Friday, 23 October 2020 14:45

ደንብ አስከባሪው

Written by  ድርሰት - አንቶን ቼ ኾቭ ትርጉም - ዮናስ
Rate this item
(4 votes)

 "ጓድ ብሬሽቤቭ! የቀረበብዎት ክስ መስከረም 3 ቀን የፖሊስ አባል የሆኑትን ጓድ ዚጂን ጨምሮ የተወደዱና የተከበሩ ያገር ሽማግሌ አልያፓቭ፣ የሰላም አስከባሪው ኦቦ ኤፊሞቭ፣ በምስክርነት በቀረቡት ኢቫኖቭ እና ጋቭሪሎቭ እንዲሁም ሌሎች ስድስት የመንደሩ ነዋሪዎች ላይ ያልተገባ ዘለፋ፤ ከዚያም አልፎ ጉልበት ሁሉ ተጠቅመዋል የሚል ነው፡፡ ክፉኛ ካመነጫጨቋቸውና ከገፈታተሯቸው ግለሰቦች መካከል ስማቸው ከላይ የተጠቀሰው የመጀመሪያዎቹ ሶስት ግለሰቦች ደሞ በእለቱ ግዴታቸውን እየተወጡ የነበሩ ደንብ አስከባሪዎች ናቸው። በእርስዎ በኩል በዚህ ላይ የሚሉት ነገር አለ?"
በገዛ ፍቃዳቸው እራሳቸውን ደንብ አስከባሪ አድርገው የሾሙትና ያለ ክፍያ እያገለገሉ ያሉት ጓድ ሚሊሻ ሳጂን ብሪሽቤቭ፤ የችሎቱን ታዳሚዎች “እንዴት ብትደፍሩኝ ነው እንደዚህ የምትሉኝ?” በሚል አይነት ስሜት እያይዋቸው ጭንቅላታቸውን ሲነቀንቁ  ቆዩና፣ ድምጻቸውን ኮምጨጭ አድርገው፣ ሁኔታውን ልክ እዚያው ግርግሩ ውስጥ እንዳሉ አድርገው በዝርዝር  ይዘግቡ፣ ያስረዱ ጀመር።
“የሰላሙ ዳኛ - ክቡር ሆይ! በማናቸውም አይነት ሁኔታ ቢሆን ፍርድ ቤቱ የሚቀርቡለትን ማስረጃዎችም  ሆኑ ምስክሮች ለሁለቱም ወገን እንደሚሆኑ በሚዛናዊነት መታየትና መወሰድ እንዳለባቸው ህጉ ይደነግጋል፡፡ እና በዚህ ጉዳይ ጥፋተኛው እኔ ሳልሆን እንደውም እራሳቸው በኔ ላይ የተነሱት ናቸው ተጠያቂዎቹ፡፡  
"ይሄ ሁሉ የመጣው  ነፍሱን ይማረውና፣ ሞቶ በተገኘው ሰውዬ ነው፡፡ ወሩ በገባ ሶስተኛው ቀን ላይ ነው፤ እኔና ባለቤቴ አንፊሳ እንደተለመደው ማንም ላይ ሳንደርስ በጨዋ ደንብ ብርድ ማጥፊያዋን እየተጎነጨን ነበር ድንገት ማዶ ከውሀ ዳር የሆነ ግርግር ያየሁት። ምንድን ነው እንደዚህ የሚያተረማምሳቸው? ሲጀመር ህጉ እንደዚህ መሰባሰብ ትችላላችሁ አይልም። በመንጋ እየተሰባሰቡ ግርግር መፍጠር የሚቻል መሰላቸው እንዴ? ብዬ እየተምዘገዘኩ ሄድኩላቸዋ!
"እዚህ ጋ ምንድን ነው ተሰብስባችሁ ሁከት የምትፈጥሩት? ሁላችሁም በፍጥነት ከዚህ ጋር ተበተኑ! ብዬ ብጮህባቸውም እንደ መንቀሳቀስ ጭራሽ ተገትረው ሲያዩኝ ጊዜ ነዋ በሽቄ የገፈታተርኳቸው፡፡ በዚያ ሁኔታ ነው ሁሉም ወደየቤቱ እንዲበተን ያስጠነቀቅሁት እና አስፈላጊ ከሆነም ትንሽ ሾጥ እንዲያደርጋቸው ለደንብ አስከባሪው የነገርኩት።"
“ይሰሙኛል ጓድ! እርስዎ ያገር ሽማግሌም አይደሉ፣ ደንብ አስከባሪም አይደሉ፤ እና መጀመሪያውኑ ምን አግብትዎት ነው እንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ እጅዎን እያስገቡ ሰዎችን ግርግር አትፍጠሩ፣ ተበተኑ እያሉ ችግር የሚፈጥሩት?"
“አዎ! ምንም አያገባቸውም፣ ዝም ብለው በማይመለከታቸው ነገር ውስጥ እኮ ነው ጥልቅ የሚሉት!” ፍርድ ቤቱ ውስጥ የነበረው ሰው በአንድ ላይ ይንጫጫ ጀመር፡፡ “ምንም ሊያስኖሩን  እኮ አልቻሉም - ክቡር ዳኛ! ከወታደር ቤት ከተመለሱ ጊዜ ጀምሮ ይኸው አስራ አምስት አመት እንዲሁ በማያገባቸው እየገቡ፣ ሰውን በረባ ባልረባው ከመነዝነዝና ከማወክ ውጪ ሌላ ስራ የላቸውም፡፡ መድረሻ እኮ ነው ያሳጡን፡፡ በጣም በዛ፣ ከልክ አለፈ፤ ለእሳቸው ስንል ቀያችንን እንልቀቅ እንዴ?” ምሬቶች ከየአቅጣጫው ተወረወሩ።
"የተከበረው ፍርድ ቤት፤ እንግዲህ ነገሩ ይኸው እንደሰሙት ነው” በማለት ያገር ሽማግሌው አቦሆይ የችሎቱን አየር ያዝ አደረጉና ንግግራቸውን ቀጠሉ፤ “ያካባቢው ነዋሪ በሙሉ አንድ  ሳይቀር በሱ ያልተማረረ የለም፡፡ ሁሉ በሱ ላይ ስሞታ አቅራቢ ነው። እሱ እያለ ማንም ሰው ነፃ አየር መተንፈስ አልቻለም። ታቦት ለመሸኘትም ይሁን ለሰርግ አልያም ለሌሎች መሰል ማህበራዊ ጉዳዮች፣ ብቻ ሰው ትንሽ ሰብሰብ ብሎ ካየ፣ ሲበር መጥቶ “ምንድን ነው እንደዚህ መሰባሰብና ሁከት መፍጠር? ስርአት ያዙ እንጂ!" እያለ መጮኹ አይቀርም፡፡ የሚጫወቱ ህጻናት እንኳን አይቀሩትም፤ እየያዘ ጆሯቸውን ሲመዘልግ፡፡ በዚህ ብቻ ቢያበቃ ጥሩ፤ ማጋጣ  መሆን የለባቸውም በሚል ባለትዳር ሴቶችን እየተከታተለ መግቢያ፣ መውጫ ሲያሳጣቸውም ጥሩ አማች እኮ ነው የሚመስለው፡፡ መች ዕለት ደግሞ ጭራሽኑ በየቤቱ እየዞረ  ዘፈናችሁን አቁሙ፣ መብራትም አጥፉ ሲል ነበር፡፡”
“አቦሆይ! ግድ የለም አንድ ጊዜ ይቆዩማ! ያንን እንዲያስረዱ እድሉ ይሰጥዎታል። ለጊዜው ግን ጓድ ብሪሽቤቭ ይቀጥሉና የሚሉትን እንስማ።” በማለት ዳኛው ጣልቃ ገቡና ተራውን ለሳጅን አሳለፉላቸው፡፡
“አመሰግናለሁ ክብሩነትዎ!” አሉና ጀመሩ ሳጅን ብሪሽቤቭ፡፡ “ክቡር ዳኛ! ሰዎች ወሬ እያነፈነፉ እንዲያ ተግተልትለው ግርግር ሲፈጥሩ እንዲበተኑ ማድረግ የኔ ስራ እንዳልሆነ ሲገልጹ ከልብዎ ነው፡፡ ይሁን ግድ የለም፤ ደህና፡፡ ግና እንደዚህ ያሉ ነገሮች የሰውን ሰላም የሚያደፈርሱ እንደሆነ ይታመናል፡፡ እርስዎም ቢሆኑ  ሰዎች እንዲያ መረን እንዲወጡና ዋልጌ እንዲሆኑ መፍቀድ የለብዎትም ብዬ አምናለሁ፡፡ ሲቀጥል ደግሞ የትኛው ህግ ነው ሰዎች እንደዛ ነጻ መሆን ይችላሉ የሚለው? ይህ  በፍጹም  የማልቀበለው ነገር ነው፡፡ ከስር ከስር እየተከታተልኩ  እኔው ካላረምኳቸውና ካልገሰጽኳቸው፣ ሌላ ማን ሃይ ሊላቸው ኖሯል?
ስለ ህግና ስርአት ማንም እንደኔ የሚያውቅ የለም፤ በመላው መንደር ነው የምልዎ ክቡር ዳኛ፤ ዋልጌነት የሚያድጠውን መንጋ እንደምን ሰጥ ለጥ አድርጎ መስመር ማስያዝ እንደሚቻል ከኔ በላይ የሚያውቅ የለም፡፡ እናም የተከበሩ፤ ባጭሩ ምንም የማላውቀው ነገር እንደሌለ ነው የምነግርዎ፡፡ ዝም ብዬ ተራ ሰው እኮ አይደለሁም። ያለምንም ክፍያ በገዛ ፍቃዴ የማገለግል ደንብ አስከባሪ፣ በጡረታ የተገለልኩ የእሩብ አለቃ ሳጅን ነኝ! የመጀመሪያ አገልግሎቴን የሰጠሁት በዋርሶ የመምሪያ ጣቢያ ስር ሲሆን ከዚያም ክቡርነትዎ፤ እጅግ በሚያኮራዎት መልኩ በክብር ተሰናብቼ ከመጣሁ በኋላ በእሳት አደጋ ተከላካይ ብርጌድ ውስጥ ሁለተኛ ሰው ሆኜ ነበር የተቀጠርኩት፡፡ ከዚያ በደረሰብኝ የጤና እክል የተነሳ የእሳት አደጋውን ብርጌድ ለቅቄ፣ የብላቴናዎቹ የመጀመሪያ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጥበቃ ሆኜ ነው ለሁለት አመታት ያህል ያገለገልኩት፡፡
"እያንዳንዷን ህግና ደንብ ጠንቅቄ አውቃታለሁ! የተከበሩ፤ ምንም የማያውቀውን የባላገር ጀሌ ማስነሳት ይችላሉ፤እኔ የምለውን ብቻ ነው ማድረግ ያለበት፡፡ ምክንያቱም የምነግረው ለራሱ የሚበጀውን ነውና! የሆነው ይሁንና ነገሮች እንዲህ ሳሉ ነው፤ ይህ አሁን የምንነጋገርበት መናኛ ነገር የተከሰተው፡፡ እርግጥ ነው ግርግሩን እንደበተንኩ አይካድም፡፡ እዚያው ከውሃው ዳርቻ ላይ ነበር አሸዋው ላይ የሆነ ሬሳ የተዘረጋው፤ አዩ አይደል! አንድ የሆነ ሰው ነው ሰጥሞ የሞተው፡፡ እዚያ ጋ እንዲጋደም ግን ማነው የፈቀደለት? አልኩና እራሴን ጠየኩ። እንደዚያ ማድረግ አሁን ምን ይሉታል? አሁን ያ ደንብ አስከባሪ እዚያ ሆኖ ምንድነው የሚሰራው? ብዬ እምር ብዬ ሄጄ “ጉዳዩን ለበላይ አካል ማሳወቅ አለብህ፤ ምናልባት ሟቹ ራሱ ይሆናል ሰጥሞ የሞተው ወይም ደሞ የነዚያ ባዕዳን እጅም ሊኖርበት ይችላል፤ ምናልባትም በነፍሰ ገዳይ የተፈፀመም ይሆናል…ምንም ይሁን ግድ የለም"
"ጓድ ዚጂን ግን እንኳንስ እኔን ሊሰማኝ ጭራሽ ቁፍድድ ብሎ ትምባሆውን እየማገ፤ ማነው ትእዛዝ እየሰጠ ያለው? ከየት የመጣ ነው? ማድረግ ያለብንንና የሌለብንን ነገር እራሳችን የማናውቅ ይመስለዋል?-- አይለኝ መሰልዎ፡፡ ግን እኔም በዋዛ አልተመለስኩለትም፡፡ የማትረቡ ገልቱ ነገር ናችሁ! ብዬ አጥረገርጋቸው ጀመራ። እውነታው ምን እንደምትሰሩ እንኳ የማታውቁ መሆኑ ነው፡፡ ዝም ብላችሁ ተገትራችሁ አውሩ እንጂ ሌላ ምን ስትሰሩ ነው?! ስል ልክ ልካቸውን ነው የነገርኳቸው። ከዚያ ነው የአካባቢውን ፖሊስ ኃላፊ እንደ ትናንት አይቷቸው እንደነበር የገለፀልኝ፡፡ ለምን? አልኩና ጠየቅሁ፡፡ የፖሊስ ኃላፊውን አይቻቸው ነበር ነው ያልከው? በየትኛው ህግና ደንብ ነው እንደዚያ የሚሆነው? አንድ ሰው ሰጥሞ ወይም ታንቆ ሲሞት ወይም ደግሞ እንደዚህ ያሉ ነገሮች ሲከሰቱ ኃላፊው ምን እንዲያደርጉ ነው የሚጠበቀው? አሁን እዚህ የተከሰተው ነገር በትክክል የነፍስ ግድያ ነው፡፡ እናም ጉዳዩ በሲቪል ፍርድ ቤት የሚታይ ነው፤ በማለት ሁኔታውን አስረዳሁ፡፡
"አያይዤም፤እንደ ህግ አስከባሪነቱ ከሱ የሚጠበቀውና ማድረግ የሚችለው ጉዳዩን እንዲመረምሩ ለሚመለከተው ክቡር ፍርድ ቤትና ጠቅላይ ዳኞች በአፋጣኝ ማሳወቅ እንደሆነ ካስገነዘብኩት በኋላ ምንም ነገር ከማድረግህ በፊት ግን መጀመሪያ ክሱን አጠናቅረህ ለአባ ፍትህ - የሰላሙ ዳኛ መላክ ይሁን! አልኩት። በደንብ ካዳመጠኝ በኋላ ምን እንደመለሰልኝ ግን ክቡር ዳኛ ማመን ነው የሚያቅትዎ! ከትከት ብሎ ነው የሳቀብኝ። እዚያ ተሰብስበው የነበሩት ወሬኞችም አብረው ሳቁብኝ፡፡ ሁሉም ናቸው የተሳለቁብኝ ክቡር ዳኛ፡፡ ይህ የምለው ነገር ሁሉ በትክክል የተፈፀመ ነገር መሆኑን ደግሞ እምልልዎታለሁ። እውነቴን ነው የምልዎ ክቡር ዳኛ፤ እዩ እዚያ ጋ ያለው ሰውዬ ራሱ ሲስቅብኝ ነበር፡፡ ያኛውም ግለሰብ እንደዚያው እየሳቀ ሲያንጓጥጥ ነበር። ምን አለፋዎ እራሱ ጓድ ዚጂን ጨምሮ ሁሉ ሲዘባበትብኝና ሲሳለቅብኝ ነበር፡፡ እናም ምንድን ነው የሚያስገለፍጣችሁ? ብዬ ስላቸው፣ እንደዚህ ያለውን ጉዳይ የሚመለከተው የሰላሙ ዳኛ አይደለም፤ በማለት ነበር ህግ አስከባሪው አፉን ሞልቶ የመለሰልኝ። ደሜን ነው ያፈላው፤ እያሉ ትኩሳታቸውን አድፋፍተው ሲያበቁ፤ ቃል በቃል እንደዚያ አይደለም ያልከው ጓድ? አሉ፤" ወደ ዚጂን ዞረው፡፡
“አዎ! ብያለሁ፡፡” አለና መለሰላቸው፡፡
“በትክክል እንደዚያ ነው እንጂ ያልከው! በዚያ ተሰብስቦ የነበረው ሰው ሁሉ ሰምቶሃል፡፡ ቆይ እንደዛ ያለ ነገር የሰላሙን ዳኛ አይመለከትም ማለት ምን ማለት ነው ክቡር ዳኛ? እንዴት ደሜን እንዳፈላው ልነግርዎት አልችልም! እጅጉን በጣም ከመገረሜና ከመደንገጤ የተነሳ፣ እስኪ ያልከውን ድገመው? አልኩት። እንዴት ነው ስለተከበረው ፍርድ ቤት ዳኛ ደፍረህ እንደዚያ የምትናገረው? ብዬ አፈጠጥኩበት። እንደ አንድ የፖሊስ አባል፣ በህግ የተቀመጠውን ስልጣን የሚቃረን ነገር ለማለት መድፈርህ ምን ይባላል? እንደዚያ በማለትህ ብቻ ክቡርነትዎ ህገ ደንቡን በሚረማመድ ታላቅ የስነ ምግባር ጉድለት ከአውራጃው ፖሊስ ጣቢያ ሰድደው ሊያሳስሩህ እንደሚችሉ ታውቃለህ? በዚህ ፖለቲካዊ አንደምታህ በቀጥታ ከስራህም ሊያስባርሩህ እንደሚችሉ ይገባሀል?"
በዚህ መሃል አቦሆይ ገቡና፤ ክቡርነታቸው፤ በህግ ከተሰጣቸው ስልጣን ውጪ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፤ ቀለል ያሉ ጉዳዮችን ብቻ ነው የሚመለከቱት፤ አሉ፡፡ እሱም ያለው ያንኑ ሲሆን ሁሉም ደሞ ሰምተዋል፡፡ ባለስልጣኑን እንደዚያ ዋጋ የሚያሳጡት እንዴት ነው?  እውነቴን ነው የምልዎ ወንድም ጋሼ፤ እንደዚያ እያሉ ባያሾፉብኝ ጥሩ ነው፤ አልያ ግን በኋላ ያዝናሉ፡፡ በዋርሶ እያለሁ ከዚያም በብላቴናዎቹ የመጀመሪያ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ጥበቃ ሳለሁ፣ አንድ ያልተገባ ህገ ወጥ ነገር ከሰማሁ ወዲያውኑ ነው ወደ ጐዳና ወጥቼ ፖሊስ የምፈልገው። እናም ፖሊስ ይዤ መጥቼ በስርአቱ ነው ቁጭ አድርጌ የሆነውን ሁሉ የምነግረው፡፡
እስኪ አሁን እዚህ መንደር ውስጥ እንደዚያ የሚያደርገው ማነው? ዛሬ ላይ ሰዎች መብት፣ መብት እያሉ በነፃነት ስም እንዲህ ሲመላገጡ እና ያልሆነ ነገር ሲያደርጉ ሳይ በጣም ነው የምበሽቀው፡፡ ለዚህ ነው ቱግ ያለብኝና የመታሁት፤ ማለቴ ያን ያህል ሳይሆን ትንሽ ነው ቸብ ያደረኩት፣ መቼስ ይረዱኛል፤ አለ አይደል! ስለ ክቡርነትዎ እንደዚያ መናገር እንደሌለበት እና ሁለተኛ እንዳይለመደው ለማስገንዘብ ያህል ነው፡፡ እሱ ግን ልክ እንደ እንትን ነው ዘልሎ ከአቦሆይ ስር የተወሸቀው፡፡ ጦሱ ለእሳቸውም ተረፈ እንጂ፤እና እንደነገሩ እሳቸውንም ቸብ አድርጊያቸዋለሁ፡፡ ከዚያ ነው ነገሩ የተጋጋለው። ክቡር ዳኛ! የምር በጣም ነበር የተናደድኩት። ደግሞም ግልጽ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ ሰዎችን ቸብ፣ ቸብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እንደነሱ ያለውን አጉራ ዘለል ሾጥ እያደረጉ ልክ ካላስገቡት ኋላ ፀፀቱ ለራስ ነው፡፡"
 “ቆይ እስኪ አንዴ! ስራቸው የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ማስከበር የሆነ ህጋዊ አካላት እኮ አሉ፡፡ ፖሊስ፣ ደንብ አስከባሪ፣ ጉምቱ ሽማግሌዎች…” ብለው ዳኛው የጀመሩትን ሳይጨርሱ ሳጅን ቀበል አደረጉና “ፖሊስ ብቻውን እያንዳንዷን ነገር ተከታትሎና ተቆጣጥሮ አይችለውም። በዚያ ላይ ደግሞ ነገሮችን በኔ መጠን ሊረዱ አይቻላቸውም” አሉ ረገጥ አድርገው፡፡
“እንደው ግን ይኼ ነገር ከቶውኑ እንደማይመለከትዎ ውል ብልዎት አያውቅም?”
“ምንም አይመለከትህም ሲሉ ምን ማለትዎ ነው ጌታዬ? ጨርሶ ከርስዎ ጋር የማይሄድ አባባል ነው፡፡ ሰዎች እንዲያ እየተንጋጉ ችግር ሲፈጥሩና መረን ሲወጡ ዝም ብለህ እለፋቸው! አይመለከትህም እያላችሁኝ ነው! ዋልጌነት ሲያጠቃቸው ጭንቅላታቸውን ትንሽ ገጨት ማድረግ የለብኝምን? ለምን እንዳንዘፍን ከለከልከን ብለው እኮ ነው የሚከሱኝ! እስኪ አሁን ከዳንኪራ ምን ይገኛል? እነሱ አንድ የሚረባ ነገር ከመስራት ይልቅ ሃያ አራት ሰዓት አሸሼ ገዳሜ ቢሉ ደስ ይላቸዋል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ መብራታቸውን አቀጣጥለው እስከ እኩለ ሌሊት ቁጭ ማለት አምጥተዋል፡፡ በዚያ ሰዓት እኮ መተኛት ነው ያለባቸው። እነሱ ግን ጭራሽ ተጐልተው ሲያወሩና ሲያሽካኩ ነው የሚያመሹት፡፡ በነገራችን ላይ ይህንንም አመልክቼ ነበር፡፡”
“ምን ብለው ነበር ያመለከቱት?”
“ቁጭ ብለው አላግባብ መብራት ሲያበሩ እንደሚያመሹ--” አሉና- የወረዛች ወረቀት ከኪሳቸው በማውጣት መነጽራቸውን ሰክተው ማንበብ ጀመሩ፡፡ “እነዚህ ስማቸውን የምጠቅሰው የሚከተሉት ወዛደሮች ማታ መብራት አብርተው ሲያውካኩ የነበሩ ግለሰቦች ናቸው - ኢቫን ፕሮኮቭ፣ ሳቫ ሚክሮቭ እና ዬቶር ፔችሮቭ፡፡ የሟቹ ወታደር ሚስት ሺስትሮቫ ደግሞ ከሴሞን ኪስሎቭ ጋር እንደምትማግጥ። ኢግናት ቬርሾክ በጥንቁልና እንደተተበተበ እና ሚስቱ ማቭራም ብትሆን ማታ፣ ማታ  በየሰው ቤት እየሄደች ከብቶቻቸውን የምታልብ ጠንቋይ እንደሆነች--፡፡”
“ይበቃል” አሉና ዳኛው ወደ ምስክሮቹ ዞሩ፡፡
ሳጅን ፕሪሽቤቭ መነጽራቸውን ወደ ግንባራቸው አቃኑና ለእሳቸው እንዳልወገኑ ግልጽ የሆነላቸውን የሰላሙን ዳኛ እጅግ በመገረምና በማዘን ተመለከቷቸው፡፡ አይኖቻቸው ተጉረጠረጡና እሳት ለበሱ፣ አፍንጫቸው ፍም መሰለ፡፡ ዳኛውን አጢነው ሲያበቁ  ወደ ምስክሮቹ ዞሩ፡፡
የዳኛው ትንሽ መረበሽ፣ የታፈኑ ሳቆች ትንቅንቅና ሹክሹክታዎች መጉላትና ችሎቱን መሙላት ግራ አጋባቸው፡፡ የተወሰነባቸው የአንድ ወር እስራት ፈጽሞ  ሊዋጥላቸው አልቻለም፡፡
“ለምን? እኮ ለምን?” አሉ፤ የሆነውን ማመን አቅቷቸው፡፡ “ኧረ ቆይ የትኛው ህግ ነው እንዲህ የሚለው?” እያሉ እጃቸውን አውጥተው ተማጽኗቸውን ሊያሰሙ ሞከሩ፡፡
አንድ የተገለፀላቸው ነገር ቢኖር አለም ክፉኛ እንደተለወጠች እናም በዚህ ሁኔታ አብረው መቀጠል እንደማይችሉ ነው። ዓለም ነው የተደፋችባቸው፡፡ ልባቸው ክፉኛ ተሰበረ። ከችሎቱ ወጥተው ወደ ግዞታቸው እያመሩ ሳለ ግን ሰዎች መንገዱ ላይ የሆነ ያልሆነውን እየቦጠረቁ ሲተምሙ ተመለከቱና በንዴት ጦፉ። ማንነታቸው መጣባቸውና መንገደኛው ላይ ዘራፍ አሉ። ሁሉም እኩል ዞረው አዩዋቸው፡፡   
“እዚያ ጋ! ተንቀሳቀሱ እንጂ በተን በሉ! የምን አጀባ መፍጠር ነው! ዳይ ወደየቤታችሁ!; አሉና እንዲበተኑ ትእዛዝ ሰጡ፡፡   

Read 1971 times