Saturday, 31 October 2020 11:17

4ኛው ጣና ሶሻል ሚዲያ አዋርድ በባህርዳር ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ተግባር የሚያውሉ ተቋማትንና ግለሰቦችን  በየዓመቱ የሚሸልመው ጣና ሶሻል ሚዲያ ሽልማት፤ ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በጣና ላይ በጀልባ ጉዞ በሚደረግ ስነ ሥርዓት የዘርፉን አሸናፊዎች እንደሚሸልም ዘመራ መልቲ ሚዲያና ፕሮሞሽን  አስታወቀ። የዘንድሮ ሽልማት በኮቪድ - 19 ወረርሽኝና ጣናን ለመታደግ በተደረገ ርብርብ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ተቋማትና ግለሰቦችን “ትኩረት ለጤና፤ ትኩረት ለጣና” በሚል መርህ እንደሚሸልም አዘጋጁ አስታውቋል።
የሽልማት ድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ደምስ አያሌው እንደገለጹት፤ ባለፉት 3 ዓመታት በ21 ዘርፎች ሽልማቶች ሲሰጡ የቆዩ ሲሆን ዘንድሮ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የሽልማት ዘርፎቹ ወደ 6 ዝቅ የተደረጉ ሲሆን ዘርፎቹም በበጎ አድራጎት፣ በሰብአዊነት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በጤና መረጃ፣ በፈጣን ወቅታዊ መረጃ፣ በጣና ሀይቅ አካባቢ ጥበቃና ልማት ዘርፍ እንዲሁም በልዩ ተሸላሚ ዘርፎች መሆኑ ታውቋል፡፡
ከሽልማት ስነ-ስርዓቱ ጐን ለጐን፣ ከ8ኛ-11ኛ ክፍል ላሉ ታዳጊ ተማሪዎች የሚያገለግል የኢትዮጵያ ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መለማመጃና የሥነ ምግባር ትምህርት በስርአተ ትምህርቱ ውስጥ እንዲካተትና ተማሪዎች አገራቸውንና ግብረ ገብነትን በጠበቀ መልኩ ማህበራዊ ሚዲያን እንዲጠቀሙና ግንዛቤን ጨብጠው እንዲያድጉ ለማስቻል፣ የማስተማሪያ መጽሐፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደምስ፣ መጽሐፉን በተቻለ መጠን በፍጥነት ጨርሰው ለሚመለከተው አካል ለማስረከብ እየሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል።

Read 11150 times