Monday, 02 November 2020 00:00

ግዙፍ የአሜሪካ ኩባንያዎች ከድሃ አገራት በአመት የ2.8 ቢ. ዶላር ታክስ ያጭበረብራሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ቦይንግ 20 በመቶ ሰራተኞቹን እንደሚቀንስ አስታወቀ

          ፌስቡክ፣ ጉግልና ማይክሮሶፍትን ጨምሮ ግዙፍ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በከፋ ድህነት ውስጥ ለሚገኙ አገራት በየአመቱ በግብር መልክ መክፈል የሚገባቸውን 2.8 ቢሊዮን ዶላር በማጭበርበር እንደማይከፍሉ አንድ ጥናት ማረጋገጡን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
አክሽንኤይድ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በየአመቱ እጅግ ከፍተኛ ትርፍ የሚያጋብሱት እነዚህ ግዙፍ ኩባንያዎች፣ ዜጎች በከፋ ድህነት ለሚማቅቁባቸው ድሃ አገራት መክፈል የሚገባቸውን ግብር በአግባቡ እየከፈሉ አይደለም፡፡
እነዚህ ግዙፍ ኩባንያዎች ከድሃ አገራት በየአመቱ የሚያጭበረብሩት ከፍተኛ ገንዘብ ለ850 ሺህ ያህል የአገራቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ደመወዝ መሆን የሚችል ነው ያለው ጥናቱ፤ ኩባንያዎቹ ከፍተኛ መጠን ያለው ግብር ካጭበረበሩባቸው አገራት መካከል ህንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ብራዚል፣ ናይጀሪያና ባንግላዴሽ እንደሚገኙበትም አመልክቷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ቦይንግ እስከ መጪው የፈረንጆች አመት 2021 መጨረሻ ድረስ ከአጠቃላይ ሰራተኞቹ ውስጥ 20 በመቶ ያህሉን ወይም 7 ሺህ ገደማ ሰራተኞቹን ከስራ እንደሚቀንስ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በምርቶቹ ደህንነት ጉድለትና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ የከፋ ቀውስ ውስጥ የገባው የአሜሪካው ግዙፍ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ፤ እስካለፈው መስከረም በነበሩት ወራት 466 ሚሊዮን ዶላር መክሰሩንና ከዚህ በፊትም 10 በመቶ ሰራተኞቹን ማሰናበቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 2768 times