Sunday, 25 October 2020 00:00

ባለፈው ዓመት ብቻ 12ሺ ገደማ ዜጐች በኤችአይቪ ህይወታቸውን አጥተዋል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

   - አዲስ አበባ ከጋምቤላ በመቀጠል ከፍተኛ የኤችአይቪ ስርጭት የሚታይባት ከተማ ናት
          - ባለፈው ዓመት አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ14ሺ 800 በላይ ሆኗል
                   
           በአገራችን ባለፈው ዓመት ብቻ በኤችአይቪ/ኤድስ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 11ሺ 546 መድረሱን የፌደራል ኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠሪ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡ በዚሁ ዓመት አዳዲስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 14ሺ843 መድረሱንም ቢሮው አስታውቋል፡፡
የፌደራል ኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ቢሮ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች አዘጋጅቶት በነበረው የውይይት መድረክ ላይ እንዳስታወቀው፤ የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው፡፡
በዓመቱ በኤችአይቪ ከተያዙት ሰዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች የሆኑ 3230 ህፃናትም በበሽታው ተይዘዋል። በዓመቱ ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከልም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ማለትም 6570  ሴቶች ሲሆኑ፤ 2055 የሚደርሱት ደግሞ ህፃናት መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ከመጣባዠው ክልሎች ጋምቤላ ቀዳሚው ሲሆን የበሽታው ስርጭት 4.45 ደርሷል። አዲስ አበባ ከተማ ከጋምቤላ ቀጥሎ የበሽታው ስርጭት እየተስፋፉባቸው ከሚገኙ ከተሞች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን የበሽታው ስርጭትም 3.42 መድረሱን ከፌደራል አብኮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ የበሽታውን ስርጭት መስፋፋት ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም በዚሁ ጊዜ ተገልጿል፡፡ ኮሮና ቫይረስ ስርጭት መከሰት ጋር በተያያዘ ለኤችአይቪ ኤድስ ይደረግ የነበረው ትኩረት በመቀዛቀዙና በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የህክምና ክትትል ማድረግ በመቀነሳቸው ሳቢያ የሞት ቁጥሩ መጨመሩም በዚሁ ወቅት ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት በአገራችን በአጠቃላይ 669 ሺ 236 ሰዎች የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ይገኛል፡፡

Read 1185 times Last modified on Sunday, 25 October 2020 15:25