Saturday, 07 November 2020 13:01

ኢሠመጉ የሠኔ 2012 ጥቃት ለዘር ማጥፋት ወንጀል የቀረበ ነው አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በጥቃቱ ከ4.6 ቢሊዮን ብር በላይ ንብረት ወድሟል ብሏል
          የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን አሠቃቂ ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያና አዲስ አበባ ተፈጥሮ በነበረው ሁከትና ግርግር ለዘር ማጥፋት የቀረበ ወንጀል መፈፀሙን ያመለከተው ኢሠመጉ ለጥቃቱ አስቀድሞ ዝግጅት ተደርጓል ብሏል፡፡
ኢሠመጉ ባለፉት ወራት በጉዳዩ ላይ ያከናወነውን ምርመራ ውጤት በ78 ገፆች አዘጋጅቶ ትናንት ይፋ ሲያደርግ በግኝቴ ማስረጃ አግኝቼባቸዋለሁ ያላቸውን የ43 ሟቾችን ማንነትና ፎቶግራፍም ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህ ጥቃት በአጠቃላይ የግለሰቦች መኖሪያ ቤት፣ የንግድ መደብር፣ የኢንቨስትመንት ተቋማትን ጨምሮ ከ4.6 ቢሊዮን በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙንም ነው ኢሠመጉ በሪፖርቱ ያስገነዘበው፡፡ ኢሠመጉ በምርመራ ስራው የአርቲስቱ ህይወት ከማለፉ በፊትም ጥቃቶች ሊደርሱ እንደሚችል የሚያሳዩ ፍንጮች ማግኘቱን በሪፖርቱ አስታውቋል።
በተለይ አርቲስቱ ህይወቱ ከማለፉ ቀደም ብሎ ባሉ ቀናት ጭምር በምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ፣ በባሌ ዞን አጋርፋ፣ በምስራቅ ሸዋ ደራ ከተማ ማንነታቸው ያልታወቁና ለአካባቢው እንግዳ የሆኑና ብዛት ያላቸው ሰዎች በግለሰቦች ቤት ውስጥ ይገቡና ይወጡ እንደበረ ኢሠመጉ ከምስክሮች ማረጋገጡን በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ጥቃቱ በተፈፀመበት ቀንም ጥቋት አድራሾቹ ጥቃት የሚፈፀምባቸውን ሰዎች የስም ዝርዝር በመያዝ ሰዎችን ያፈላልጉ እንደነበርም ነው ኢሠመጉ የጠቆመው፡፡
በዱላ፣ ቆንጨራ፣ ገጀራ፣ ጩቤ እና ሌሎች ድምጽ አልባ መሣሪያዎችን በመጠቀምም ጥቃቱ በግለሰቦች ላይ መፈፀሙን አረጋግጫለሁ ብሏል ኢሠመጉ፡፡
ጥቃት አድራሾች ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ መሆናቸውን በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች ደግሞ ጥቃት የሚፈፀምባቸውን በመጠቆም አቅጣጫ በማመላከት ተሳታፊ መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡
ጥቃቱ ሲፈፀምም ብሔርን፣ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ መሆኑን የጠቆመው የኢሠመጉ ግኝት በምዕራብ አርሲ ገደብ አሣሣ፣ አደባ፣ ዶዶላ፣ ባሌ፣ አጋርፋ፣ አምቤቴ፣ በምዕራብ ሀረርጌ መኢሶ እና አሰቦት፣ በምስራቅ ሃረርጌ ባቲ ባሉ አካባቢዎች በአብዛኛው ጥቃቱ መሠረት ያደረገው የሃይማኖት ማንነትን ላይ ነው ብሏል፡፡
በእነዚህ ቦታዎች የብሔር ማንነታቸው ኦሮሞ የሆኑ በርካቶች የጥቃቱ ሠለባ መሆናቸውም አመልክቷል፡፡
በምስራቅ ሸዋ አቦምሣ፣ አርቦዬ፣ ዴራ፤ ምዕራብ ሸዋ ወሊሶ፣ ምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ፣ አዳሚቱሉ፣ አርሲ ነገሌ፣ ዝዋይ፣ ባሌ (ኮፈሌ)፣ ምዕራብ ሀረርጌ ጭሮ፣ ድሬደዋ ባሉ አካባቢዎች ደግሞ ጥቃቱ ብሔርን መሠረት ያደረገ ነበር ብሏል - ሪፖርቱ፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች ጥቃቱ በቡድን በተደራጁ ሃይሎች ሲፈፀም የክልል ፀጥታ አካላት ትዕዛዝ አልተሰጠንም በሚል በቸልታ ማየታቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
በጥቃቱም በጥቅሉ የጭካኔ ወንጀሎች ተብሎ መበየን የሚችል በተለየ ሁኔታ ግን የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ምልክቶች ተብለው ከሚገለፁት አስር ደረጃዎች መካከል ቢያንስ ስድስት ያህሉን ደረጃዎች ያሟላ ወንጀል ነው የተፈፀመው ብሏል ኢሠመጉ፡፡

Read 954 times