Saturday, 31 October 2020 11:47

ከፍተኛው ሳምንታዊ የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ተመዝግቧል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በአለማችን በሳምንቱ ከ2 ሚ. በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች ተገኝተዋል

            በአለማችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛው ነው የተባለው ሳምንታዊ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው ሳምንት መመዝገቡንና በሳምንቱ በመላው አለም ከ2 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
በሳምንቱ በመላው አለም ከተመዘገቡት አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መካከል ወደ ግማሽ የሚጠጉት በአውሮፓ አገራት እንደሚገኙ የዘገበው ቢቢሲ፤ በአውሮፓ አገራት በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በየዕለቱ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ካለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር በ40 በመቶ መጨመሩንም የአለም የጤና ድርጅትን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል።
በድርጅቱ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ዳይሬክተር ማይክ ሪያን ባለፈው ሰኞ እንዳሉት፣ ቫይረሱ ከየትኛውም የአለም ክፍል በተለየ ሁኔታ በአውሮፓ አገራት እየተስፋፋ የሚገኝ ሲሆን አውሮፓ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን በሞት ልትነጠቅ ትችላለች፤ የከፋውን ጥፋት ለመቀነስ አገራት ሙሉ ለሙሉ እስከ መዘጋት የሚደርስ ቁርጠኝነት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመላው አውሮፓ የከፋና አስደንጋጭ በሆነ መልኩ በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመር ታይቷል ያሉት የአለም የጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ዶ/ር ማርጋሬት ሃሪስ፤ ከቀደመው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር በየቀኑ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአንድ ሦስተኛ ሲጨምር፣ የሚመዘገበው የሞት መጠን በ40 በመቶ ከፍ ማለቱንም ተናግረዋል።
በአብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት ሆስፒታሎች የሚገኙ የጽኑ ህሙማን የህክምና ክፍሎች በቫይረሱ ተጠቂዎች ከአፍ እስከ ገደፋቸው መሙላታቸውን መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአሜሪካ ባለፈው ሳምንት ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ያህል አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውን የዘገበው ዘ ጋርዲያን በበኩሉ፤ በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እስካለፈው ረቡዕ 1.74 ሚሊዮን መድረሱን፣ የሟቾች ቁጥር ወደ 42 ሺህ መጠጋቱን፣ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ1.42 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ጠቁሟል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በታደሙበት የእራት ግብዣ ላይ የተገኘ አንድ እንግዳ በኮሮና ቫይረስ መያዙ መረጋገጡን ተከትሎ፣ ራሳቸውን ማግለላቸውን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡

Read 1791 times