Saturday, 31 October 2020 11:02

በአስተዳደር ወሰንና በማንነት ጉዳዮች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ያስችላል የተባለ ጥናት እየተካሄደ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

   ጥናቱ በመጪው ግንቦት ወር ይጠናቀቃል ተብሏል
                          
              የአስተዳደር ወሰን፣ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ያስችላል የተባለ ጥናት እየተካሄደ ሲሆን ጥናቱ የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ያለባቸው ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የተካተቱበት ነው፡፡  ጥናቱም በመጪው ግንቦት ወር ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን፣ የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ ክንውኑን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዶክተር ጣሰው ገብሬ እንደተናሩት፤ ኮሚሽኑ በአስተዳደር ወሰንና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰቱትን ቅሬታዎች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችልና የማያዳግም መፍትሔ ሊሰጥ የሚችል ጥልቅ ጥናትና ምርምር በማድረግ ለመንግስት የመፍትሔ ምክረ ሃሳብ ያቀርባል ብለዋል።
ኮሚሽኑ አደረጃጀቱን ካስተካከለ በኋላ ካለፈው ሰኔ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የጥናትና ምርምር ውል መፈራረሙን የተገሩት ዶ/ር ጣሰው፤ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከ28 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ70 በላይ ተመራማሪዎች የሚሳተፉበት አገራዊ የምርምር ሥራ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ፅ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አወል ሁሴን በዚሁ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ የአስተዳደር ወሰን የማንነትና፣ ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ ዘላቂ መፍትሔ የሚመጣው "አንተም ተው አንተም ተው" በሚል ሳይሆን በጥናት ላይ በተመሰረተ ውጤት ነው ብለዋል። አያይዘውም፤ ይህንን የጥናት ውጤት ለማግኘትም ከ28 ዩኒቨርሲቲዎች የተመረጡ ከ70 በላይ ተመራማሪዎች በጥናቱ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉንም ገልፀዋል። የአጥኚው ቡድን አባላት የትምህርት ዝግጅታቸውና የሥራ ልምዳቸው እንዲሁም ነገሮችን ገለልተኛ ሆኖ የማየት አዝማሚያቸውን መሰረት ያደረገ መስፈርት ወጥቶ መመረጣቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ እያካሄደ ያለው አጠቃላይ አገራዊ የዳሰሳ ጥናት፤በመጪው ግንቦት ወር ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 4142 times