Sunday, 25 October 2020 00:00

"የምርጫ ሥርአት ለውጥ" በዘንድሮ ምርጫ አይመከርም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  "ሥርአቱ የሚለወጥ ከሆነ የምርጫውን ተዓማኒነት አደጋ ላይ ይጥለዋል"

          ሀገሪቱ ለምርጫ በተዘጋጀችበት ዓመት፤ የምርጫ ሥርአት ለውጥ ማድረግ እንደማይመከር የጠቆመው  ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የምርጫ ሥርአቱ በአሁኑ ምርጫ ይለወጥ ከተባለ፣በምርጫ ሂደቱ ተዓማኒነትና ተቀባይነት እንዲሁም አካታችነትና ወቅታዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋን ይደቅናል ብሏል፡፡
የምርጫ ሥርአቱን እስካሁን በሥራ ላይ ከቆየው የአብላጫ ድምጽ ሥርዓት፣ ወደ ተመጣጣኝ ድምጽ  ሥርአት ለመቀየር ከተፈለገ፤ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያዎችን ጨምሮ ብዙ የህግና መዋቅር ለውጦችን ማድረግ እንደሚጠይቅ ቦርዱ ያብራራል፡፡   
የምርጫ ስርአትን ምርጫ በሚደረግበት ዓመት መቀየር ለመራጩ ህዝብ፣ ለምርጫ አስፈፃሚውና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁመው ቦርዱ፤ ሥርአቱን መለወጥ የምርጫ ህጐችን በሰፊው መቀየርን፣ የምርጫ ኦፕሬሽን ዲዛይን መከለስን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት ክለሳን እንዲሁም ስለተቀየረው የምርጫ ስርአት በሰፊው ትምህርት መስጠትን ይጠይቃል፤ ይህም እጅግ ሰፊ ጊዜን ይወስዳል ብሏል፡፡
ምርጫ በሚካሄድበት አመት ላይ ስርአቱን መለወጥ፤ በምርጫ ሂደቱ ጥራትና ተዓማኒነት ላይም ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ነው ቦርዱ የሚያመለክተው፡፡  
በአጠቃላይ አሁን ያለውን የአብላጫ ድምጽ ሥርአት ለመለወጥ ከህገ መንግስታዊ ማሻሻያው ባሻገር፤ ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ የምርጫ ክልሎች አከላለል እንዲሄም የምርጫ በጀት ለውጦችን እንደሚጠይቅ  ነው ቦርዱ የሚያመለክተው። ከፋይናንስ አንፃርም አክሳሪ እንደሚሆን ነው ቦርዱ የገለፀው፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ቁሳቁሶችን መግዛት ሊያስፈልግ እንደሚችል በመጠቆምም፤ ሀገሪቱን ለሌላ ከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ይሆናል ብሏል፡፡ #የግድ ይለወጥ ከተባለም ቦርዱ ጉዳዩን ፈጥኖ ማወቅ ያለበት ሲሆን ቁርጥ ያለ የጊዜ ሰሌዳም ሊቀመጥለት ይገባል፤ ቦርዱ በሂደቱ ላይም ምርጫ ቦርድ ለማሳተፍ ይገባል; ብሏል፡፡
በፓርቲዎች መካከል እየተካሄደ በሚገኘው የብሔራዊ መግባባት ውይይት ላይ፤ለምክክር እንደሚቀርቡ ከሚጠበቁ ጉዳዮች አንዱ የምርጫ ሥርአቱ ሊሆን እንደሚችል ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡  


Read 1114 times Last modified on Sunday, 25 October 2020 15:27