Print this page
Saturday, 07 November 2020 15:48

የኑሮ ዥንጉርጉር መልኮች፤ በአለማየሁ እሸቴ ዜማዎች

Written by  ፊደል ችሎ
Rate this item
(0 votes)

  ሙዚቃ፣ ልብን የመቧጠጥ፣ ፍላጎትን የመግለጥ ታላቅ አቅም አላት፡፡ በተፈጥሮዋ፣ እንዲህ ብለን የማንገልፀውን ሰፊ ዓለም  የማዳረስ አቅም አላት፡፡ የሰነፈ ገላን የማበርታት፣ ተስፋ የቆረጠ ልብ ተስፋን እንዲሰንቅ የማድረግ፣ በፍርሀት የተሸበረን መንፈስ የማጀገን ኃይል አላት፡፡ የካሳ ተሰማን “ፋኖ ፋኖ” ሰምቶ ማነው የማይጀግን? የእጅጋየሁ ሽባባዉን “እኔ የራበኝ ፍቅር ነው” የሚለውን ውብ የጥበብ ሥራ አድምጦ ማነው በፍቅር የማይብሰለሰል? የሙሀመድ አህመድን “ሰላም” ሰምቶ ማነው ዘገሩን አርቆ የማይጥል?
ሙዚቃ፣ የተሰበረ መንፈስን በማዝናናትና በማዋዛት ብቻ አትወሰንም፤ በድንበር የምትገደብ ረቂቅ ጥበብም አይደለችም፡፡ በየዘመኑ፣ ስልቱ ይለያይ እንጂ ሙዚቃ የተከፋውን የማፅናናት፣ የደከመውን የማበርታት፣ በሀዘን ልቡ የተሰበረውን የማባበል ሚና አላት፡፡ እስኪ የሀገሬን ገበሬ የአጨዳ ላይ ሆሆታ ልብ እንበል፣ እስኪ የአዝማሪውን እውነትን የተመለከተበትን ምስጢር እንግለጥ፡፡ ሙዚቃ፣ የሰው ልጅ መከፋቱን፣ መራቡን፣ መጠማቱን በአጠቃላይ በህልውናው ውስጥ የተከሰተውን ሁሉ የምትዳስስ፣ መለኮታዊ ህልውና ያላት ታላቅ የሰው ልጅ የምናቡ ውጤት ናት፡፡
አለማየሁ እሸቴ ታላቅ ዘፋኝ ነው፤ ስሜታችንን ቀስቅሶ ሳናስበው አብዮተኛ የሚያደርገን፣ ድንገት ተነስተን ለውጥ ናፋቂ፣ ኢ-ፍትሀዊነትን ተገዳዳሪ እንድንሆን የሚያነሳሳ ታላቅ ድምፃዊ ነው፡፡ በዘፈኖቹ ውስጥ የሰው ተስፋው፣ ህመሙ፣ ቁጭቱ፣ አልሸነፍም ባይነቱና ትግሉ ጎልተው የሚገኙ ናቸው፡፡ ሥራዎቹን በአንክሮ ስናዳምጥ፣ በኑሮአችን ተስፈኛ መሆን ትልቅ ፋይዳ እንዳለው እንረዳለን፡፡ በ‘ተማር ልጄ’ ዉስጥ የተላለፈዉ ቁም ነገር፤ ከአባት ለልጅ የተሰነዘረ መልካም  ምክር ነው፡፡ “ያበጠው ይፈንዳ”  የሚለው ዘፈን፣ ነገርን በሆድ ውስጥ አርግዞ ከመብሰልሰል ይልቅ የሚያምኑበትን መተንፈስ ተገቢ ጉዳይ መሆኑን የሚጠቁመን ነው፡፡
አለማየሁ እሸቴ፣ በስራዎቹ ስለ ኢትዮጵያ ይታመማል፣ ስለ ተራቡት፣ ስለ ታረዙት፣ ተስፋ ስለ ቆረጡት ..ወዘተ በስፋት አዚሟል። አለማየሁ፣ የወገኖቹን ስቃይና ህመም በስራዎቹ ውስጥ በስፋት ያስተጋባ ታላቅ ከያኒ ነው፡፡
አለማየሁ፣ በዘፈኖቹ ውስጥ የግል ሕይወቱንና ገጠመኙን የሚያዜም ይመስላል፣ ጠለቅ ብለን ስናስተውል ግን ዜማዎቹ የወል ህልውናዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ናቸው፡፡ ‘ስቀሽ አታስቂኝ፣ የደላኝ ይመስል’ የሚለው ዜማው፣ የአገሩን እንግልት የሚገልፅ ነው። ዜማው፣ የዘመኑ ኢትዮጵያ እንዴት እንደ ነበረች፤ ኢትዮጵያውያኖች የሚኖሩትን ህይወት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነዉ፡፡ ሙዚቃ፣ በባህሪዋ ጨካኝ ልብን የማራራት፣ የተቆጣን መንፈስ የማለዘብ፣ የናፈቀን ልብ የማፅናናት ልዩ ኃይል አላት፡፡ ይህ ተፈጥሮዋ አለማየሁ እሸቴ ላይ ሲደርስ ይጎላል። እሱ ስለ እናት ሲያዜም ሰምቶ ማን ነው ልቡ የማይተክዝ? የአለማየሁ ስራዎች የያንዳንዳችን ልብ የመያዝ አቅም አላቸው። አለማየሁ፣ በኪነት ስራዎቹ ታሞ ሌሎች ህመሙን እንዲጋሩት የሚያስገድድ ባለ ልዩ ተሰጥኦ ድምፃዊ ነው፡፡ በዘመኑ የነበረው የአገሩ የፖለቲካ ምስቅልቅል  የፈጠረበትን የልብ ስብራትና ቁጭት በስራዎቹ ውስጥ በጥልቅት ዳስሷል፡፡ ስቀሽ አታስቂኝ በሚለው ዜማው፣ ኢትዮጵያውያኖች ምን ፈልገው ምን እንዳጡ፣ ለምን የተራቡትን ማጥገብ እንዳቃታት  ሲጠቅስና የወገኖቹን ህመም አብሮ ሲታመም እናስተውላለን፡፡  
እኔ ልኮራመት እኔ ከሰል ልምሰል፣
ስቀሽ አታሲቂኝ የደላኝ ይመስል፡፡
ሁሉን አውቀዋለሁ  ግማሽ አካሌ ነሽ
ሞተሽ ታርፊዋለሽ አንድም ቀን ሳይደላሽ።
አለማየሁ በእንዲህ መሰል ዜማዎቹ ስለ መቸገር፣ ስለ ማጣትና ስለ ህይወት ዥንጉርጉር መልኮችና ገፅታዎች በስፋት አዚሟል፡፡ የእሱን ስራዎች ሰፋ አድርገን ስንመረምራቸው፤ የያኔዋን ኢትዮጵያ፣ የዘመኑን እውነት፣ የህዝቦቿን ውሎ፣ ተስፋ፣ ማጣትና ማግኘት የሚዳስሱ ናቸዉ፡፡ የአለማየሁ ዘመን ኢትዮጵያ፣ እንደ ዛሬዉ በየደጃፉ የትምህርት ተቋማት አልተስፋፉም ነበር፡፡ በውቅቱ፣ ብዙዎች ፊደል ለመቁጠር ተነሳሾች አልነበሩም፡፡ ታዲያ አለማየሁ ዝም አላለም፡፡ የትምህርትን ጥቅም ለህዝቡ ሊያስረዳ #ተማር ልጄ;ን አቀነቀነ፡፡ ይህ ዘፈን ኢትዮጵያኖች ለትምህርት ያላቸውን ቦታ መነሻ ያደረገ ነው፤ ትምህርትን አስመልክቶ የኢትዮጵያ  ወላጆች ምን አይነት አተያይ እንደነበራቸው ያብራራል፡፡
ተማር ልጄ … ተማር ልጄ …
ወገን ዘመድ የለኝ ሀብት የለኝም ከእጄ፡፡
ስማኝ ልጄ ...  
ሌት ፀሀይ ነው፣
ላልተማረ ሰው ግን ቀኑ ጨለማ ነው፡፡
 ተማር ልጄ፣ ሠው ከድንቁርና አዘቅት ወጥቶ ወደ ፀዳልና ትልቅነት ጎዳና የሚሸጋገርበት መሰላል መሆኑን የሚያትት ድንቅ የፈጠራ ስራ ነው፡፡ እንደ እኔ መረዳት፣ አለማየሁ እንዲህ ያሉ ስራዎችን ለመስራት የቻለው የአገሩን ህመም መታመም መቻሉንና የህዝቡን ጭንቀት አብሮ መጨነቅ መቻሉ ነው፡፡ ከፖለቲካ አመላካከት በላይ ሀገር አለች፣ የትውልድ ቅብብሎሽ አለ፡፡ እነዚህ ሀቆች ናቸው የአለማየሁ ኪናዊ ስራዎች አቢይ ገፊ ምክንያቶች፡፡ የአለማየሁ ስራዎች፣ አንድ ከያኒ ሲብሰለሰል፣ አጥብቆ ሲጠይቅ፣ ብዙሀኑን ህዝብ ሲያስብ፣ ለውጥን አብዝቶ ሲመኝ ይበልጥ ትልልቅ ኪናዊ ስራዎችን መስራት እንደሚችል ማሳያዎች ናቸዉ፡፡   
አለማየሁ፣ የሰው ልጅ፣ ስለ ነፃነት መታገል እንዳለበት ይዘፍናል፤ ግን  አብዮት አቀጣጣይ ብቻ አይደለም፣ ለነፃነት የሚደረግ ትግል አስተውሎት በተሞላበት መንገድ የሚደረግ እንደሆነ ያሰምርበታል፡፡ ጭቆና፣ መጎሳቆል፣ በአንድ ዘመን ተከስተው የሚያልፉ፣ ታሪክ የሚሆኑ እንደሆኑም ይነግረናል፡፡ ለዚያም ነው፣ በችግር ውስጥም ሆኖ ነገን በተስፋ መመልከት እንደሚገባ የሚዘፍነው፡፡
የአለማየሁ ዘፈኖች፣ ለነፃነት የሚሰጡት ግምትና ቦታ ልዩ ነው፤ ብቸኝነትን የሚመለከቱበት አንግል አስደናቂ ነው፡፡ የአለማየሁ ስራዎች፣ የእያንዳንዱን ግለሰብ የስጋና የመንፈስን ህመም የሚጋሩ ናቸው፡፡  ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ስራው ይህን እውነት የሚያስረግጥ ነው፡፡
አንድ ነኝ ለናቴ እሷም የለች ባለም   
ብቸኝነት ጭንቄን የሚሰማኝ የለም   
የት አለኝ መካሪ የምወደው አባት?   
የት አለኝ መመኪያ ወንድም እና እህት?  
የት አለኝ ጓደኛ እንደራሴ የማምነው?     
የሆዴን የልቤን ምስጢር የማዋየው፡፡
ይህ ዘፈን፣ በብቸኝነት የተገፋ ማንነትን የሚናገር ነው፡፡ ግን፣ ዘፈኑ መቼና ለምን እንደተዘፈነ ታሪኩን ስንመረምር፣ የዚያን ዘመን በኑሮ ተስፋ ማጣት፣ እርስ በርስ ያለመተማመን መንፈስ እንዲሁም የሰውን ልጅ የስጋና የመንፈስ ጭንቀት ይጠቁማል። ምርምራችንን ባሰፋነው ቁጥር፣ በጊዜው በነበረው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ተከስቶ የነበረውን የሰውን ልጅ የስነ-ልቦና መታወክ በቅጡ መግለፁን ስናስተውል፣ የዘፈኑን ጥልቀት እንረዳለን፡፡ ዘፈኑ፣ ተስፋ የመቁረጥን ስሜት ማእከል አድርጎ የሚነሳ ሲሆን የግለሰቦች ውስጣዊ የባይተዋርነት ዓለም ምን እንደሚመስል የሚተነትን ነው፡፡
ዘፋኝነት፣ ልዩ ክህሎት ወይም መሰጠት ከሚፈልጉ ሙያዎች መካከል አንዱ ነው። ዘፈን የአቀንቃኙን ስስ ልብና ስሜት እንዲሁም ጥልቅ መመሰጥን ይፈልጋል። ዘፋኝነት፣ አብሮ የሚወለድ ፀጋ ሊሆንም ይችላል፡፡ አለማየሁ ሲዘፍን፣ እያንዳንዳችን የውስጣችንን ሀሳብና ስሜት እናስተጋባለን። አለማየሁ፣ ትምህርትን፣ ነፃነትን፣ የሰው የመንፈስ መታወክን፣ ከፖለቲካ እውነታችን ጋር እያሰናሰለና ከማህበራዊ እውነታችን ጋር እያነፃፀረ ዘፍኗል፡፡ አለማየሁ፣ “የሰው ቤት የሰው ነው” በተሰኘው ሥራው የሚያነሳው ጭብጥ ራስን ስለመቻል ነው፡፡ ዘፈኑ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ የፍለጋ አውድ፣ ግላዊ ህይወቱን የማደላደል ሃላፊነቱን ለመሸከም ጫንቃውን እንዲያደነድን የሚሰብክ ነው፡፡
አለማየሁ፣ የሰው ልጅ ነፃነትን፣ ማህበራዊ ፍትህን፣ የብዙዎቻችንን ነፍስ የሚሞግቱንን ጥያቄዎች፣ የሚያሙንን የመከራ ሸክሞች በጥበብ ስራዎቹ ዳስሷል፡፡ ከተጣባን የመንፈስ ድውይ የምንፈወስበትንም ዜማ አዚሟል፡፡ ለዘመኑ መንፈስ ትኩረት ሰጥቶ፣ እያንዳንዱ ሰው የሚያመውን፤ የስነ-ልቦና መታወኩን ታሞታል፡፡   

Read 1380 times