Sunday, 25 October 2020 16:24

“አቶ ልደቱን አስሬ ያቆየሁት፤ ህገ መንግስትን በሃይል በመናድ በሚል ስለተከሰሱ ነው” - ፖሊስ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

“በአፋጣኝ ወደ አሜሪካ መጥተው ቀጣይ ህክምናቸውን ሊከታተሉ ይገባል” --ዶ/ር ሚካኤል ሌሚት

         የቢሾፍቱ ወረዳ ፖሊስ መምሪያ፣ በፍ/ቤት በ100 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ የተወሰነላቸውን አቶ ልደቱ አያሌውን አስሬ ያቆየሁት፣ በሌላ መዝገብ "ህገ መንግስቱን በሃይል በመናድ ስለተከሰሱ ነው" ሲል ከሰሞኑ ምላሽ የሰጠ ሲሆን የአቶ ልደቱ ሃኪም በበኩላቸው፤ የታካሚያቸው ጤንነት በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ አንደሚገኝ ጠቁመው፤ "በአፋጣኝ ወደ አሜሪካ መጥተው ቀጣይ ህክምናቸውን ሊከታተሉ ይገባል፡፡" ሲሉ አሳስበዋል፤" ዶ/ሩ በጻፉት ደብዳቤ፡፡
"ህጋዊ ፍቃድ የሌለው የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት” በሚል በቀረበባቸው ክስ፤ የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ 100 ሺህ ብር አስይዘው፣ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ቢወስንላቸውም፣ የፍርድ ቤቱ  ውሣኔ ሳይተገበር ከሁለት ሳምንት በላይ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ውሣኔውን የሰጠው ፍ/ቤትም፣ ፖሊስ ተከሳሹን በመፍታት፣ ትዕዛዙን እንዲያከብር በተደጋጋሚ ሲያሳስብ የቆየ ሲሆን ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎትም፣ ፖሊስ በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት፣ አቶ ልደቱን ያልፈታበትን ምክንያት በጽሑፍ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ነበር፡፡ የቢሾፍቱ ወረዳ ፖሊስ መምሪያ፣ ምክንያቱን በጽሁፍ  አስረድቷል። በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት፤ በ10/12/2013 በመዝገብ ቁጥር 670/13፣ በዋስትናው ትዕዛዝ መሠረት መለቀቃቸውን፤ ነገር ግን በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ ህገ መንግስቱን በሃይል በመናድ በሚል ሌላ ክስ ስለተመሠረተባቸው መልሰን አስረናቸዋል" በማለት ፖሊስ ምክንያቱን በደብዳቤ አስረድቷል ብለዋል፤ ችሎቱን የተከታተሉት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ አደነ ታደሰ፡፡
በሌላ በኩል፤ ቀደም ብለው አቶ ልደቱ ከፍተኛ የጤና ችግር እንዳለባቸውና ለኮሮና በሚያጋልጥ የእስር ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለፍ/ቤት አቤቱታ አቅርበው የነበሩትና ህክምናቸውን የሚከታተሉላቸው፣ በአሜሪካን የኢስትሳይድ ህክምና ቡድን የልብ ህክምና ስፔሻሊስቱ፣ ዶ/ር ሚካኤል ሌሚት፤ የታካሚያቸው የጤንነት ሁኔታ እንዳሳሰባቸው በደብዳቤ አስታውቀዋል። ዶክተሩ ባሠራጩት ደብዳቤ፤ “ልደቱ አያሌው ምህረቱ፣ የልብ ህመምተኛ የሆነ ታካሚዬ ነው፡፡ በሴፕቴምበር 5/201 የልብ ቧንቧ ቀዶ ጥገና አድርጌለታለሁ። አሁን ደግሞ የህክምናው ቀጣይ ክትትል የሚደረግበት ጊዜ ነው፤ በፍጥነት ወደ አሜሪካ መጥቶ ህክምናውን የመከታተሉ ጉዳይ እጅግ አንገብጋቢ ነው፤ ከህመሙ ሙሉ ለሙሉ ለማገገም፣ በዚህ ጊዜ ማከወናወን ያለበት ህክምና ወሳኝ ነው” በማለት በዝርዝር ያብራሩት ሃኪሙ፤ በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ያለው ማንኛውም አካል ሊያነጋግረኝ ይችላል" ብለዋል፤ ሰሞኑን ባሳራጩት ደብዳቤ፡፡

Read 1333 times