Sunday, 25 October 2020 18:52

በምዕራብ ኢትዮጵያ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ የእርዳታ አቅርቦትን ማስተጓጎሉ ተጠቆመ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በጉራ ፈርዳ ወረዳ 20 አርሶ አደሮች ተገደሉ

         በኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚንቀሳቀሱ ማንነታቸው የማይታወቅ ታጣቂ ሃይሎች የተነሳ ባለፉት ሁለት ወራት ለተረጅዎች  ምንም አይነት እርዳታ ለማድረስ አለመቻላቸውን የረድኤት ድርጅቶች አስታወቁ፡፡
በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ካማሺ ዞን፤ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች እየተበራከቱ መምጣታቸው፣ በተከታታይ የሚደረጉ የገበያ አድማ ጥሪዎች እንዲሁም የመንገዶች መዘጋጋት፤ ባለፉት ሁለት ወራት ለ270 ሺህ ያህል ተፈናቃዮች መቅረብ የነበረበትን እርዳታ ያስተጓጎለ ሲሆን ረጅዎች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ አለመቻሉን ነው፤ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ በሪፖርቱ ያመለከተው፡፡
በምዕራብ ወለጋ ካለፉት 5 ወራት ወዲህ ጠንካራ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ መፈጠሩን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ይህ እንቅስቃሴም ከዚያ በፊት አንፃራዊ ሠላም ወደነበረባቸው ምስራቅና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ መዛመቱን ያትታል፡፡ በአካባቢውም ካለፈው ሚያዚያ ወዲህ ብቻ 240 የሚሆኑ ወታደራዊ የጦር ግጭቶች ሲከሰቱ፣ ለአራት ጊዜያት የመንገድ መዘጋትና የገበያ አድማ የተደረጉ ሲሆን በየቀኑም በከባድ የጦር መሣሪያ የታገዘ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን ሪፖርቱ ይዘረዝራል፡፡ ይሄን ተከትሎም፣ የረድኤት ድርጅቶች ወደ አካባቢው የሚደርጉትን እንቅስቃሴ ለማቆም በመገደዳቸው በርካታ ተረጂዎች ለችግር መዳረጋቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡  
በምስራቅ ወለጋ በቋሚነት የሚረዱ 140 ሺህ ያህል ዜጐች፣ በምዕራብ ወለጋ ደግሞ 12 ሺህ ያህል ዜጎች እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን እነዚህ ወገኖች በየጊዜው ይቀርብ የነበረው የምግብና የህክምና እርዳታ በአካባቢው ባለው አለመረጋጋት ምክንያት መቋረጡን ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡ በአካባቢው በዚህ ወቅት መሠጠት የነበረበት የኩፍኝ ክትባትም መስተጓጐሉን ነው፤ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበያ ጽ/ቤቱ ያመለከተው፡፡ በአካባቢው ባለ የጦር እንቅስቃሴም፣ የህክምና አምቡላንሶች ሳይቀሩ ጥቃት እንድተፈፀመባቸውና ሹፌሮቻቸው እንደተገደሉ ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡
በተመሳሳይ፤ ከቤኒሻንጉል ከማሺ ዞን፣ወደ ወለጋ የሚመጣው መንገድ በመዘጋቱ፣ በዞኑ ለሚገኙ 130 ሺህ ያህል ተረጅዎች የምግብ አቅርቦት ማድረስ እንዳልተቻለ ተመልክቷል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራትም፤ ተረጅዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ እንዳልተቻለ ሪፖርቱ ይጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል፤ ከሰሞኑ ያልታወቁ ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች፣ በደቡብ ክልል በቤንችማጅ ዞን፣ በጉራ ፈርዳ ወረዳ በፈፀሙት ጥቃት፣ 20 አርሶ አደሮች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን የክልሉ መንግስት በበኩሉ፤ በጥቃት ፈጻሚዎቹ ላይ እርምጃ መወሰዱን አመልክቷል፡፡

Read 9607 times