Saturday, 31 October 2020 11:09

አብን ሰላማዊ ሠልፍ መከልከሉን አምነስቲ አወገዘ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

    ዜጐች በሠላማዊ ሠልፍ ተቃውሟቸውን እንዳይገልጹ በመንግስት መከልከሉ፤ የሃሳብ ነፃነትንና በሠላማዊ መንገድ የመሰብሰብ መብትን የሚጥስና የሚያፍን ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል አወገዘ፡፡
ሰሞኑን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን የሚቃወም ሠላማዊ ሰልፍ አብን እንዳያካሂድ በመንግስት መከልከሉ የለውጡን ዲሞክራሲያዊ ጉዞ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው ያለው አምነስቲ፤ እንዲህ ያሉ መንግስታዊ የክልከላ ልምምዶች፣ በሃሳብ ነፃነት ላይ አደጋ ይጋርጣሉ ብሏል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ፣ የተጠራውን ሠላማዊ ሠልፍ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤  ሰልፉ ዕውቅና የሌለውና ህጋዊ ባለመሆኑ መንግስት ሰልፍ በሚወጡ ወገኖች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቁ፤ሀገሪቱ እከተለዋለሁ ከምትለው ዲሞክራሲያዊ ለውጥ አንፃር የሚደገፍ አይደለም ብሏል፤ተቋሙ፡፡
#ሠላማዊ ሠልፍ ለማድረግ የጠየቁ ዜጐችን በፀጥታ ሃይሎች እርምጃ እወስዳለሁ ብሎ ማስፈራራትም፣ ፈጽሞ ሊደገም የማይገባው ነው; ሲል አሳስቧል፤አምነስቲ በመግለጫው፡፡  
በተመሳሳይ ካለፈው ነሐሴ ጀምሮ አቶ ጀዋር መሐመድና በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች እስረኞች እንዲፈቱ በሚጠይቁ ሠላማዊ ሠልፈኞች ላይ በተወሰዱ የሃይል እርምጃዎች፣ በትንሹ 20 ሰዎች በምዕራብ ሀረርጌና ባሌ ዞን መገደላቸውን በመጥቀስም፤ድርጊቱ ያልተገባ ነው ሲል ተቃውሞታል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን መግለጫ በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ፤#እንኳን የአምነስቲን መግለጫ ቀርቶ ራሱን አምነስቲንንም አናምነውም; ብለዋል፡፡ #አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሚባለው ተቋም በራሱ የህወሃትና ዲጂታል ወያኔዎችን መረጃ የሚያስተጋባ በመሆኑ በተቋሙ ላይ ፍጹም እምነት የለንም; ሲሉም የተቋሙን መግለጫ በቸልታ አልፈውታል፡፡
ከሰሞኑ የሰልፍ ክልከላ ጋር በተያያዘ ኢዜማ ባወጣው መግለጫ፤ በህገ መንግስቱ የተደነገገው ሠላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብት ሳይሸራረፍ ሊጠበቅ እንደሚገባው አሳስቧል፡፡
“ሠላማዊ ሠልፍ ማድረግ ፈቃጅም ከልካይም የሌለው መብት ነው ያለው ኢዜማ፤ ሠላማዊ ሠልፉን ለማድረግ አብን በደብዳቤ ማሳወቁን ተከትሎ የክልሉ መንግስት ሰልፉን መከልከሉ ኢ-ህገ መንግስታዊ አካሄድ ነው፤ እናወግዘዋለን፤ መደገምም የለበትም; ብሏል፡፡


Read 5926 times