Print this page
Monday, 09 November 2020 00:00

የልብ ማዲያቶች - “በዕልልታ እና ሙሾ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ግጥምን ሁሉም ሰው አንብቦ ለየራሱ የሚሰጠው ትኩስ ስሜት አለ፤ ወይ ይጠላል፤ ወይ ይወድዳል - ይላሉ የስነ ግጥም ሂስ ምሁር የሆኑት ኤስ ኤች በርተን፡፡ ይህ ግን ገና ድስቱ ምድጃ ሲነካ ነው፡፡ ደጋግመው ሲያጣጥሙትና፣ የቅመማውን ስልትና ይዘት ሲያጤኑ የሰውም ልዩነት፣ የጥበብም ቃና በጣም ይለያል፡፡
ግጥምን Good and bad በማለት አሊያም “Great, Good and bad” በማለት ሒሊየርና ፔረኔ ይለዩታል፡፡ የመጀመሪያው ግን እንዲህ ብለን ባንከፍለው በተሻለ ነበር ይሉናል፡፡ እንደገና “Major” “Minor” ስለሚባሉ ገጣሚያን ያወራሉ። እኛ ሀገር ገጣሚ አይደለሁም የሚል ሰው ስለሌለ፣ አንገታቸው ቀና ያለ፣ ዓይኖቻቸው ሕይወት መዝነው ስንኝ ጠርበው፣ የዜማ ቀለም የቀቡትን መለየት ከባድ ነው፡፡ የመጽሐፉ ብዛት የትየለሌ ነው (መጽሐፍ ካልነው) አንዳንዴም ነፍስ ያላቸው፣ የተወለዱና አበባቸው ውስጥ ፍሬ ያዘሉ ቀንበጦች ሳይታዩና ሣይጤኑ እንደ ሕልም ያልፋሉ፡፡
እናም በግልቦች ተርታ ሲወድቁ ስሜታቸው ይጐዳል፡፡ ውስጣቸው ይቀዘቅዛል፡፡ ከዚህ ለማዳን ብጥርጥር ያለ ሂስ ለመሥራት ጊዜውና ሁኔታው ባይፈቅድ እንኳ ፍካታቸውን ለአደባባዩ፤ ቁመናቸውን ለተደራሲ መሸሸግ አግባብ አይመስለኝም፡፡
ስለዚህም መፃሕፍት ቤት በገባሁ ቁጥር ስለ ግጥም ልቤ ተስፋ አይቆርጥም፡፡
አንዳንዶቹን በጨረፍታ አይቼ ቤት ሰልፍ ላይ ያስቀመጥኳቸውም ጥቂት አይደሉም። ይሁንና ግን ደግሞ ተስፋ ያነቦጡ አሉ። ለምሣሌ የትዕግስት ዓለምነህን የግጥም መጽሐፍ ሳየው፤ ሽፋኑ እጅግ ዘግንኖኝ ነበር፤ በዚያ ላይ ደግሞ በተገኘው መጽሐፍ ላይ (ሳይመርጡ) አስተያየት ለሚሰጡ ሰዎች ያለኝ እምነት ዝቅተኛ ስለሆነ ጀርባውን አይቼ እንደዋዛ አልፌው ነበር፡፡
የትዕግስት ጥራዝ ግን፣ ነፍስ የሚኮረኩሩ ማማሰያዎች አሉት፡፡
ለምሣሌ ገፅ 25 “ጥሪ” የሚለውን ግጥም እነሆ፡-
የተሳሰሩበትማገርናፍልጡ፣
የተቀጣጠለውላልቷልናምጡ፤
በጭድ ያልተቦካ፣ የመረሬ ልጥፍ ምርጉ
እየወደቀ፤
ሰንበሌጥ ክዳኑ፣ በድንገቴ ነፋስ ተመዞ
እያለቀ፣
አዝምማለችና ያረጀች ጐጇችን፣
በቁር በሐሩሩ ከመበተናችን፣
ጭቃውን ረግጠን፣ ቋሚና ወጋግራ በልኳ
ተጠርቦ፣
ምሰሶዋ ሳይወድቅ፣ ትጠገን ቤታችን፣
እንውጣ በደቦ፡፡
ግጥሟን ሙሉዋን የወሰድኳት፣ እንዴት ተሽሞንሙና የተጠረበች እንደሆነች አይተን - እንድናጣጥማት ነው፡፡
ዜማና ምት ብቻ አይደለም - የሀሳብ አወራረዱና ቅርፁ ሁሉ ሸጋ ነው፡፡ ቁምነገሩን ጭብጡን ስታዩት ሁለንታዊ (Universal) ነው፤ ለሀበሻ ብቻ አይደለም፤ ለሌላውም የሰው ዘር ይሆናል፡፡ ጐጆ ያልሠራ፣ ወይም የማይሠራ የለም፡፡ እንደተምሣሌት - ስታዩት ደግሞ ጀርባው ላይ ያለው ሥዕል፣ ውስጡ የደበቀችው ጥላ፣ ምናባዊ አቅምዋን የሚያሳይ ነው። ሼክስፒርን የማይበርድ የጥበብ እሣት ያደረገው የጭብጡ ትልቅነት እንደሆነ ግጥምን የተነተኑ ሁሉ መሥክረውለታል፡፡
 “ስቆርጠው” የሚለው የትዕግስት ግጥምም እጅግ የሚመስጥና የሚመነዘር ነው፡፡
አንድ ሁለት ስንኞችን ብቻ ልውሰድ፡-
የልብህ መሬቱ ጭንጫ ነበር ለካ፣
ሥር አልይዝ ብሎኛል የተከልኩት ዋርካ።
የልቡን ሚዛን ተመልከቱ፤ አስቸጋሪነቱን። ደግሞ የተራኪዋን ገርነት መዝኑት!
በጭንጫ ልቡ ላይ፣ የተከለችውን ዛፍ ግዝፈት፡፡ ምናልባት ይህ ዛፍ የእምነት ስራ ነው ዘር እንደመበተን፡፡
ይህ የተከለችውን የፍቅር ዋርካ ስር እንዳይሰድድ ያጠጠረውን ሰው መልሳ እንዲህ ትለዋለች፡- አሁንም ፍቅር እንደ ጐርፍ ውስጧ እየፈሰሰ፡፡
አልሻውምካልከኝ፤
አላስቸግርህም በፍሬ አልባ ሙግት፤
ባይሆንአትንቀለው፣
ይሆንሃልና ለርስትህ ምልክት፤
ግን አደራምልህ፣
ቅርንጫፉንሁሉ በሆዴ ከምረው፣
መልምልና ግንዱን
ለ’ሳቴ እየማገድኩ እንዳልፍበት ብርዱን፡፡
ግርምርም የሚል ነገር ነው፡፡ አሁንም ዛፉ ርስትህ ነው! ማለት፣ እንግዲህ ለሌላ ሰው አይሰጥም ዓይነት ነው፡፡ ያ ብቻ አይደለም፤ የመጨረሻዎቹ መዝጊያ ስንኞች እንዴት ያለ ዜማ ነው ያላቸው!! ብዙዎቹ የትዕግስት ግጥሞች በሙዚቃና ምት ችሎታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡  የብዙ አማርኛ ግጥሞች ሠባራነትና ሽባነት ያለበትን ቦታ እርሷ ተወርውራ አልፋዋለች። ግጥሞቻችንን መርምሩ! ዋናው በሽታ ይህ ነው፡፡
“ጦም አዳሪ” የሚለው ግጥም የሀበሻን ይሉኝታ ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ ነው፡፡
ከልብህ በራፍ
ላይ ለወራት ቆሜአለሁ፣   
 ስትከፍት ስትዘጋ፣ ስትዘጋ ስትከፍት፣
ተወው አንዳከም ሐበሻነት ክፉ፣
 ነይ ግቢ እስካላልከኝ፣
አላልፍም ከደፉ፡፡
ተራኪዋ ግብዣ ትጠብቃለች፣ ተፈቃሪው ራስዋ ትምጣ ይላል፡፡ ይተያያሉ፣ ግን ውሣኔ እንደውሻ በባህል ሰንሰለት ተጠፍሯል። በ“ባቢሎን በሳሎን” ኮሜዲ ቴአትር ላይ ባልና ሚስቱ ልባቸው እየተፈላለገ፣ በይሉኝታ ሳሎናቸውን አጥረው፣ በስቃይ ነፍሳቸው ተንጠልጥላ እንደምትቃትት አይነት ነው ነገሩ! እነዚህ ግን ገና አልጀመሩም፡፡ ይህንን ነው ገጣሚዋ የምትሸነቁጠው፡፡ በዚህ መሃል ደግሞ ነጣቂ ቢመጣ፣ ስሜት ቢላላ፣ የዕድሜ ልክ ፀፀት ነው፡፡
የመጽሐፉን ርዕስ የያዘው “እልልታና ሙሾ”ም የሚመረጥ ግጥም ነው፡፡
እዚህ ግጥም ላይ መሠሪነትና ብቀላ አይን ላይን ተፋጥጠዋል፡፡ ተበቃዩ ወገን ግን ዳኛ ነው የሚፈልገው። ይኸ ዳኛ ከየት ይሆን…የሚመጣ!መዘግየቱ ሩቅነትን የሚጠቁም ይመስላል፡፡ ትዕግስት ብዙ በሽታዎችንና ግሣንግሥ ችግሮቻችንን ከነጥቀርሻቸው ታውቃቸዋለች፡፡ ከላይ የሚለብሱትን የበግ ለምድም ከቀበሮዎቹ ገፍፋ የማየት አቅም አላት። ግጥሞችዋ ማህበራዊ ሒሶች ይበዟቸዋል፡፡ “ገመና” የምንላቸው ሽንቁሮቻችንም ከአይኗ አልተሰወሩም፡፡ ፈልፋይና ቅንዐት (Zeal) ያላት ናት፡፡ ለብቻቸው ሞቀን ብለው፣ እሾህ ያንገበገበውን የሚረሣ ነፍስ የላትም። “ምናልባት “ሀገርህን ጥላት ልጄ” የሚል መጽሐፍ የፃፈውን ወጣት ደራሲ አይነት ነገር አይቼባታለሁ፡፡
ጆሮዎችዋ ወደ ውስጥም ወደ ውጭም የሚያዳምጡ ይመስላል፡፡ ግጥሞችዋ ከአንድ ሰሞን ወረት ያፈሠቻቸው አይደሉም። በሰው ልጅ ፍቅር የነደዱ ልቦች ላይ የከሰሉ ማዲያቶች ምስል ናቸው፡፡ ሳቆችዋ ይጣፍጣሉ፣ እንባዎችዎ አንገት ይነቀንቃሉ፡፡
ግጥሞቿ፤ እንደ ባህር ዛፍ ቅጠል ላይ ላዩን አይነድዱም፤ ሥር ገብተው የልብን እምብርት ይቆነጥጣሉ፡፡ እንደ ጉንዳን ደም ውስጥ ይሄዳሉ፤ እየቆነጠጡ፡፡
ገጣሚዋ ትልልቅ ጭብጦች እጅዋን ሞልተውታል፣ ብዕርዋን ውጠውታል፡፡ ጥቅል ሰው፤ ሀገር፣ እና ያገር ሰው ጭብጦችዋ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ጉዳዮችዋ መሣጭና ቆንጣጭ ናቸው፡፡ “አዬ ኢትዮጵያዬ!” ብላ ሀገርዋን በቁልምጫ እየጠራች፣ ችግሯን የተጋራቻትን ግጥም ቀዳዳችሁ አንብቡት፤ ደጋግማችሁ፡-
“ሐዘንሽ ቅጥ
አጣ
ከቤትሽ አልወጣ፣
የገደለው ባልሽ፣
የሞተው ወንድምሽ”
እንዲል ባለቅኔው ዕጣ ክፍልሽ ሆኖ፣ ይዘሽ እንደ ሲቃ፣ እንባሽ ወደ ውስጥሽ፣ መፍሰስ መንቆርቆሩ ዛሬም አላበቃ፡፡
  ከልጅሽ ገዳይ ጋር፣ ድንኳን
ተጋርታችሁ ደረት እያደቃሽ፣
  ማን ያባብልሻል አንቺም
እሱም አልቃሽ፡፡
(ከሃያሲ ደረጀ በላይነህ ለህትመት የተዘጋጀ ረቂቅ መጽሐፍ የተወሰደ)

Read 2784 times
Administrator

Latest from Administrator