፡-
ጃን፡ሜዳ፡- ትልቅና ሰፊ ሜዳ
ጃንሜዳ (ሜዳ፡ጃን)፡- የንጉስ ሜዳ ንጉሱ፣ የጦር ሰራዊት ሰልፍ የሚያሳይበት ከባለሙአሎቹ ጋር ጉግስ የሚጫወትበት ሜዳ፡ በጎንደርና በአዲስ አበባ ይገኛል።ከ1933 ወዲህ ግን አዲስ አበቦች ጃንሆይ ሜዳ ይሉታል፣ ስህተት ነው።ጃንሆይ የቅርብ ስሚ ነውና ዘርፍ አይሆንም።”
ስለ ጃንሜዳ ስያሜና ለምን ዓላማ  ታስቦ አንደተቋቋመ ብሎም የሜዳውን የስፋት መጠን በተመለከተ የታሪክ ምሁሩ ስርግው ሀብተስላሴ ደግሞ  “ምኒልክ የአዲሱ ስልጣኔ መስራች” በሚለው መጽሐፋቸው ሲገልፁ፡-
“በአዲስ አበባ በሁለተኛውና በሶስተኛው ክልል መካከል በስተሰሜን በኩል ለሕዝብ መሰብሰቢያ፡መዝናኛና የስፖርት ማዝወተሪያ እንዲሆን ታስቦ የተንጣለለ ሜዳ፣ ወደ 800,000 (ስምንት መቶ ሺህ) ሜትር ካሬ ስፋት ያለው ተከልሎአል።
ሜዳውን ‘ጃንሜዳ’ ተብሎ እንዲጠራ የሰየሙት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ናቸው። እንዲሁም በጃንሜዳ ግዙፍ ህዝባዊ ስብሰባ የተደረገው የአደዋ ሰባተኛ ዓመት የድል በዓል ላይ ነው።”
በጃንሜዳ ላይ ጥናት ካደረጉ ሌሎች ባለሙያዎች መካከል ደረሰ ጌታቸው አንዱ ነው። ደረሰ በ “12th Biennial International Conference” ላይ ያቀረበው ጽሁፍ ተጠቃሽ ነው።
“A tragedy of the Urban Commons?in case of two public Space in Addis Ababa” በሚለው  የጥናት ጹሁፉ ውስጥ ጃንሜዳ እንዲህ ገልጾታል፡-
“Jan Meda has been Playing role in the modern history of Ethiopia staging religious festivals, coronation, military reviews and campaign inaugurals. Moreover, Jan Meda has also served and still serving as the play ground for various sports activities ranging from horse racing to athletics field events. Jan Meda has also served as aplace of refuge and temporary settlement in times of crisis and transitions”
(Derese Gatacew kassa 2008)
በአጠቃላይ ጃንሜዳ በብዙ ታሪካዊ ሐይማኖታዊ ፖለቲካዊ ማህበራዊ ጉዳዮች  ብሎም ታሪካዊ የሆኑ  የስፖርትና፡የኪነጥበብ ተግባራት የተከወኑበት የሚከናወኑበት ህዝባዊ ቦታ ነው። ጃንሜዳ ከትላንት እስከ ዛሬ ድረስ ቀለም ዘር ብሔር ጎሳ ወዘተ ሳይመርጥ  የአዲስ አበባን ነዋሪና ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ክንዋኔዎች ከሰባቱም አሕጉር የሚመጡትን ሁሉ በፍቅር የሚቀበልና የሚያስተናገድ የሚያገናኝ ህዝባዊ ቦታ ነው።
ጃንሜዳ ኢትዮጵያዊነትን ያስተሳሰረ ህዝባዊ ቦታ
ጃንሜዳ ከአዲስ አበባ መመስረት ጀምሮ የተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶችን ያስተናገደ ህዝባዊ ቦታ ነው።በተለይ  ከአደዋ ድል ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን የነጻነትን ድል ያበሰሩበት ያጣጣሙበት ብሎም ድላቸውን በአንድነት ያከበሩበት ታላቅ ህዝባዊ ቦታ ነው። ጃንሜዳ ከ1888 ዓም ጀምሮ ህዝባዊ ቦታ በመሆን አያገለገለ ይገኛል። ጃንሜዳ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ሐይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ዘመናዊ ስፖርቶችና የኪነጥበብ ትዕይንቶች የተለያዩ ሁነቶች የሚስተናገዱበት ህዝባዊ ቦታ በመሆን ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያገለገለ ሥፍራ ነው። በጃንሜዳ የአደዋ ድል የተበሰረበትና ከ 7 ዓመት በኋላም ድሉ በድምቀት የተከበረበት ቦታ ነው።  ዳግማዊ ምኒልክ አቤቶ እያሱ ወራሽ መሆኑ አዋጅ ለህዝብ የተነበበት ቦታ ነው።ጃንሜዳ በማህል ሰፋሪ የፖለቲካ ዱለታ እያሱን ወደ ስልጣን በማምጣትና ጣይቱን ከስልጣን ገሸሽ ያደረገ ቦታ ነው።  እያሱንም ከስልጣን በማውረድና ዘውዲቱን ወደ ስልጣን በማምጣት፡ የንግስ ስርዓት የተከናወነበት እንዲሁም ኮሮኔል መንግስቱ ሐይለማሪያም ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ የታዩበትና ደርግ ሶሻሊዝምን ይፋ ያደረገበት ቦታ ነው። የዘመኑ ተራማጅ ምሁራንን፣ ተማሪዎችንና መምህራንን ለዕድገት በህብረት ዘመቻ በአንድ ላይ በማሰባሰብ አስተዋጽኦው ቀላል አይደለም፡፡ ጃንሜዳ ባለ ውለታ ነው። ከሰገሌ ጦርነት በኋላ የንጉስ ሚካኤልን ሽንፈት በአደባባይ ለሕዝብ ያሳየበት ቦታ ነው። በስፖርቱም ረገድ ዛሬ የአገራችንን ሰንደቅ አላማ በአለም የስፖርት መድረክ ላይ ከፍ ያደረጉ እንቁ አትሌቶች ከጃንሜዳ ጋር ጥብቅ  ታሪካዊ ትስስር አላቸው። ጃንሜዳ የፈረስ ጉግስ፣ የገና ጨዋታን፣ የመስቀል እንዲሁም የጥምቀትን በዓል በማክበር ኢትዮጵያዊያንን በማቀራረብና ወንድማማችነት በማጠንከር  በአለም መድረክ ላይ ክንውኖቹ እንዲታወቁ በማድረግ ባለውለታ ነው። በኢኮኖሚ መስክ ደግሞ ዛሬ የገበያ ቦታ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡
የዓደዋድልና ጃንሜዳ
ዓደዋ  የኢትዮጵያዊያን ታላቁ የድል ታሪክ ምዕራፍ ነው።በአራቱም አቅጣጫ ያሉ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ለአንድ አላማ ያሰባሰበ፡የድል ሸማ ያላበሰ፡ ታሪካዊ የነፃነት አርማ ነው። የኢትዮጵያዊያን በአንድነት ላይ የተመሰረተ የተጋድሎ ታሪክ ነው። ዓድዋ ኢትዮጵያዊያንን ለነጻነት በተከፈለ መሰዋእትነት በደም ያስተሳሰረ፤ የኢትዮጵያዊያንን ነጻነት፣ አንድነትና ወንድማማችነት የተረጋገጠበት ማህተምና የማዕዘን ድንጋይ  ነው።
“ለንጉሰ ነገስቱ ነጻነትና የአገር ድንበርን የማስከበር ጥሪ ጦር ያልላከ የአገሪቱ ክፍል አልነበረም።......... በትልቅ የአገር ፍቅር ስሜት ይዋጋ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር በስልትና በቅንጅትም ከጠላት ልቆ በመገኝቱ ምንም እንኳን ብዙ ሰው ቢያልቅም በጠላት ላይ የማያወላውል ድል ተቀዳጀ።” (ባህሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1887-1983)
ጃንሜዳ ከዓደዋ ታሪካዊ ድል ጋርጥብቅ ግንኙነት አለው። ጃንሜዳ ከአደዋ ድል ማግስት ጀምሮኢትዮጵያዊያንን በፖለቲካ በሐይማኖት፡ በማህበራዊ ጉዳዮች በስፖርት በኪነጥበብ ወዘተ በማሰባሰብ ታሪካዊ ተግባራት የተከናወነበት ታላቅ ታሪካዊና ህዝባዊ ቦታነው። ጃንሜዳ  ከዓደዋ ድል ጋር ጥብቅ ትስስር አለው። ይኸውም አንደኛው ኢትዮጵያዊያን  ወራሪውን ጣልያንን አደዋ ላይ ድል ካደረጉ በኋላ ንጉስ ምኒልክ ከበርካታ ወታደሮችና የጦር መሪዎች ጋር አዲስ አበባ ሲደርሱ ድሉን ከህዝቡ ጋር በድምቀት ያከበሩበት ታሪካዊ ቦታ ነው። ሁለተኛው ከመላው ኢትዮጵያ የመጡ ህዝቦችናከሶስት መቶ ሺህ በላይ የሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች የተሳተፉበት እንዲሁም ከአውሮፓና ከእስያ የመጡ ተጓዦችና በአዲስ አበባ የሚገኙ ዲፕሎማቶች በተገኙበት  በታደሙበት የአደዋ ድል 7ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል የተከበረበት ታሪካዊ ቦታ  ነው።እነዚህ ሁለት ታላላቅ የአደዋ ድል ክብረ በዓሎች በጃንሜዳ ላይ ሲከናወኑ የነበረውን ሁኔታ በተመለከተ ከታሪክ ጸሐፊያን መዝገብ ላይ ያገኝሁትን መረጃ እነሆ።
የአደዋ ድል አከባበር በጃንሜዳ
የንጉሱ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዜና መዋል ጸሐፊ የሆኑት  ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ከአደዋ ጦርነት ማብቃት በኋላ ግንቦት 15 የአድዋ ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቆ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ከመቀሌ ተጉዘው አዲስ አበባ ሲገቡ፣ በጃንሜዳ ላይ የነበረውን ሁኔታ ሲገልፁ፤
“አጼ ምኒልክም ተእንኪጨው ተመልሰው መቀሌ ሲደርሱንጉስ ተክለሐይማኖትን ተሰናብተው በሳሬም በኩል ወደ ጎጃም ሄዱ። ንጉሰ ነገስቱም ወደ ሸዋ ሲጓዙ የማይጨው አቡነ ተክለሐይማኖት ብዙ መሬት ብዙ ላምና በሬ ሰጥተው፤ ዳሩ እሳት መካከሉ ገነት ይሁን ብለው ደብረ ዳሞ አደረጉት።ይህም የሆነበት ምክንያት ፊት ወደ አደዋ ሲዘምቱ ከዚያ ሰፍረው ሳሉ የፈረስና የበቅሎ በሽታ ገብቶ ይፈጅ ነበር።የማይጨው አቡነ ተክለሐይማኖት ተስለው ጠበሉንም ለከብቱ ቢያጠጡት በሸታው ለቀቀ። ስለዚህ ገዳም አደረጉት። ቤተክርስቲያኑንም አሰርተው ብዙ መጽሐፍት ሰጥተው መምህራንና መዘምራን ሰርተው፣ ጉባኤ የሚነገርበት ታላቅ ደብር ሆነ።
አጼም ከአደዋ ዘመቻ ሲመለሱ ሲዘምቱ በሄዱበት መንገድ እየተጓዙ በየሐገሩ በየመሳፈሪያው ድግስ እንዲደገስ ታዞ ነበርና በየሰፈሩበት ሰራዊቱን ግበር እያበሉ እያጠጡ፣ በግንቦት 15 ቀን አዲስ አበባ ከተማዋ ገቡ።ከጣሊያንም የተማረከው መድፍ አስቀድሞ ተጉዞ ነበርና ሁሉም ከሰፊሜዳ (ጃንሜዳ) ተሰልፎ ቆይቶ ነበር።
   በዚያን ቀን የመድፍ ግባት ተተኮሰ።የአዲስ አበባም ካህናትም የአምስቱም ደብር ከሰፊው ሜዳ ላይ ቆይተው “ ወምድረኒ ትገብር ፋሲካ ተሐጺባ በደመ ኢጣልያ” እያሉ ተቀበሉ። አደዋ በጣልያ ጦርነት ስለ ሞቱት መኳንንትና ሰራዊት ምንም መዋዕለ ሃዘን ቢሆንም መንግስቱም ስለቆመ አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱም በደህና ስለመግባታቸው ፍጹም ደስታ ሆነ።የተማረከውም ኢጣልያ ሁሉ በሃገሩ ምሪት ገብቶ ከረመ።”
(ጸሐፊ ትእዛዘ ገብረስላሴ 207-210)

Read 1693 times