Sunday, 25 October 2020 15:54

ከግማሽ በላይ የአለም ህዝብ ማህበራዊ ድረገጽ ይጠቀማል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በዓለማችን በቀን 10 ቢሊዮን ሰዓታት በማህበራዊ ድረገጽ ላይ ይባክናል


              ከአጠቃላዩ የአለማችን ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የማህበራዊ ድረገጾች ተጠቃሚ መሆኑንና ማህበራዊ ድረገጾችን በቋሚነት የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር 4.14 ቢሊዮን ያህል መድረሱን ከሰሞኑ የወጣ አንድ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ሆትሱት እና ዊአርሶሻል የተባሉት የጥናት ተቋማት ከሰሞኑ ይፋ ያደረጉት የሩብ አመት አለማቀፍ ዲጂታል ሪፖርት እንደሚለው፤ 7.81 ቢሊዮን ከሚገመተው የአለም ህዝብ ውስጥ 60 በመቶው ወይም 4.66 ቢሊዮን ያህሉ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥም 4.14 ቢሊዮኑ ማህበራዊ ድረገጾችን በቋሚነት የሚጠቀሙ ናቸው፡፡
ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ በአለማችን የተለያዩ አገራት ከ450 ሺህ በላይ አዳዲስ የማህበራዊ ድረገጾች ተጠቃሚ ደንበኞች መመዝገባቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ይህም በአመቱ በአማካይ በየአንዳንዱ ሰከንድ 14 ሰዎች ማህበራዊ ድረገጽ መጠቀም መጀመራቸውን ያሳያል ብሏል፡፡
ከሃምሌ እስከ መስከረም በነበሩት 3 ወራት በመላው አለም፣ የማህበራዊ ድረገጾች ተጠቃሚዎች ቁጥር፣ በአማካይ በየዕለቱ በ2 ሚሊዮን መጨመሩን ያመለከተው ሪፖርቱ፣ ለዚህ በምክንያትነት የጠቀሰው ዋናው ጉዳይም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በርካታ ሰዎች እንቅስቃሴያቸው ተገትቶ በቤት መቆየታቸውን ነው፡፡
ባለፈው ሩብ አመት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች፣ በየዕለቱ በአማካይ 6 ሠዓት ከ55 ደቂቃ ያህል ጊዜ ኢንተርኔት በመጠቀም አሳልፈዋል ያለው ሪፖርቱ፤ 2 ሰዓት ከ29 ደቂቃ ያህሉን ያጠፉት ደግሞ በማህበራዊ ድረገጾች ላይ መሆኑን አክሎ ገልጧል፡፡
የአለማችን የማህበራዊ ድረገጽ ደንበኞች በቀን በድምሩ 10 ቢሊዮን ሰዓታትን ኢንተርኔት ሲጎረጉሩ ያጠፋሉ ማለት ነው፤ በሪፖርቱ ስሌት ሲታሰብ፡፡

Read 1772 times