Saturday, 07 November 2020 13:05

ዜጐች ከመከላከያ ሠራዊት ጐን እንዲቆሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 የትግራይ ክልል ልዩ ሃይል በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ፣ በተፈጠረው ጦርነት ዜጐች በአንድ ልብ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጐን እንዲቆሙ፣ መንግስትም የጀመረውን የህግ ማስከበር ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አቀረቡ፡፡
በትግራይ የሚንቀሳቀሰው አሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ “ለህወኃት መቃብር እንሠራለን” በሚል በሰጠው መግለጫ፤ በህወኃት ላይ የሚወሰደውን እርምጃ ህዝባችንም እኛም እንደግፈዋለን ብሏል፡፡
ለ30 ዓመታት ህወኃት በኢሮብ ህዝብ ላይ አያሌ ጭቆናና በደል ሲፈፀም ነበር ያለው ፓርቲው፤ "የህወኃት መቃበር ለኢሮብ ህዝብ ትንሣኤና ነፃነት ነው" ብሏል። ለዚህም ህወኃት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቀበር ከፌደራል መንግስት ጋር እንሠራለን ብሏል - በመግለጫው፡፡
የህወኃት አስተዳደር በይፋ መፍረሱን በመገንዘብ፣ የኢሮብ ህዝብ የወረዳውን የህወኃት አመራሮች ሙሉ ለሙሉ በማባረር በጊዜያዊነት በሚመርጣቸው መሪዎቹ መተዳደር እንዳለበት ነው አሲምባ የጠቆመው፡፡  
የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) በበኩሉ፤ የትግራይ ህዝብ በስሙ ሲነግዱ የነበሩትን የህወኃት አመራሮች በማጋለጥ ከመከላከያ ሠራዊት ጐን እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት በህወኃት ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃም ተገቢና የትግራይን ህዝብ ከጭቆና ነፃ የሚያወጣ ነው ብሏል፡፡
“ለአገራችንና ለህዝባችን ህልውና በአንድነት እንቁም” በሚል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫም፤ በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ዋነኛ ተጠያቂ የሆነው ህወኃት፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ አለበት ብሏል፡፡ ለዚህም መንግስት በህወኃት ላይ እየወሰደ ያለው የህግ ማስከበር እርምጃ ከፍፃሜ እንዲደርስ፣ ሁሉም ወገን ትብብር ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል፡፡  
ህዝቡ ከምንጊዜውም በላቀ አንድነቱን በማጠናከር፣ የመከላከያ ሃይልን እንዲደግፍና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ደህንነቱን እንዲያረጋግጥ አብን ጥሪ አቅርቧል፡፡
በህወኃት ላይ ከሚወሰደው የሃይል እርምጃ ጐን ለጐን፣ ድርጅቱ በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ የጠየቀው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) በበኩሉ፤ ከህወኃት በተጨማሪ ኦነግ ሸኔ እና ጽንፈኞችም ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡
“የሀገር ሰላምና አንድነትን ለማረጋገጥ የሚወሰደው እርምጃ በፍጥነት ተጠናቆ ሙሉ ትኩረታችንን ዲሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት ላይ እናድርግ” በሚል መግለጫ ያወጣው ኢዜማ በበኩሉ፤ እርምጃው የዘመናት የዜጐችን ስቃይና ሰቆቃ ለማስቆም በእጅጉ ጠቃሚ ነው ብሏል፡፡ መንግስት ሠላምና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከሚወስደው እርምጃ ጐን፣ ሙሉ ለሙሉ እንደሚቆም የገለፀው ኢዜማ፤ እርምጃው ሲወሰድ የሁሉም ዜጋ ሰብአዊ መብት እንዲረጋገጥ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ከህወኃት ጋር በማንኛውም መልኩ እንዳይተባበር፣ የትግራይ ልዩ ሃይልና ፖሊስ ለሀገሩ ኢትዮጵያ እንዲቆም ጭምር ኢዜማ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በቀጣይ በየክልሉ ያለው ልዩ ሃይል እንዲፈርስና በአንድ የፀጥታ ሃይል ስር እንዲደራጅም ኢዜማ አሳስቧም፡፡ የሚወሰደው ሠላም የማስከበር እርምጃ በአፋጣኝ ተጠናቆ፣ ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲካሄድና በሀገር ሠላም ላይ የጋራ አቋም እንዲያዝም ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል፡፡  
መንግስት በህወኃት ላይ የጀመረውን ጥቃት በጥንቃቄ እንዲያካሂድ የጠየቀው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በበኩሉ፤ "እርምጃው የሚደገፍ ነው፤ ህወኃት ሃገሪቱን በጦርነት መልሰን እንቆጣጠራለን ብሎ መነሳቱ የተሳሳተ ውሣኔ ነው" ብሏል፤ በመግለጫው፡፡
ጦርነቱ ሀገሪቱን በዘርና በሃይማኖት ሊነጣጥል ያለመ ሊሆን እንደሚችል የጠቆመው ኦነግ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር፣ በሃይማኖት ሳይለያይ ሀገር እንዳይፈርስ፣ ሁሉም በንቃት አካባቢውን መጠበቅ አለበት ብሏል፡፡ የመንግስት ዘመቻ አላማም፤ ጥቅማችን ተነካ የሚሉ ጥቂት ሃይሎችን ስርአት የማስያዝ መሆኑን ኦነግ እንደሚገነዘብም ነው ያስረዳው፡፡     



Read 11714 times