Monday, 02 November 2020 08:34

የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጆች ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ተመለሱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 "ቤተ ክርስቲያን እንደ ጥንቱ በአንድነት ትቀጥላለች"

          የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ በሚል ሲንቀሳቀሱ የነበሩት እነ ሊቀ አላፋት ቀሲስ በላይ መኮንን፣ ከ6 ወራት በላይ በፈጀ ውይይትና ድርድር፣ በቤተ ክርስቲያኗ ጥላ ስር ሆነው ለማገልገል ከስምምነት ላይ  መድረሳቸው ተገለፀ።
#በኦሮሚያ ክልል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በኦሮምኛ ቋንቋ መሆን አለበት፤ለዚህም ራሱን የቻለ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እናቋቁማለን; በሚል ሲንቀሳቀሱ የነበሩት እነ ሊቅ አላፋት ቀሲስ በላይ መኮንን፤በቅዱስ ሲኖዶሱ ተጥሎባቸው የነበረው እንደተነሳላቸውና በእርቅ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር መመለሳቸው ተመልክቷል፤ ሁለቱ አካላት ከትናንት በስቲያ በጋራ በሰጡት መግለጫ፡
 የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ማደራጃ የሚለው እንቅስቃሴ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከአደራጆቹ ጋር ለ6 ወራት ያህል በርካታ ድርድሮችና ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ያመለከተው የአስታራቂ ሽማግሌዎች ቡድኑ፤በሁለቱም ወገን ያሉ የሃይማኖት አባቶች ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያደረጉት ጥረት አርአያነት ያለው ነው ሲሉ አድንቀዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የተቋቋመው የሽማግሌዎች ቡድን፤የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አመራሮች፣ ቋሚ ሲኖዶስና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የውይይቱ ተሳታፊዎች የነበሩ ሲሆን ከዚህ ቀደም ከነበረው በተጠናከረ መልኩ በኦሮሚያ ቋንቋ አገልግሎት ለመስጠት ከስምምነት ላይ መደረሱ ተጠቁሟል፡
በኦሮሚያ የእምነቱን መዳከም አስመልክቶም በጋራ ተንቀሳቅሶ መፍትሄ ለማበጀት ከስምምነት   መደረሱ የተነገረ ሲሆን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጆች ሲጠቀሙበት የነበረው የሣተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያም፤ እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን ሚዲያ እንዲያገለግል መስማማታቸው ነው በመግለጫው የተነገረው፡፡
የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን እናደራጃለን በሚል ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሊቀ አእላፋት ቀሲስ በላይን ጨምሮ አራት ካህናት ችሎታቸውን በሚመጥን የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ቦታ ላይ ይመደባሉ ተብሏል።#የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም እንደ ጥንቱ በአንድነት ትቀጥላለች; ብለዋል፤ሁለቱ አካላት በጋራ በሰጡት መግለጫ።  

Read 8695 times