Saturday, 07 November 2020 13:06

በሕወኃት ኃይል ላይ የተወሰደው የመጀመሪያው ዙር ዘመቻ በስኬት ተጠናቀቀ - ጠ/ሚ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ, በስግብግቡ ጁንታ የሕወኃት ኃይል ላይ የተደረገው የመጀመሪያው ዙር ዘመቻ በስኬት መጠናቀቁን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ፤ የአየር ኃይል በወሰደው እርምጃ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ የነበሩ ሮኬቶችን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ማውደም መቻሉን ገልፀዋል።
ሮኬቶቹ እስከ 300 ኪሎ ሜትር መወንጨፍ የሚችሉ በመሆናቸውና በወንጀለኛው ቡድን ሮኬቶቹን የመጠቀም ፍላጎት በመኖሩ በመቐለና አካባቢዋ በነበረው የከባድ መሣሪያ ማስቀመጫ ላይ የአየር ኃይሉ እርምጃ እንዲወስድ መደረጉ ተገልጿል።
ከህወሀት ጋር ከእንግዲህ ድርድር እንደማይኖርና ጉዳዩ ፌደራል መንግስት በሚወስደው ህግን የማስከበር እርምጃ ብቻ ይፈታል የተባለ ሲሆን መከላከያ ሠራዊት ሠላማዊ ዜጐች በማይጐዱበት ሁኔታ ተልዕኮውን በጥንቃቄ ይወጣል ተብሏል፡፡
በመከላከያ ሠራዊት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ግልጽ፣ የተወሰነና ሊደረስበት የሚችል አላማ ያለው መሆኑንም ጠ/ሚኒስትሩ ትናንት በትዊተር ገፃቸው ያመለከቱ ሲሆን እርምጃውም በሀገሪቱ ህግና ስርአትን ለማስፈን ያለመ ነው ብለዋል። መንግስት ወደ ሃይል እርምጃ ከመግባቱ በፊት ከህወሓት ጋር ያለውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለወራት ታግሶ ድርድርና ሽምግልና ሲያካሂድ መቆየቱን የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይሁን እንጂ መንግስት ያደረገው ጥረት በሙሉ በህወኃት እምቢተኝነት መክሸፉንም ገልፀዋል፡፡
 የመንግስት ወቅታዊ አቋም ይፋ ያደረገው የመንግስት መግለጫ በበኩሉ   “ህወኃት ድብቅ ሴራ ሲያራምድ ቆይቷል፤ አሁንም እያደረገው ነው፤ ከአንድነት ይልቅ የብተና ፖለቲካ በማራመድ ህዝብን እርስ በእርስ በማጋጨት ለሞትና መፈናቀል ዳርጓል” ይላል።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮም ይህን እኩይ አላማ ይዞ መንግስትን በተለያዩ ጉዳዮች ውጥረት ውስጥ በመክተት ወደ ኋላ ለመጐተት ያለማቋረጥ ትንኮሳ ሲፈፀም መቆየቱንም መግለጫው ያትታል፡፡
የፌደራል መንግስት በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ በሆደ ሠፊነት ነገሮችን ለማለፍ መሞከሩን፣  ለእርቅና ለሠላም ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱን፣ በተለያዩ አካላትም የሠላም ጥሪ በተደጋጋሚ መቅረቡን፤ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ህወኃት ሳይቀበላቸው መቅረቱም ተመልክቷል፡፡
ይባስ ብሎ በህገ ወጥ መንገድ ምርጫ ማካሄዱን፣ ከዚህም አልፎ የሀገሪቱ ኩራት የሆነው መከላከያ ሠራዊት ላይ ተኩስ በመክፈት፣ የሀገር ሉአላዊነትና ክብርን መዳፈሩን የጠቆመው መግለጫው፤ የህወኃት ቡድን በተለያዩ እኩይ ድርጊቶቹ ሀገሪቱን በግልጽ ለማፈራረስ መንቀሳቀሱን ያመለክታል፡፡
ከእንግዲህ በኋላ ግን ይህ ሀገርን የማፍረስ እንቅስቃሴ አይፈቀድለትም ያለው መንግስት፤ አስፈላጊው ሁሉ እርምጃ እስከመጨረሻው ተወስዶ የህግ የበላይነት እንደሚከበር ነው  በአቋም መግለጫሙ ያስገነዘበው፡፡
በህወኃት ቡድን ላይ የሚደረገው የህግ የበላይነትን የማስከበር ተልዕኮ ያለ ምንም ድርድር እንደሚከናወን የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ በበኩላቸው፤ ሐሙስ እለት የተለያዩ የዲፕሎማቲክ አካላት ለድርድር እንዲቀመጡ ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸውንም ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የህወኃት ቡድን በሰሜን እዝ ላይ የፈፀመው ክህደትና ወረራ በብቃት መመከቱን የገለፁት የመከላከያ ሠራዊት ም/ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው፤ “ሀገራችን ያላሰበችው ጦርነት ውስጥ ገብታለች፣ ጦርነቱ አሳፋሪና አላማ የሌለው ነው” ብለዋል፡፡
መከላከያ ሠራዊቱ ተልዕኮውን ሠላማዊ ዜጐች በማይጐዱበት ሁኔታ በጥንቃቄ ያከናውናል ያሉት ጀነራል ብርሃኑ ጁላ፤ የትግራይ ወጣቶች በዚህ ጦርነት እንዳይሳተፉ ለሀገራቸው ኢትዮጵያ ዘብ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የህወኃት ቡድን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ባደራጃቸው ቡድኖች ያልታሰቡ ጥቃቶችን ሊያደርስ ስለሚችልም ሁሉም ህብረተሰብ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ አሳስበዋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ትናንት በሰጠው መግለጫም፤ “የህወኃት ጽንፈኛ ቡድን” በትላልቅ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ኃይል ማሠማራቱ መረጋገጡን አስታውቋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰውና የኮማንድ ፖስቱ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ትናንት በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ቡድኑ የሽብር ሃይል ወደተለያዩ ትላልቅ ከተሞች ማሠማራቱንና ከእነዚህ ሃይሎችም የተወሰኑት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡
ህወኃትና ኦነግ ሸኔ ከሀገር ውስጥም ከውጭ በሚደረግላቸው የፋይናንስ ድጋፍ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥፋት ሲፈፀም ቆይተዋል ብለዋል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል። ጥቅምት 24 ቀን 2013 በትግራይ ክልል ከ22 በላይ ተቋማት በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ሃይል ጥቃት ከመፈፀሙ በተጫማሪ ከፍተኛ የንብረት  ዝርፊያ መፈፀሙ ነው ኮሚሽሩ በግለጫው ያመለከቱት።
በአሁኑ ወቅት በህወሃት የተከፈተው ጦርነት ለመመከት የመከላከያ ሰራዊት ፌደራል ፖሊስ እና የክልል የፀጥታ ሃይሎች በተቀናጀ መልኩ እየወሰዱ ባለው እርምጃ አብዛኞቹ በቁጥጥር ስር መዋሉንና የተቀረውንም በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽነር ጀነራሉ አስገንዝበዋል። ውጥኑንም ሙሉ ለሙሉ ለማክሸፍ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡም ከፀጥታ ሃይሉ ጐን በመቆም ድጋፉን እንዲያሳይ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ መከላከያ ሠራዊት በተለያዩ አቅጣጫዎች ተልዕኮ ተቀብሎ መሠማራቱንና ትናንትም ጠንካራ እርምጃዎች ሲወስድ መዋሉን ነው መንግስት ያስታወቀው፡፡
የመቀሌ አየር ማረፊያን ጨምሮ በትግራይ አየር ክልል ውስጥ ማንኛውም አውሮፕላን እንዳይበር የፌደራል ሲቪል አቪየሽን ትዕዛዙንም አስተላልፏል፡፡
የሱዳን መንግስትም በከሠላ በኩል ያለውን ድንበሩን ሙሉ በሙሉ መዝጋቱን ሱዳን ፖስት አታውቋል፡፡    


Read 12158 times