Saturday, 31 October 2020 12:48

ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ቤተሰብ ውስጥ ያለ አንድ አስቸጋሪ ልጅ ነበረ፡፡ ይሄ ልጅ ነጋ ጠባ ማልቀስ ነው ሥራው፡፡ ሞገደኛ ነው፡፡
አባት፤ “አንተ ልጅ እረፍ፤ እምቢ ካልክ ዋ! ለጅቡ ነው የምሰጥህ” ይሉታል፡፡
ልጅ ለጥቂት ጊዜ ዝም ይላል፡፡ ሆኖም ብዙ ሳይቆይ እንደገና ማልቀስ ይጀምራል።
“አንተ ልጅ ዛሬ ምን ነክቶሃል ዋ! ለአያ ጅቦ ነው የምሰጥህ፤ አውጥቼ ነው የምወረውርህ” ይሉታል፡፡
አሁንም ልጁ የአያ ጆቦን ድምጽ ሲሰማ፣ ድንግጥ ይልና ድምፁን ያጠፋል፡፡ ሆኖም አመለኛ ልጅ ነውና ከጥቂት ቆይታ በኋላ ማላዘኑን ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ አባት ይናደድና ሁለት እጁንና ሁለት እግሩን ጥፍር አድርገው ያስሩታል፡፡ ቆጥ ላይ አውጥተው ያስቀምጡታል፡፡ ይሄኔ ልጁ ዝም ይላል፡፡
እናት መቼም እናት ናትና አንጀቷ ይባባና፤
“ግዴሎትም ይሄ ልጅ አሁን ፀባይ አሳምሯል፤ ልፍታው” ትላለች፡፡
አባት፡- እንደገና ቢያለቅስ ግን ውርድ ከራሴ፤ ልጃችን በጣም ሞገደኛ ሆኗል፡፡”
እናት፡- “ልጅ አይደል፤ በአንዴ አይታረም ቀስ በቀስ ያሻሽላል፡፡ እርሶም ብዙ አይጨክኑበት፡፡”
እውነትም እናት እንዳለችው ልጁ ፀጥ አለ፡፡
ለካ ይሄ ሁሉ ሲሆን አያ ጅቦ ጓሮ ሆኖ ያዳምጥ ኑሯል፡፡ ጥቂት ቆይቶ ድምፁ ሁሉ ፀጥ አለ፡፡ አሁን አሁን ልጁን ይወረውሩልኛል እያለ ይጠብቅ የነበረው አያ ጅቦ፣ ጆሮ ቢጥል ምንም ድምጽ ጠፋ፡፡ እናትና አባት ልጁን አስተኝተው የግል ወሬያቸውን ቀጥለዋል፡፡
“ያን ቦታ እንሸጠው ስልሽ… የመሬት ዋጋ አሽቆለቆለ”
እናት፡- “ግዴለም ላመት መጨመሩ አይቀርም፡፡ ዋናው መሬቱ በስማችን ያለ መሆኑ ነው፣ በዚያ ላይ ምንም አንገብጋቢ የኢኮኖሚ ችግር አለመኖሩ ነው፡፡ የመሬት ዋጋው እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይመጣም፡፡”
አባት፡- “ነገሩ እውነትሽን ነው፡፡ የቦታ ሽያጭ በየጊዜው ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ እኔ እንደው ጓጉቼ ነው የተጣደፍኩት”
ይሄንና ሌላም የቤታቸውን ነገር እየተወያዩ ቆይተው ለጥ ብለው ተኙ፡፡
“ይሄኔ አያ ጆቦ ወደ በራፉ ጠጋ ብሎ ኧረ የልጁን ነገር ቶሎ ወስኑልኝና ገላግሉኝ” አለ ይባላል፡፡
*   *   *
በሀገራችን ብዙ ያልተወሰኑና በይደር የቀሩ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንድም ቁርጠኛ ወሳኝ አካል ባለመኖሩ፣ አንድም ደግሞ ከስር መሰረት ሲወርዱ ሲዋረዱ የመጡ በመሆናቸው፡፡ ወደ ተወሳሰበ ግጭት ያስገቡም በመሆናቸው ነው፡፡ ለያዥ ለገራዥ የማይመቹ በመሆን ደረጃ ላይ በመድረሳቸው፡፡ ይኸው የኢኮኖሚ ገጽታችን መልክ የሌለው ሁኔታ ውስጥ ገብቷል፡፡
በመሠረቱ ስራዬ ብሎና ይሁነኝ ብሎ የሚያጠና፣ የሚያቅድና የሚተገብር፤ የሚጨነቅና የሚጠበብ አካልና “አባከና” የሚል በሌለበት ንፍቀ ክበብ ውስጥ አገርን ለማልማትና ህዝብ የመታደግ ሂደትን ማጐልበት እጅግ አዳጋች ነው። ፖለቲካዊ ያገባኛል ባይነትና ኢኮኖሚያዊ ይገባኛል ባይነት ተሰናስለው በማይጓዙበት ሁኔታ ውስጥ ሥር የያዘ ለውጥን በአግባቡ ፈር አስይዞ መንቀሳቀስ፣ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአህጉራችንም ካንሰር አከል አባዜ ነው፡፡ ዛሬም ስለ ሙያዊነት፣ ሥነ ምግባራዊነት ማውራት የምንገደደው ወደን አይደለም፡፡ ያልበለፀገ የሰው ኃይል፣ በሌብነት የፈነቀለ ጐደሎ ሥርዓት፣ ስለ ሀገርና ህዝብ ይሄ ነው የሚባል እውቀትም ሆነ ብቃት አሊያም በቂ ትምህርት በሌለው ትውልድ እጅ ላይ የወደቀ ህብረተሰብ ወደፊት እንዳይራመድ አያሌ አሽክላዎች እንደሚደቀኑበት ከቶም አጠያያቂ አይደለም፡፡
ከቀን ቀን እየተሸረሸረ ያለው ሞራል ቁልቁለቱ አሳሳቢ ነው፡፡ የሀገር ፍቅር እየተመናመነ መምጣቱ አስጊ ነው፡፡ እንስራ ሲባል “እንዝረፍ” የሚል አስተሳሰብ ያለው ትውልድ፤ እለት ሰርክ እየቀፈቀፍን፣ ቀቢፀ ተስፋን እንጂ ተስፋን ማለም ጤናማ ራዕይ አይደለም፡፡ ይህ ጥበብ  “decadence” ክፉ አባዜ ነው። ሳይታወቀን እየወረድንበት ያለውን አዘቅት መለስ ብለን የምናይበት አንገት የሚያሳጣ አስደንጋጭ ተዳፋት ነው፡፡
እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሁላችንንም ተጠያቂ የሚያደርግ የመሽቆልቆል መርገምት ነው፡፡ “ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ” የሚያሰኝ ሶሽዮ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ አዝሎ የሚጓዝ ባለቤት አልባ የሚመስል ከባቢ አየር ውስጥ መሆናችን ኤጭ የማይባል ነገር ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ሠላምን ማረጋገጥ የመንግሥትም የህዝብም ግዴታ ነው። “እዚህ ቦታ ግጭት ተጀመረ…እዚህ ቦታ ሽብር ተቀሰቀሰ…” እያልን፣ በዜናና በዜማ የምናልፈው አይደለም፡፡ በድሮው መንግሥት ጊዜ መግለጫው ውስጥ “ዳሩ ሲነካ መሀከሉ ዳር ይሆናል” ይባል ነበር፡፡ ትልቅ እውነት ነው፡፡ በየዳር አገሩ የሚፈጠሩትን ግጭቶች ቸል ማለት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ የምንመኘው ብልጽግናና እድገት እውን የሚሆነው ቅንነት፣ ታታሪነትና  የመነሳሳት መንፈስ ሲኖር ነው፡፡ ያ በሌለበት ሂደት ውስጥ ያለን ከሆነ ግን “ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” የሚለውን የአበው አባባል እንድናሰላስል እንገደዳለን፡፡



Read 13073 times