Sunday, 25 October 2020 00:00

ባንኮች ለገበታ ለሃገር ፕሮጀክት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ኮይሻ ወንጪና ጎራጎራን የቱሪስት መዳረሻ አድርጎ ለማልማት የተዘረጋውን የገበታ ለሃገር ፕሮጀክት በመደገፍ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች 283 ሺህ 328 ዶላር ማዋጣታቸውንና በሃገር ውስጥ ያሉ ተቋማትም ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን ጠ/ሚኒስትሩ ዐቢይ አህመድ አስታወቁ፡፡
“ዜጎች ለገበታ ለሃገር  እያደረጉ ያሉት ድጋፍ አስደናቂ ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የዲስፖራው ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን ለጥሪው ምላሽ  ከሰጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል አስር ዲያስፖራዎች በዕጣ ተመርጠው በህዳር አጋማሽ በሚካሄደው የገበታ  ለሃገር እራት ላይ ሙሉ ወጪያቸውን ተችሎ ይጋበዛሉ ብለዋል።
ለፕሮጀክቱ እየተሰበሰበ ያለው ገንዘብ በእቅዱ መሰረት እየተካሄደ ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የታቀደውን ሶስት ቢሊዮን አጠቃላይ ገቢ የሚያሳካ መሆኑንን  ማረጋገጣቸውንም አስታውቀዋል። የገንዘብ ማሰባሰብ ስራውን በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከአንድ ወር በኋላ በደማቅ ስነ ስርአት እያንዳንዱ ሰው 5 ሚሊዮን ብር ከፍሎ የሚታደምበት ገበታ ለሃገር የእራት ፕሮግራም መዘጋጀቱንም  ጠ/ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ለገበታ ለሃገር ፕሮጀክት ድጋፍ ካደረጉ ተቋማት መካከል አዋሽ ባንክ 30 ሚሊዮን ብር፣ ኦሮሚያ  ብድርና ቁጠባ  5 ሚሊዮን ብር፣ አስመራ ሆሊዲንግ ሊትድ 10 ሚሊዮን ብር፣ ደቡብ ግሎባል ባንክ 5 ሚሊዮን ብር፣ ንብ ኢንተርናሽናል፣ባንክ 10 ሚሊዮን ብር፣ ፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አመራርና ሰራተኛ 10 ሚሊዮን ብር፣ ዳሽን ባንክ 30 ሚሊዮን ብር፣ ብርሀን ባንክ 20 ሚሊዮን ብር፣ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ 10 ሚሊዮን ብር፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ  10 ሚሊዮን ብር ፣ አቢሲኒያ ባንክ  20 ሚሊዮን ብር ፣ዘመን ባንክ 10 ሚሊዮን ብር፣ ቡና ኢንተርናሸናል ባንክ 10 ሚሊዮን፣ ብር አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም 5 ሚሊዮን ብር፣ ሁርስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ አ.ማ 5 ሚሊዮን ብር፣ አባይ ባንክ 10 ሚሊዮን ብር ፣ የኢትዮጵያ ጠለፋ መድህን አ.ማ 5 ሚሊዮን ብር፣ ወጋገን ባንክ 10 ሚሊዮን ብር በማዋጣት ይጠቀሳሉ።

Read 1265 times Last modified on Sunday, 25 October 2020 15:26