Saturday, 14 November 2020 10:36

ምርጫ ማስፈፀም በአገረ አሜሪካ (የምርጫ ቀን ውሎ)

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት አሜሪካውያን ለ59ኛ ጊዜ መሪያቸውን መርጠዋል። የ78 ዓመቱ የደላዌር ሴናተርና የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት በሶስተኛው ሙከራ ተሳክቶላቸው በሀገሪቱ ታሪክ በዕድሜ የገፉ ተመራጭ ሆነዋል። በአንፃሩ ተፎካካሪያቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ውጤቱን ባለመቀበል፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እየዛቱ ይገኛሉ።
ለመሆኑ በየአራት አመቱ የሚካሄደው ምርጫ እንዴት ይከናወናል። የአንድ ምርጫ ጣቢያን ውሎ እንቃኛለን።
አስመራጭ
የምርጫ አስፈፃሚዎች ከተለያየ የሕብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ናቸው። ጡረተኛ ፖሊስ፥ መምህር፥ ዳቦ ጋጋሪ፥ የኮሌጅ ተማሪ፥ ሕንፃ ተቋራጭ፥ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች መኪና መንገድ አሻጋሪ፥ የማህበራዊ ግልጋሎት ሰራተኛ፥ ገንዘብ ያዥ፥ የምርጫ ቦርድ ባልደረባና የመሳሳሉትን ያካተተ ነው። እነዚህ ሰዎች ገለልተኛ መሆን አይጠበቅባቸውም። የተመዘገቡ የፓርቲ ደጋፊዎች ከሆኑ ግን ያንን ማሳወቅ አለባቸው። ፖለቲካዊ ተሳትፎን ለማበረታታት አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ለአስፈፃሚዎቹ እስከ ሁለት ቀን እረፍት ይሰጣሉ። አበል መከፈሉ ደግሞ ሌላው ማበረታቻ ነው።
ኬተንስቪል
ኬተንስቪል ከከተማ ወጣ ያለ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የሚኖሩበት፤ በአመለካከት ለዘብተኛ የሚባሉ ነጮች በቁጥር የሚያመዝኑበት፤ ሥነ ጥበብን ማድነቅና ወጥቶ መብላት ‘የገባው’ የሚያሰኝበት፤ በሜሪላንድ ግዛት የሚገኝ ሰፈር ነው። ዌስተርን ቴክ ተግባረዕድ ትምህርት ቤት የአካባቢው አንድ የምርጫ ማዕከል ነው። ከኮቪድ ወረርሽኝ በፊት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶቹ ይህንኑ አገልግሎት ይሰጡ ነበር። አሁን ለጥንቃቄ ሲባል ሰፋፊ የውስጥ ስፖርት ማዘውተሪያ ያላቸው የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተመራጭ ሆነዋል።
ጎበዝ በማለዳ
ማክሰኞ ማለዳ ከ11 ሰዓት ጀምሮ የምርጫ አስፈፃሚዎች በት/ቤቱ ተገኝተዋል። በይፋ ሥራ የሚጀመረው 11፡45 ነው። የምርጫ ካርዶች ያሉባቸውን ካርቶኖች እየከፈትን፣ በቁጥር ቅደም ተከተል እየደረደርን፣ በዛውም ሌሎችን እንጠብቃለን። የምርጫ ማካሄጃ ዘመናዊ መሳሪያዎች ሰኞ ማታውኑ ተገጥመው ጨርሰዋል። በዚህ ቀን ወንበርና ጠረጴዛ መደርደር፥ ቦታዎቹን ማዘጋጀት፥ የአካባቢውን ፅዳት መጠበቅ እንዲሁም የሥራ ክፍፍል ማድረግ ነው የሚቀረው። የምርጫ ጣቢያው ዋና ሀላፊ ሁሉም እንደ ፍላጎቱ እንዲሰማራ የተቻላትን አድርጋለች። ከዚህ በፊት በአስፈፃሚነት ያልሰሩትን እንደየ ሁኔታው ትመድባለች።
መራጮችን አራርቆ ሰልፍ ማስያዝ፤ የእፍ ጭምብል ማድረጋቸውን መቆጣጠር፤ ማንነታቸውን ከኮምፒተሩ መዝገብ ጋር ማመሳከር፤ ካርድ መስጠት፤ እያንዳንዱ ሰው በምስጢር ድምፅ የሚሰጥበትን ቦታ ወዲያው ወዲያው በመድሃኒት ማፅዳት፤ ካርዱ ድምፅ መስጫው ውስጥ ከመግባቱ በፊት አካሄዱን ማመሳከር፤ ዳቦ ፍለጋም ይሁን በሌላ ጉዳይ በምርጫው ቀን ኬተንስቪል እግር የጣላቸውን መራጮች ጊዜያዊ የድምፅ መስጫ ካርድ መስጠትና የመሣሠሉት የሥራ ክፍፍሎች ናቸው። እንደታዘብኩት ከሆነ አብዛኛውን ሰው መሥራት የሚፈልገው ለመቀመጥ ዕድል የሚሰጠውን ነው። ከሌሊቱ 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ረጅም ቀን በመሆኑ መቀመጥ የማይከጅል የለም። ለማንኛውም ግን በተራ በተራ የሚሰጥ ሁለት የ30 ደቂቃ እረፍት አለ።
የምርጫ ቦታው በዋናነት አምስት ክፍሎች አሉት። የመራጮች ማንነት የሚመሳከርበት፤ አዲስ መራጭ የሚመዘገብበት፥ ምርጫ ካርድ የሚሰጥበት (እንደ ሰው ፍላጎት - በእርሳስ ወይም በኮምፒውተር የሚሞላ ሁለት አይነት ካርዶች)፤ የመምረጫ ቦታ እንዲሁም ድምፅ ሳጥን ውስጥ የሚከተትበት ሥፍራዎች ናቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመርጡ ሰዎች ጭብጨባ ይደረግላቸዋል።
ሰዎች በተከለለ ሥፍራ ለብቻቸው የሚመርጡባቸው 13 ቦታዎች ተዘጋጅተዋል። አስሩ ካርዶቹን በእርሳስ የሚሞሉባቸው ሲሆን ሶስቱ ግን ምርጫቸውን በኮምፒውተር ማድረግ ለሚፈልጉ የተዘጋጀ ነው። የኮምፒተሩ ዘዴ ለአካል ጉዳተኞችም እንዲመች ተደርጎ የተዘጋጀ ሲሆን ብሬልና ማዳመጫ የተገጠመለት ነው። ይህ ፀሀፊ እዛ ላይ ተመድቦ ሲውል ሁለት አካል ጉዳተኛ ብቻ ነው ለመታዘብ የቻለው። የኮምፒውተሩ ትልቅ ጥቅም አንዱ ገፅ ላይ ምርጫ የተሰጠበት ሁኔታ ስህተት ካለው ወደ ተከታዩ መሄድ አይቻልም። ግለሰቡ የመረጣቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር የያዘው ካርድ፤ ከኮምፒውተሩ የሚወጣው ሁሉም ነገር ትክክል ከሆነ ብቻ ነው። በወረቀት ድምፅ የሚሰጡ ሰዎች፣ አልፎ አልፎም ቢሆን ስህተት ይሰራሉ። ኮምፒውተሩና ስህተት ግን አይተዋወቁም።
በእርሳስም ሆነ በኮምፒውተር የመረጡ ሰዎች፣ የድምፅ መስጫው ጋ በመሄድ ካርዳቸውን ሳጥኑ ላይ ባለው ስካነር በኩል ያስገባሉ። ኮምፒውተሩ ድምፁን ያነባል። የካርዱ ጥቅም ውዝግብ ቢነሳ ለመቁጠር ካልሆነ በስተቀር ስካን ሲደረግ መራጩ ለማን ድምፅ እንደሰጠ ኮምፒውተሩ ይመዘግባል። ውጤቱ ሊታወቅ የሚችለው ከምርጫው በኋላ ኮምፒውተሩ በሚዘጋበት ጊዜ በሚታተመው ማጠቃለያ ወረቀት ነው። ነገር ግን በፖስታ የተላኩት ካርዶች ከዚህ በተለየ ሁኔታ ነው የሚስተናገዱት። እነሱን መቁጠር የግድ ነው። የምርጫው ውጤት እስኪታወቅ አምስት ቀን የፈጀውም በዚህ ምክንያት ነው።
ዕጩዎች
በምርጫው ወቅት ጎላ ብሎ የሚታየው ለፕሬዚዳንትነት የሚደረገው ውድድር ቢመስልም በዛው ቀን የግዛቶች አስተዳዳሪዎች፤ ሴናተሮች፥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ የወረዳ ምክር ቤት ሊቀ መንበር፥ ከንቲባ፥ ዳኞች፥ የፖሊስ አዛዥ፥ የኦዲት ሀላፊ፥ ዋና የኑዛዜ መዝጋቢና ሌሎችም ይመረጣሉ። ይህ እንደ ግዛቱና እንደ ወረዳው አንዳንዴም እንደ ከተማው ህግና የአስተዳደር ባህል ይለያያል። በተጨማሪም በአንዳንድ አከራካሪ ጉዳዮች ላይ ሕዝበ ውሳኔ ይሰጣል። ለምሳሌ በዚህ አካባቢ የስፖርት ውርርድ ሕጋዊ ይሁን አይሁን፥ የወረዳ መስተዳድሩ ለፍሳሽ ማስወገጃና ተያያዥነት ያላቸውን ግንባታዎች ማካሄድ እንዲያስችለው የ200 ሚሊዮን ዶላር ቦንድ ሽያጭ ያከናውን ወይስ ይቅር የሚሉ ክርክሮች በዛው ቀን ድምፅ ተሰጥቶባቸዋል። ሩቅ ካለው ፕሬዚዳንት ምርጫ ይልቅ ለኗሪዎች አሳሳቢ የሚባሉት እንደነዚህ አይነት ጉዳዮች ናቸው። ቁማሩ ይፈቀድ የሚለው በርካታ ድጋፍ አግኝቶ አልፏል።
በነገራችን ላይ ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት ትራምፕና ባይደን ብቻ አልነበሩም። የሊበርታሪያን፥ የአረንጓዴ፥ የ‘ዳቦና አበባ’ ፓርቲ ዕጩዎች ነበሩ። አንድ ግዛት ላይ ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ የሆኑ ሰዎች ሌላ ቦታ መስፈርት ላያሟሉ ይችላሉ። ለምሳሌ ዘፋኙ ካኜ ዌስት በ12 ግዛቶች በተፎካካሪነት ቀርቦ ነበር። እጩዎቹ “ከዝንጀሮ ቆንጆ”  ለሚሆኑባቸው ሌላ እድል አለ። እገሌ ይሁንልኝ ብለው የፈለጉትን መፃፍ ይችላሉ። አንዱ ወዳጃችን ያደረገውን እናንሳ። ሜሪላንድ የተባለው ግዛት አፍቃሬ ዲሞክራት ነው። አስተዳዳሪው ግን ተወዳጅ ሪፐብሊካን - ያውም ሁለት ጊዜ የተመረጠ! ላሪ ሆገን ሪፐብሊካን በመሆኑ ብቻ ለትራምፕ ድምፁን መስጠት አልፈለገም። ስለዚህ በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ዝነኛ የነበሩትን ሮናልድ ሬገንን መርጧል። ሬገን በሞት ከተለዩ 15 ዓመት አልፏቸዋል።
መራጭ  - ውጣ ውረድ
ከማለዳው 12፡30 ጀምሮ መራጮች በት/ቤቱ ግቢ ተገኝተዋል። ምርጫው አንድ ሰዓት ላይ ተጀምሮ እስከ ሁለት ተኩል ድረስ ድምፃቸውን ሰጥተው ወደ ሥራ የሚሮጡ በርካቶች ነበሩ።
ከሶስት ሰዓት በኋላ ግን ሰዉ እየተንጠባጠበ ነው ሲመጣ የነበረው። ከመራጩ ሕዝብ ከግማሽ በላይ ቀድሞ በፖስታና በየጎዳናው ላይ በነበሩ ሳጥኖች ውሳኔውን አስመዝግቧል። ለዚህም ይመስላል ያን ያህል ብዛት ያለው መራጭ ያልነበረው። ለነገሩ ዘንድሮ በታሪክ ከፍተኛ የተባለ ከ150 ሚሊየን ሕዝብ በላይ እንደተሳተፈ ተገምቷል። አብዛኛው ድምፅ የተሰጠው ከምርጫው ቀን ቀደም ብሎ ነው።
ከ11 ሰዓት ጀምሮ ሰዎች እንደገና በብዛት መምጣት ጀምረዋል። ያም ሆኖ ለቁጥጥር የሚቸግሩ አልነበሩም። ምሽት ወደ 1፡30 የግል ታዛቢዎች ናቸው የተባሉ ሁለት ሰዎች መጥተው፣ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ቆይተዋል።
አሸናፊውን እናስታውቃለን
ምርጫው ሁለት ሰዓት ላይ ሲዘጋ አንድም መራጭ ት/ቤቱ ቅጥር ግቢ አልነበረም። የምርጫ ሳጥኖቹ አንድ በአንድ በዋናዋ አስፈፃሚ ተራ በተራ ሲዘጉ፣ የሽያጭ ወረቀት የሚመስሉ ረዣዥም ወረቀቶች ታትመው ይወጣሉ። እሱ ግድግዳ ላይ ይለጠፋል። ያ ማለት ኮምፒውተሩ ያወጣው የምርጫ ውጤት ነው። ድምፅ የሰጡ ሰዎች ብዛት፤ የትኛው ዕጩ ስንት ድምፅ አገኘ የሚሉት ዝርዝሮች ማጠቃለያው ላይ ታትመው ወጥተዋል። በኛ የምርጫ ጣቢያ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሸንፈዋል፤ አካባቢውን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደረችው ሪፐብሊካኗ የ38 ዓመቷ አፍሪካ አሜሪካዊ ኪም ክላሲች፤ የ72 ዓመቱን አንጋፋ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ ክዋሲ ምፉሚን አሸንፋለች። በኋላ በግዛት ደረጃ እንደታየው ግን ሁለቱም ተሸናፊዎች ሆነዋል። በምርጫው ቀን የተገኙት አብዛኞቹ መራጮች የሪፐብሊካን ደጋፊዎች እንደነበሩ በኋላ በተደረገ ጥናት ለማወቅ ተችሏል።
በአገረ አሜሪካ የምርጫ ቀን ውሎ ይህንን ይመስላል። አሁን አሳሳቢው ነገር፣ አበሉ እስካሁን አለመምጣቱ ነው።


Read 513 times