Print this page
Sunday, 25 October 2020 18:52

አዲስ አበባን ራስ ገዝ ለማድረግ የሚታገሉ ፓርቲዎች ስምምነት ላይ ደረሱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 “አዲስ አበባ ራስ ገዝ መሆን አለባት; በሚል ርዕስ ባልደራስ ከሰሞኑ ባዘጋጀው ውይይት ላይ 10 የተቃዋሚ ፓርቲዎች የመከሩ ሲሆን ኢዜማ በበኩሉ፤ #የአዲስ አበባ ጉዳይ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ ተለይቶ የሚታይ አይደለም; በማለት ራሱን ከሂደቱ ማግለሉ ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባን ራስ ገዝነት በጋራ የመታገያ አጀንዳ ለማድረግ ባለመውና በባልደራስ አነሳሽነት በተጠነሰሰው ውይይት ላይ ከተሳተፉት ፓርቲዎች  መካከል 8ቱ ከወዲሁ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመው፣ የጋራ መግባቢያ ሰነድ ለማዘጋጀት የተስማሙ ሲሆን አብን፤ ውይይቱን ደግፎ በፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ደረጃ ጉዳዩን መክሮበት አቋም እንደሚይዝ ታውቋል፡፡ ኢዜማ በበኩሉ፤ በስብስቡ ውስጥ እንደማይቀጥል ማስታወቁን የባልደራስ አመራር ዶ/ር ገለታው ዘለቀ ጠቁመዋል፡፡  
በዚህ ውይይት ላይ ተሳትፈው የአዲስ አበባ ራስ ገዝነት ጥያቄን ወደፊት ለመግፋት የጋራ አቋም የያዙትና የጋራ ኮሚቴ ለማቋቋም የተስማሙት የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ህብረት፣ የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ፣ የጋምቤላ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ አብሮነት፣ አሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ መኢአድ እና ባልደራስ ሲሆኑ በቀጣይ በሚደረገው ውይይትም፤ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስቡን ይቀላቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ዶ/ር ገለታው አስታውቀዋል።
የጋራ ኮሚቴ ለማቋቋም የተስማሙት የፖለቲካ ድርጅቶች፤በቀጣይ ሁለት ሳምንት ውስጥ ተገናኝተው ኮሚቴውን እንደሚያዋቅሩ የተመለከተ ሲሆን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ፤ በሃሳቡ ዙሪያ በስራ አስፈፃሚ ደረጃ እንደሚመክርበት ነገር ግን የአዲስ አበባ ራስ ገዝ ጉዳይ አጠቃላይ ስምምነት እንዳለው ጠቁመዋል፤ የባልደራስ አመራር፡፡
በእለቱ በስብሰባው ከተገኙ 10 የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ኢዜማ አንዱ የነበረ ሲሆን አዲስ አበባ ራሷን በራሷ ማስተዳደሯን እንደሚደግፍ ጠቁሞ፤ አዲስ አበባ ራስ ገዝ (ስቴት) ትሁን የሚለውን ጥያቄ አንግቦ በጋራ ለመስራት ግን ዝግጁ ባለመሆኑ በውይይቱ እንደማይቀጥል አረጋግጧል፡፡ የአዲስ አበባ ጉዳይም በአጠቃላይ ከሃገራዊ ጉዳዮች ተለይቶ የሚታይ አለመሆኑን ኢዜማ አስገንዝቧል፡፡
አዲስ አበባ አሁን ባለው ህገ መንግስት ራሷን በራሷ እንደምታስተዳድር ቢገለጽም፤ብሔር ስለሌላት የፌደሬሽን ም/ቤት አባል አለመሆኗን የሚያወሱት ዶ/ር ገለታው፤ትግሉ ያስፈለገውም እነዚህን ሁኔታዎች ለውጦ የአዲስ አበባን ህልውና ለማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ምርጫም የአዲስ አበባ ጉዳይ አንዱ መታገያቸው እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

Read 10813 times