Saturday, 31 October 2020 11:14

መንግስት በዩኒቨርስቲዎች የተማሪዎችን ደህንነትን እንዲያስጠብቅ ኦፌኮ አሳሰበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    ዩኒቨርስቲዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዘንድሮን ዓመት ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት የተማሪዎች ደህንነትን ማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወናቸውን መንግስት አስቀድሞ እንዲያረጋግጥ ኦፌኮ ጠየቀ።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ለአዲስ አድማስ በላከው  መግለጫ፤ በ2012 የትምህርት ዘመን በኮሮና ምክንያት ትምህርት  ከመቋረጡ በፊት በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች  የተማሪዎች ህይወት በግጭት ምክንያት መጥፋቱን ጠቅሶ፤ መንግስት ችግሩ እንዳይደገም ከወዲሁ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስድ አሳስቧል፡፡
“በሃገሪቱ ያለው የፖለቲካ ቀውስና በየቦታው እየተነሱ የህዝቦቻችንን ደህንነት የሚያውኩ ግልገል አምባገነኖች የሚፈፅሙት እኩይ ተግባራት ተጨማሪ ስጋት ሊሆን እንደሚችል የጠቆመው ኦፌኮ፤ “ጠባብ አላማ ያነገቡ የተለያዩ ሃይሎች በሚፈጥሯቸው ግጭቶች፣ መንግስት የሚመድባቸው ባለስልጣናት የማስፈፀም አቅም ውስንነትና አንዳንዶች ደግሞ ከህዝባዊ ወገናዊነት ማነስ የተነሳ፤ በትምህርት ፕሮግራሙ ስኬት የሚጠበቅባቸውን ግዴታ በትክክል ሳይወጡ ሲቀሩ ተማሪዎች አደጋ ላይ ይወድቃሉ” ብሏል ኦፌኮ በመግለጫው።
ባለፈው ዓመት በተፈጠሩ ግጭቶችም በርካታ ተማሪዎች መገደላቸውን አስታውሶ፤ ተማሪዎች ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል  ሲጓዙ አላማቸውን ትምህርት ብቻ አድርገው እንዲንቀሳቀሱ የመከረው ፓርቲው፤ መንግስትም የተማሪዎችን ደህንነት ከወትሮ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያስጠበቅ ጥሪ አቅርቧል።


Read 6512 times