Saturday, 07 November 2020 13:02

የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 የአገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ እያከናወነ ባለው የህግ የበላይነትን የማስከበር ተልዕኮ፣ በርካታ አካባቢዎችን እየተቆጣጠረ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የተጀመረው ህግን የማስከበር ተልዕኮም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የተገለፀ ሲሆን ለ6 ወር የሚቆይ የኮማንድ ፖስትም ተልዕኮውን በዋናነት እንዲያስፈጽም ተቋቁሟል፡፡
 የኮማንድ ፖስቱ ተልዕኮውን ማጠናቀቁን ተከትሎ፣ ግጭቱ እንዴት እንደተጀመረ፣ምን ኪሣራና ውጤት እንደተገኘ፣ ምን አይነት መልክ እንደነበረው በዝርዝር ለህዝብ እንደሚገለጽ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አስታውቀዋል፡፡  
"በመቀሌ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 4 ሰዓት ገደማ፣ የብሔራዊ ባንክ አዲሱን ብር ለባንኮች አሠራጭቶ አሮጌውን ብር የማምጣት ተልዕኮ የያዘች አውሮፕላን፣ መቐሌ አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ትደርሳለች፡፡ እስከ ምሽቱ 4፡30 ድረስም የገንዘብ ርክክቡን የብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች መቐሌ ካሉ ባለሙያዎች ጋር እያከናወኑ ነበር፡፡ መቐሌ በደረስንበት ሰዓት ላይ ምንም አይነት የተኩስም ሆነ የረብሻ አይነት ስሜት አልነበረም" ሲል ለኢቲቪ የነበረውን ሁኔታ ያስረዳው የብሔራዊ ባንክ ሠራተኛው ቢኒያም ፈቃዱ፤#የአሮጌ ብሩን የማረጋገጥ ተግባር ጨርሰን ልክ እኔ ወዳመጣሁት አዲስ ብር ሄደን ርክክብ ልናደርግ ስንል ተኩስ ተጀመረ” ይላል፡፡
በነበረው ተኩስ በመደናገጥ ከአዲስ አበባ የሄዱት የባንኩ ሠራተኞችም ሆነ በመቀሌ ርክክብ ሊያደርጉ የነበሩት ሠራተኞች ከአካባቢው መሸሻቸውን፣ በዚህ ሁኔታም ለሠአታት መቆየቱን ኋላም የመከላከያ ሠራዊ አካባቢውን መቆጣጠሩን ይናገራል፤ ቢኒያም፡፡ የተኩስ ልውውጡ በሌላ አካባቢ መቀጠሉንም በመጠቆም፣በአየር ማረፊያው ግን መከላከያው ባደረገው ተጋድሎ፣ የገንዘብ ልውውጡ በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን ይገልጻል፤ የባንክ ሠራተኛው፡፡
"መከላከያ ከተማዋን በመቆጣጠሩም የተለወጠውን አዲሱን ብር ወደ ማይጨው አድማ፣ ሽሬ እንደስላሴ ያሉ ባንኮች ገንዘቡን በማሠራጨት አጠናቀን በአስቸኳይ ከከተማው በመልቀቅ፣ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰናል" ብሏል፤ ቢኒያም፡፡
በእለቱም 1.3 ቢሊዮን አዲሱ ብር ለባንኮች መከፋፈሉንና 4 ቢሊዮን አሮጌውን ብር ይዘው ለጥቅምት 25 አጥቢያ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ወደ አዲስ አበባ በሠላም መመለሳቸውን አስረድቷል፤የብሔራዊ ባንክ ሠራተኛው፡፡  
መንግስት በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በህወሓት ልዩ ሃይል ስለተፈፀመው ጥቃት ዝርዝር ማብራሪያ ያልሰጠ ቢሆንም፣ ጥቃቱን በተሳካ መልኩ መቀልበስ መቻሉንና ወዲያው ከመከላከል ወደ ማጥቃት መሸጋገሩን ነው ጠ/ሚኒስትሩ ያብራሩት፡፡
ለዚህ ህግን የማስከበር የሃይል እርምጃም ቀድሞ ከመከላከያ በጡረታ ተሰናብተው የነበሩ ሦስት ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ማለትም፡- ሌ/ጀነራል ባጫ ደበሌ፣ ሌ/ጀነራል አበባው ታደሰና ሌተናል ጀነራል ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር፣ ወደ ሠራዊቱ እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን ለረጅም አመታት በሶማሊያ በሠላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ተሰማርቶ የቆየው የመከላከያ ሠራዊትም ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ በሀገር ህልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ እንዲቀለብስ ጠ/ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡
በትግራይ ክልልም ለ6 ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን ይህን አዋጅ የሚያስፈጽም ኮማንድ ፖስትም በፓርላማው ይሁንታ ተቋቁሟል፡፡ ይህን ኮማንድ ፖስት የጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም ጀነራል አደም መሐመድ የሚመሩት ሲሆን 7 አባላት ያሉት ከህግ ባለሙያዎች የተውጣጣ የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድም ተቋቁሟል፡፡
በአስቸኳይ አዋጁም ኮማንድ ፖስቱ በየጊዜው ሁኔታዎችን እያየ፣ የተለያዩ መመሪያዎችን በክልሉ ሊያስፈጽም ይችላል ተብሏል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ የክልሉ ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ ማድረግን ጨምሮ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን የማስቆም፣ የመገናኛ ዘዴዎች እንዲቋረጡ የማድረግ፣ ለተልዕኮው እንቅፋት ይሆናሉ ያላቸውን መግለጫዎች የመከልከል፣ በህገወጥ ተግባር የጠረጠራቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች የመያዝና የማቆየት ተግባር ሊያከናውን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
ቤቶችን፣ ተቋማትን፣ መጓጓዣዎችን በማንኛውም ሰዓት የመበርበር፣ ተቋማትን የመቆጣጠር ስልጣን ይኖረዋል ተብሏል፤ ኮማንድ ፖስቱ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባውን የሚያካሂደው የፌደሬሽን ም/ቤት፣ የህግ የበላይነት የማስከበር ተልዕኮውን በአጭር ለመቋጨት የሚያስችሉ ተልዕኮዎች ላይ እንደሚወያይና ውሣኔ እንደሚያሳልፍም ይጠበቃል፡፡     


Read 11947 times