Sunday, 25 October 2020 16:16

ሁለት ጎጆ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(11 votes)

ጸባይዋ ግርም ይለኛል፡፡ አንዳንዴ ያበደች ይመስለኛል፡፡ቢሆንስ ምን ይደረጋል! አያድርስ ነው፡፡ ፍቅርዋ ነበልባል፣ ጨዋታዋ አጥንት ድረስ የሚዘልቅ  ትዝታ ያለው ነው፡፡ ከዚያ ዉጭ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም፤ እራስዋ ፈልጋኝ መጥታ፣ ራስዋ ነዝናዛ ሆነችብኝ፡፡
ፌቨን ውበት አላት፤ ገርነትም አይባታለሁ፤ ነጭናጫነቷን ግን መናገር ይቸግራል፡፡ ውሃ ቀጠነ ነው፡፡ ቢሆንም በተገናኘን ቁጥር ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ ውበቷ ይሁን ጸባይዋ ባላውቅም ትማርከኛለች፡፡ የሚሰለቸው ጭቅጭቋ ነው፡፡ ሰው ናት ሲሏት አውሬ ናት፡፡ የቀደሙ ፍቅረኞችዋ እንዴት እንደቻሏት፣ተሞክሮ ብወስድ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ መቸም አብራው ያላሳለፈችው ወንድ የለም፡፡ ሾፌሩ፣ ኳስ ተጫዋቹ፣ መምህሩ፣ ዲያቆኑ -- በያይነቱ ነው፡፡ ምናልባት ያፈራረቀችው ነገር፣ ሕይወቷን ያዘበራረቀው ይመስለኛል፡፡ የሚገርመው ግን እንዳንዴ ገላዋ ሲነካ፣ እንደ ድንግል ሴት መበርገግዋ ነው፡፡ ምናልባት ያወራችውን እየረሳች፣ የምትሰራው ቴአትር ይሆን ብዬ አስባለሁ፡፡ ብቻ የምትገርም ናት፡፡
ሰሞኑን ደግሞ ብሶባታል፤ ምናልባት የለመደችው የፍቅረኛ ቅያሬ ሰዐት ደርሶ ሊሆን ይችላል፡፡ ስልክ ስደውልላት በደንብ አታናግረኝም፤ ቴክስት ሳደርግላት ትነጫነጫለች፡፡ ይህ ደግሞ ሰለቸኝ፡፡ ይህቺን ሴት ማስታመም የሚችለው ልዩ ስልጠና ያለው፣ የስነ ልቡና ወይም የስነ- አእምሮ ባለሙያ ይመስለኛል፡፡ ልብ ታወልቃለች፡፡
ምናልባትም ቀደም ሲል የፈነገሏት ወንዶች ትዝ ሲሏት፣ ቂሟን በኔ ላይ ልትወጣ ይመስለኛል፡፡ ቢሆንም ባፍንጫዬ ይውጣ! አይ መልክ! አይ ቁመና እንዳልል፣ድብልብል ናት፡፡ ጥርሶቿ ግን አንደኛ ናቸው፡፡ በስማም!!
ስለዚህ አሁን አቅጣጫዬን መቀየር አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፤ወላድ በድባብ ትሂድ፡፡ በጧት አንድ ወዳጄ ጋ ደወልኩ፤ይህቺ ጸባይዋም ጭንቅላትዋም  ምርጥ ነው፡፡ ታዲያ ለምን አልጠይቃትምና አላገባትም፡፡ አሁን ቢያንስ አንድ መኖሪያ ቤት አለኝ፡፡ መኪናውም ቢሆን ይገዛል፡፡
ከፌቨን ጋር ክፉና ደግ መናገር ሰለቸኝ፤ወይ ንባብ አትወድድ፤ ከሬድዮ የለቃቀመችውን አሉባልታና ተረት እያመጣች ካልደፋሁብህ ትለኛለች፡፡ ቢያቃናት ብዬ የሰጠኋትን መጻሕፍት ገጻቸውን ሳትገልጥ መልሳልኛለች፡፡ ታዲያ ከሷ ጋር ማን ይሟገታል! ዛሬ ጧት #አሁን አምሮብ  ስላት ‹‹አትበለኝ!›› አለችኝ፡፡
ወንድ ያየች አትመስልም፡፡ ሰሞኑን ግን የሆነ ነገር አግኝታለች፡፡ የምትጠብሰው ሰው አለ፡፡ እስከሚያውቃት ሊታለል ይችላል፡፡ ጸባይዋን ካየ ግን ዐይኑን ይዞ ይጠፋል፡፡ ስትነጫነጭበት፣ ስታመናጭቀው ተመልሶም አያያት፡፡ እኔ ግን አንዳንዴ ታሳዝነኛለች፡፡ የቀድሞ ሕይወቷ ጎድቷት ይሆናል፣ ፍቅር አስጀምረው ሜዳ ላይ የጣሏት አረመኔዎች ቁስል ሊኖርባት ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን እኔ ምን መጣብኝ፤ ቀጣዩ ደግሞ እኔ የቀመስኳትን ይቅመስ፡፡
ዛሬ ስራዬ አልሰራ ቢለኝም እንደ ምንም ታግዬ ቀጠልኩ፡፡ የእርሷ ነገር ቢበቃኝ ይሻላል፡፡ ቁርጡን ነግሬያት ብገላገል እወዳለሁ፤ግን ደግሞ ሆዴ አልቆርጥ ቢለኝስ! ትዝታዋ መቀመጫ ቢከለክለኝስ! ግራ አጋቢ ነገር ነው፡፡
ቢሆንም ከጸዳል ጋር ያለኝን ቀጠሮ ጠብቄ ሄድኩ፡፡ አስር ሰዐት ላይ ኢንተር ኮንቲኔንታል፡፡ ፌቨን በቃችኝ፡፡ ከእሷ ጋር የምናዘወትረው ግዮን ሆቴል ነበር፡፡ ለምን እንደምትወድደው አይገባኝም፡፡ አባትዋ ይወዱት ስለነበረ ሊሆን ይችላል፡፡ አባትዋ ከግዮን በቀር ቡና እንኳ አይጠጡም፡፡ ያን ሰምታ አድጋ ወደዚያ ስትጎትተኝ ከረመች፡፡
አሁን ነጻ የምወጣው ከሷ ብቻ አይደለም፤ከግዮንም ነው፡፡ ኢንተር ኮንቲኔንታልን ወድጄዋለሁ፡፡ ምናልባት አሁን አሜሪካ የሚገኘው ጓደኛዬ ስለሚወድደው ይሁን!! ሁላችንም ሳናውቀው የልማድ እስረኞች መሆናችንን ያወቅሁት ይሄኔ ነው፡፡ እኔም ለካ እንደ ፌቨን ትዝታዬን ላስታምም ነው!...እኔ የጓደኛዬን፣እሷ የአባቷን! ‹‹እሳት ካየው ምን ለየው!›› ይሏል ይሄ ነው፡፡
ጥሩ ነገር ለበስኩ፤ተጣጠብኩ፡፡
ስገባ ቀድማኝ ገብታለች፤ሴቶች አንዳንዴ አዲስ አድርገው ራሳቸውን ይሰራሉ ልበል! ለነገሩ ኮሌጅ እያለችም ዘናጭ ነበረች፡፡ የወንዶች ሁሉ ዐይን እሷ ላይ ነበር፡፡ እኔ ግን ለፍቅር አስቤያት አላውቅም፤ያኔ የከነፍኩት ካንዲት የጎንደር ልጅ ጋር ነበር፡፡ ጎራዳና ተጫዋች ነበረች፡፡ አቤት ነፍሴን ጥፍት አድርጋው ….ግን ምን ያደርጋል1  አሜሪካ ሄዳ ተጠፋፋን፤ ልውሰድህ ብላኝ ነበር፤አልፈለኩም፡፡
ተሳሳምንና ወሬ ጀመርን፤የኮሌጅ ሕይወት፣ጥናት፣ቀልድ ፍቅር…ምኑ ቀረ፡፡ቀስ በቀስ ጓደኛ እንዳላት ጠየኳት፡፡ ተለያይታለች፡፡ በየቦታው መለያየት ለምን እንደበዛ ላወራ ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል1 የስነጋብቻ ምሁራን ያጥኑት፡፡ እኔ የተማረ ነጋዴ ነኝ፡፡ለዚያውም ገና…ሳይንሱ ለንግድ በማይሆንበት ሀገር!
የሚበላና የሚጠጣ አዘዝን፡፡ የፈረንጅ ምግብ ስትወድድ!! እኔ ደግሞ እንጀራና ወጥ ይግደለኝ፡፡ ፌቨን #ባህላዊ# እያለች የምታላግጥብኝ ለዚህ ይሁን? መጠጥ አትወድድም፡፡ ለስላሳዋን ያዘች፡፡ ጨዋነቷን እንደጠበቀች ናት፡፡ ድንግዝግዝ ሲል ወደ መጸዳጃ ቤት ወጣ ማለት አማረኝና ስገባ፣ልጋጭ ስል ‹‹ይቅርታ‹›› አለችኝ፡፡
በሞትኩት!
‹‹ምን ታደርጋለህ?››
‹‹አንቺስ ምን ታደርጊያለሽ?››
ፌቨን ናት፤ተፋጠጥን፡፡
‹‹ከሴት ጋር መጥተህ ነው!››
‹‹አንቺስ!››
‹‹ምንድነው የምትላት?››
‹‹ምንም!››
‹‹ከኔ ጋር ናት!››
‹‹ከኔ ጋር ነበረች››
‹‹ትናንት አልፏል፣ልቀቃት››
‹‹አልያዝኳትም››
ይዟት ሄደ፤ልማዷ ነው፡፡እኔስ ብሆን ያው አይደለሁ፡፡ የኔዋም መጣች፣ አዲሷ #የኔ;› በቃ!!

Read 2317 times