Saturday, 14 November 2020 10:24

የአገራችን “የመንግስት ቴሌኮም”፣ እና እልፍ “የስታርሊንክ ሳተላይቶች”።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

መንግስት በሞኖፖል የያዘው አገራችን የቴሌኮም አገልግሎት፣ ገና ለግል ኢንቨስትመንት አልተፈቀደም። አለማቀፍ የቴክኖሎጂና የቢዝነስ ጉዞ ግን፣ ቀሞ የሚጠብቅ አልሆነም። እንዲያውም፣ ግስጋሴው  እየፈጠነ፣ ይበልጥ እየተራቀቀና እየከነፈ ነው። አሁን ደግሞ፣ እልፍ የስታርኪንክ ሳተላይቶች እየመጡ ነው።
ሳተላይቶቹ፣ ድንበር የማይገድበው የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት ሲያስፋፉ፣ የአገራችን ቴሌኮም ምን ይውጠዋል? ነፃ ገበያን በማስፋፋት፣ ከቴክኖሎጂና ከቢዝነስ ፍጥነት ጋር እንደመገስገስ፣ በመንግስት ቁጥጥር መደንዘዝና የኋሊት መቅረትስ እስከመቼ?
የ25 ዓመት ለውጦችን አስታውሱ። ኢንተርኔት የሚሉት ነገር መምጣቱ ራሱ ተዓምር አይደለም?  ከግስጋሴው ፍጥነት የተነሳ፣ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ ለመድረስ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም።  በግል ኢንቨስትመንት አካማኝነት የተፈጠረ ተዓምር ነው ኢንተርኔት።
የኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎትስ? ከመንግስት በስተቀር ለግል ቢዝነስ አልተፈቀደም። እንደ ቀድሞው ያለ ለውጥ ነው የቀጠለው። በዚህም ሳቢያ፣ የአገራችን የኢንተርኔት አገልግሎት፣ በብዙ መስክ፣ የኋሊት ቀርቷል።
አዎ፤ ኢንተርኔትን ለፖለቲካ ብሽሽቅ ለመጠቀም አልሰነፍንም። ነገር ግን፤ በጭፍንነትና በአሉባልታ ማዕበል ለመጥለቅለቅ የመፍጠናችን ያህል፣ ቁምነገር ሰራንበት? ኢንተርኔትን፣ ለእውቀትና ለሙያ፣ ለስራና ለኑሮ፣ ለኢኮኖሚ እድገትና ለስራ እድል ፈጠራ… ብዙም አልተቀምንበትም። ወደኋላ ቀርተናል። ይህም ብቻ አይደለም።
ከኢንተርኔት ጋር እየተጣመረና ላይነጣጠል እየተዋሃደ፣ በአስገራሚ ፍጥነት የገሰገሰ ሌላ ለውጥ አለ - የሞባይል ስልክ። ይሄም፣ ከግል ቢዝነስ የተገኘ ተዓምረኛ ለውጥ ነው። ታሪኩ ያስገርማል። ያኔ፣ ከኒውዮርክና ከሆንግኮንግ ጀምሮ፣ የሞባይል አገልግሎት፣ በቴክኖሎጂውም በቢዝነስም እየተራራቀ፣ በጥቂት ዓመታት አለምን ያደርሳል ብሎ ማን ገመተ?፣ ከቢሊዮን ሰዎች የእለት ህይወት ጋር ይቆራኛል ብሎስ ግን አሰበ? ያኔ እንጂ፣ አሁንማ፣ የእለት ሕይወትን ያለ ሞባይል ስልክ ማሰብ ከባድ ሆኗል። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ስንቱ ተቀየረ? የቴክኖሎጂና የቢዝነስ ሰዎች የሰሩት አስገራሚ የለውጥ ታሪክ፣ ከድንቅ ተዓምር አይተናነስ።
የኢትዮጵያ ቴሌኮም አገልግሎትስ? አልተለወጠም። ለግል ቢዝነስ ክፍት እንዲሆን አልተደረገም። በመንግስት ስር ነው የቀጠለው። በዚህም፣ ኢትዮጵያ፣ የኋሊት ቀርታለች። በእርግጥ፣ ከ1 ሚሊዮን በላይ ፎቀቅ ማለት አቅቶት ከነበረው የመስመር ስልክ ጋር ሲነፃፀር፣ የሞባይል ስልክ ቴክኖሎጂ፣ ለኢትዮጵያ ፈጣንና ሁነኛ መፍትሄ ሆኗል። ከ40 ሚሊዮን በላይበ ሰዎች የሞባይል ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል። እንዲያም ሆኖ፣ በኢንተርኔትና በሞባይል የአገልግሎት፣ በአይነትም በጥራትም፣ ኢትዮጵያ የኋሊት ቀርታለች።
በዚያ ላይ፣ በኢንተርኔት አማካኝነት፣ ነፃ የመልዕክትና የሥልክ ትስስር እየተስፋፋ በሄደ ቁጥር፣ የኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን ገቢ እየተሸረሸረ መሄዱ አልቀረም። በተለይ፣ ከውጭ አገር የስልክ ጥሪ መጣ የነበረው ገቢ ተጎድቷል።  አሁን ደግሞ፣ ሌላ ከባድ ፈተና  እየመጣበት ነው። የአዲሱ ፈተና፣ ድንበር አይበግውም። እንዴት?
የቴሌቪዢን አገልግሎት ላይ የመጣውን ለውጥ አስታውሱ። ድሮ፣ የቲቪ አገልግሎት ለማቅረብ፣ በየቦታው አንቴናዎቻችን መትከል የግድ ነበር። መንግስትም ይህንን መቆጣጠር ይችል ነበር። ከዚያስ? ከዚያማ፣ የሳተላይት ቴሌቪዥን መጣና፣ ነገሩ ተቀየረ። የመንግስት ቁጥጥር ተሸረሸረ።
አሁን፣ የሳተላይት ኢንተርኔትና የሳተላይት ስልክ ሲስፋፋስ? የቴሌኮምን አገልግሎት፣ በሞኖፖል ይዞ በቀድሞው መንገድ መቀጠል ያዋጣዋል?
በእርግጥ፣ የሳተላይት ኢንተርኔትና ስልክ፣ እንደ ሳተላይት ቴሌቪዥን ቀላል አይደለም። ለነገሩ፣ ስንት አመት ብዙ ቢወራለትም፣ ያ ያህል አልተሳካለትም። ገሚሶቹ ሙከራዎች ያለ ውጤት ቀርተዋል። ገሚሶቹ ደግሞ፣ ለተወሰኑት ደንበኞች ብቻ ደካማ አገልግሎት ከማቅረብ ያለፈ አቅም አልፈጠሩም። ለምን? ያው፣ ቀላል አይደለም።
ታዲያ፣ የእስከዛሬው ታሪክ ሲታይ፣ ዛሬ ምን የተለየ ውጤት ይመጣል? እስከዛሬ ያተሳካው የሳተላይት ስልክና ኢንተርኔት፤… አሁን ተሳክቶለት በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓለምን ማጥለቅለቅ ይችላል? እነ ኢትዮቴሌኮምን ከገበያ ሊያስወጣ ይችላል?  አይመስልም እንል ይሆናል። ግን፣…
የአለማችን የቴክኖሎጂና  የቢዝነስ ፈጠራዎች፣… ተዓምረኛ ናቸው። ትንፋሽ በሚያሳጥር ፍጥነት፣ አገር ምድሩን ሲያዳርሱ፣ ታሪክን ሲቀይሩ አይተናል። ለዚያውም ፣ በተደጋጋሚ። የሳተላይት ስልክና ኢንተርኔትም፣ እንደዚያው፣ “ጉድ ነው፤ አዳኢብ ነው” ሊያሰኘን ቢችልስ? በተለይ ዘንድሮ፣ ስሙ እየገነነ፣ ዋና የዜና ርዕስ ሆኗል። በእርግጥ፣ ይሄ አዲስ አይደለም። ዛሬ ዛሬ እንደ አዲስ እየተወራለት ቢሆንም፣ ከ20 ዓመት በፊትም፣ ብዙ ተዘምሮበታል። ግን አልዘለቀም። ለምን?
የተወራለት ያህል ውጤታማ መሆን እየተሳነው፣ በኪሳራ ለመፍረክረክ፣ ዝናውም  ለመደብዘዝ ብዙ ጊዜ አልረጀበትም። የዛሬ 10 ዓመትም፣ ማይክሮሶፍት እና ለሌሎች ኩባንያዎች  ያፈሰሱለት የብዙ ቢሊዮን ብር ሃብት፣ ለፍሬ አልበቃም። የአብዛኖቹ ሙከራ፣ ያለ ውጤት መክኗል። ሃብታቸውም በኪሳራ ቀልጦ ቀርቷል።
የሳተላይት ስልክንና ኢንተርኔትን የማስፋፋት ህልም ግን፣ በዚያው ጠፍቶ አልቀረም። እንደገና ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ ዓለምን የሚያነጋግር ዜና ሆኗል። ለምን? “ስታርሊንክ” መጣ። ጊዜና  ቦታ የማይገድበው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት በመላው ዓለም ለማድረስ ነው፣ የስታርሊንክ  አላማ።  ለዚህም፣ ሳተላይቶችን እየሰራ ያመጥቃል። ግን፣ ሁለት ወይም  ሶስት፣ ሃያ ወይም ሰላሳ ሳተላይቶች በቂ አይሆኑም። እንደ ቴሌቪዢን ስርጭት አይደለም።
እና ምን ተሻለ? የስታርሊንክ ምላሽ፣ በርካታ ሺ ሳተላይቶችን አመጥቃለሁ የሚል ነው።
በርካታ ሺ ሳተላይቶችን ማምጠቅ? ለማመን ይከብዳል። በየዓመቱ ከሺ በላይ ሳተላይቶችን ማምጠቅ? ለዚያውም በአንድ አዲስ ኩባንያ? እስከ ዛሬ ያልታየና ያልተሞከረ ታሪክ ነው። ባለፉት 60 ዓመታ ውስጥ፣ ወደ ህዋ የተላኩ ሳተላይቶች፣ 10ሺ አይሞሉም። አገልግሎት የሚሰጡ ሳተላይቶች ቢቆጠሩ ደግሞ፣ 2 ሺ ብቻ  በነበሩበት  ወቅት ነው፤ የስታርሊንክ እቅድ የመጣው። በየዓመቱ፣ ቢያንስ ቢያንስ 1000 ሳተላይቶችን ማምጠቅ፣ እንኳን ለአንድ ኩባንያ ቀርቶ፣ ለመላው ዓለምም ይከብዳል። ያንን ሁሉ ሳተላይት ማን ይፈበርከዋል? ወጪውስ? በዚያ ላይ፣ የማምጠቂያ ሮኬቶች፣ ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚያገለግሉት። ብዙ ሚሊዮን ዶላር የፈሰሰበት ሮኬት፣ ከአንድ በረራ በኋላ፣ ተቃጥሎ ተሰባብሮ ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ሮኬት፣ ባለብዙ ሞተር ሃይለኛ ጄት አውሮፕላን እንደሆነ ልብ በሉ።
አንድ አውሮፕላን፣ አንድ ጊዜ መንገደኖችን አድርሶ፣ እንደ ፌስታል ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ተጥሎ ሲቀር አስቡት። ወጪው የሚቀመስ አይሆንም ነበር። የማምጠቂያ ወጪ እጅግ ውድ የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው።
የማምጠቂያ ሮኬት፣ እንደ አውሮፕላን እየተመላለሰ የሚያጓጓዝ መሳሪያ እስኪሆን ድረስ፣ የህዋ ጉዞ፣ በጣም ውድ መሆኑ አይገርምም።
ደግነቱ፣ ስታርሊንክ፣ በዘፈቀደ የተፈጠረ ኩባንያ አይደለም። የ”ስፔስኤክስ” ልጅ ነው። ስፔስኤክስ ደግሞ፣ አለምን ጉድ የሚያሰኙአዳዲስ የሮኬት ቴክኖሎጅዎችን የሚፈጥር ኩባንያ ነው። የህዋ ማምጠቂያ ወጪዎች፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በብዙ እጥፍ ቀንሷል። 10 ኪሎ ለማምጠቅ፣ 1 ሚሊዮን ዶላር ይፈጅ ነበር። አሁን ወደ 500ሺ ዶላር ቀንሷል። ቀስ በቀስም ወደ 100ሺ ዶላር ወርዷል።
በዚያ ላይ፣ የስፔስኤክስ ሮኬቶች፣ በአንድ በረራ ብቻ፣ ከአገልግሎት ውጭ አይሆኑም። ተመልሰው ያርፋሉ። ታድሰውና ተጠግተው፤ እንደገና ሳተላይት ተሸክመው ወደ ህዋ ያመጥቃሉ።
ይሄ፣ የህዋ በረራን የሚቀይር አዲስ ታሪክ ነው። የማምጠቂያ ወጪዎችን ለመቀነስ አስችሏል። በዚህም፣ የስፔስኤክስ ገበያ ደርቷል።
ግን፣ የሌሎች ኩባንያዎችን እቃ ከማምጠቅ  ጎን ለጎን፣ የራሱንም ሳተላይቶች “በገፍ” እያመጠቀ ነው። ማለትም የስታር ሊንክ ሳተላይቶችን።
እናም፣ የዛሬ ሁለት ዓመት፣ እንደ ህልም ይታይ የነበረው የስታር ሊንክ እቅድ፣ ለማመን ቢከብድም፣ ዘንድሮ በእውን መታየት ጀምሯል።
ለ2020፣ ስታሊንክ፣ በተከታታይ የሮኬት በረራዎች፣ ከ850 በላይ ሳተላይቶችን ለማምጠቅ የወጠነው እቅድ፣ እየተሳካለት ነው። ባለፉት 10 ወራት ውስጥ፣ ከ770 በላይ ሳተላይቶችን አምጥቋል። ምን አለፋችሁ። መለኛመሆኑ በጀው። አንደኛ ነገር፣ ርካሽ የማምጠቂያ ሮኬቶችን ፈጥሯል። ሳተላይቶቹም አዲስ ፈጠራ ናቸው። እንደ ካርቶን፣ በስርዐት ተደራርበው ሊቀመጡ የሚችሉ ስለሆኑ፣ ብዙ ቦታ አይፈጁም። ኩባንያው፣ በአንድ በረራ፣ 60 ሳተላይቶችን የሚያመጥቀውም፣ በዚህ ምክንያት ነው።
የእስከዛሬው ውጤት፣ አስገራሚ ስኬት ቢሆንም፣ ስታር ሊንክ “ገና መች አያችሁና? ገና እያሟሟቅኩ ነው” እንደሚለን አትጠራጠሩ። በየዐመቱ፣ ከሺ በላይ ሳተላይቶችን እየጨመረ፣ ዓለማቀፍ የሳተላይት ኢንተርኔትን ለማስፋፋት ሩጫውን እያፈጠነ ነው። እኛስ? አገራችንስ?
እንደ ሞባይልና እንደ ኢንተርኔት  ሁሉ፣ የሮኬትና የሳተላይት ቴክኖሎጂም፣ በአስገራሚ ፍጥነትና በአነስተኛ ወጪ እያደረገ የሚገሰግሰው፣ መንግስት ከቢዝነስ  ስራ ሲርቅ፣
ነፃ ገበያ ሲስፋና የግል ኩባንያዎች የመፎካከር እድል ሲኖራቸው ነው። ለዚህም፣ስፔስኤክስ እና ስታር ሊንክ የዘመናችን አርአያዎችና ምስክሮች ናቸው።
ኢትዮጵያ፣ በእስከዛሬ አካሄዷ፣ የኋሊት እንደቀረች ትቀጥላለች? ማንሰራራት ከፈለገች ግን፣ ገና የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎትን ለግል ቢዝነስ የመክፈት ከባድ ስራ አለባት።



Read 5581 times