Tuesday, 10 November 2020 00:00

ጊዜና ጥንቃቄ!!

Written by  (ከወንድወሰን ተሾመ መኩሪያ፤ የማህበራዊ ሳይንስና የስነልቦና ባለሙያ)
Rate this item
(2 votes)

 (የህወኃት ጁንታ ሦስት ቦታ የተሳለ ሰይፍ ነው)
                           (ከወንድወሰን ተሾመ መኩሪያ፤ የማህበራዊ ሳይንስና የስነልቦና ባለሙያ)

          ኢትዮጵያ ከህውሃት ጁንታ ጋር የገባችበት የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ፣ የጊዜ ፍጥነትና ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው። ፍጥነቱ የሚያስፈልገው የህግ ማስከበር ስራው በዘገየ ቁጥር የሶስተኛ ወገን ፍላጎትና ጣልቃ ገብነት መጨመሩ አይቀሬ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ፍላጎትና ጣልቃ ገብነት አንድም አረመኔውን ጁንታ ለማዳንና የኢትዮጵያን ህመም ለማራዘም አሊያም የኢትዮጵያን ክፍተት በመጠቀም ለራሳቸው እኩይ ዓላማ የሚሰሩ አካላት በመኖራቸው ነው። በተጨማሪም ኦፕሬሽኑ በረዘመ ቁጥር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ መፍጠሩ የማይቀር መሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ጥንቃቄ ወሳኝ ነገር ነው። ጥንቃቄ፤ ኢትዮጵያ ያለችበትን አውድ በመረዳት ኪሳራን የሚቀንስ አደራረግን ወይም አሰራርን  መከተል ነው። ይህ ጥንቃቄ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ጸጥታውን በማጠናከርና ህዝብን በማሳተፍ የጎሉ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ሊተገበር የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡
ባለፈው ማክሰኞ  ህዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ፣ የህውኃት ጁንታ ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ያደረሰውን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ሲናገሩ እጅግ አዝነናል፤ ይህም ሳይበቃ በማይካድራ በንጹሐን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ መፈፀሙን ሰምተናል፡፡ የህውኃት ጁንታ ሦስት ቦታ የተሳለ ሰይፍ አለው!
አንደኛው የሰይፉ ስለት ሞራል የለሽ (moral insanity) መሆኑ ነው፡፡  “ትክክልና ስህተት” (right and wrong) ብሎ ማመዘን የለም፤ ቅንጣት ታክል የጥፋተኝነት ስሜት አይሰማውም (a complete lack of guilt) --- የanti-social personality disorder ወይም የpsychopathic inferiority ሰለባ ነው፡፡ ውሸትንና ክህደትን እንደ ውሃ ይጠጣል (repeated lying)፤ በሌላ ሰው ጫማ ውስጥ ሆኖ ማየት አይችልም፤ ጭካኔው ወደር የለውም፤ ያዋጣኛል ያለውን አስልቶ ያደርገዋል፡፡ (lack of empathy, remorselessness, and manipulative) ይህ ከባድ የሰይፉ ጫፍ ነው፡፡ የዚህ ሰብእና ቀውስ ሰለባ የሆኑ ግለሰቦችና ስብስባቸው መጠነ ሰፊ የሆነ ህመምና ስቃይ በህብረተሰብ ላይ ያደርሳሉ፤ ወንጀለኞች የምንላቸው ሰዎች ከሚያደርጉት ብልጫ ያለው ወንጀል ይሰራሉ (---cause a considerable amount of distress in society---the offending psychopath commits more offences than the average criminal)፡፡ ይህኛው የሰይፍ ጫፍ የህውኃት ጁንታ ለሚያደርገው ነገር ሁሉ ጋሻው ነው፡፡ ይሄ አስተሳሰብ መሬት ሲወርድ (ሲተገበር) የሚፈጥረውን ጉዳት ልብ ማለት ያስፈልጋል!
ሁለተኛው የሰይፉ ስለት የህወኃት ጁንታ ከራሱ ጋር በፍቅር የወደቀ መሆኑ ነው፡፡ በግሪክ የሚነገር አፈ ታሪክ አለ፤ ናርሲሰስ (Narcissus) የተባለ በውሃ ገንዳ ውስጥ ካየው ከራሱ ምስል ጋር በፍቅር የወደቀ ሰው ነበር፡፡ ራሱን መላልሶ መላልሶ በማየት ፍቅር ይጠመዳል፤ ከዚህ መላቀቅ ያቃተው Narcissus ተስፋ በመቁረጥ ለሞት እንደተዳረገ ይነገራል፡፡ የህውኃት ጁንታ በራሱ ፍቅር ወድቋል፡፡ ሰው ራሱን ብቻ ሲመለከት ከራሱ ውጪ ያለውን ማየት አይችልም፡፡ አድራጊና ፈጣሪ እሱ ብቻ ነው። ችሎታ ያለው፤ የማይሳነውና  ጀግናው ራሱና ራሱ ብቻ ነው፡፡
Narcissus ታዲያ አንድ የሰብዕና ቀውስ አስተዋውቆናል፡፡ Narcissistic personalities ይባላል ወይም ናርሲዝም ልንለው እንችላለን፡፡ ባህርያቱን እንያቸው፡- ከመጠን በላይ የሆነ ለራስ የሚሰጥ ግምትና አፈፃፀም(inflated sense of personal worth and accomplishment)፤ “ልዩ ነኝ” የሚል እምነት (convinced of their own uniqueness)፤ ሌሎችን የሚቀበሉት “ልዩ እና አዋቂ” መሆናቸውን እስካወደሱና እስከተቀበሉ ድረስ ብቻ መሆኑ (---Contempt and value others only so long as they serve as an admiring audience for the narcissistic personalities’ apparent brilliance and genius )፤ የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለማሳካት የተጠመዱ መሆናቸው፤ “ከኔ የሚሻል የለም” የሚል አስተሳሰብ ሰለባ ናቸው። በዚህም ምክንያት ምክር አይሰሙም፤ ራሳቸውን የበላይ እስካላደረጋቸው ድረስ ውይይትን አይቀበሉም፤ “እኔ፣ ለእኔ፣ በእኔ፤ ከእኔ” የሚል ስግብግብነት የተጠናወታቸው ናቸው፡፡ ይህ ቀውስ ከምን ይመነጫል? አንዳንዶች እንደሚሉት (Kernberg, 1975 and Kohut, 1977)፤ ከፍተኛ የሆነን የዝቅተኝነት ስሜትና የዋጋ ቢስነት ስሜትን ከመከላከል የሚመነጭ የማንነት ቀወስ ነው፡፡ --these theorists argue that the narcissistic person’s grandiosity and sense of entitlement are actually a defense against underlying feelings of inferiority and worthlessness.  ይህ እንግዲህ ጥልቅ ከሆነው ዋጋ ቢስነት ስሜት ለመውጣት ሲባል፣ ከፍተኛ ያልተገባ ዋጋ ለራስ ከመስጠት ጋር የሚያያዝ ነው። በነገራችን ላይ የዚህ ቀውስ ሰለባዎች ከፍተኛ የሆነ ትኩረት የመፈለግ ነገር ይታይባቸዋል፤ ጭር ሲል አይወዱም። ስለ እነሱ እንዲወራ፤ ስለ እነሱ እንዲነገር ይፈልጋሉ--ይህ ጠባያቸው ---attention seeking grandiosity ይባላል፡፡
ይህ የህውሃት ጁንታ ሁለተኛው የሰይፍ ስለት ቀላል አይደለም፡፡ “ያበጠ ይፈንዳ”፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል”፤ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ”  ከሚሉ አገራዊ አባባሎች ከአሉታዊ ገፅታቸው ጋር ከፍተኛ ዝምድና አለው፡፡ ይህንን ስነልቦና የተጎናጸፈ ግለሰብም ይሁን ቡድን የሚያጠፋው ጥፋት ወደር የለውም፡፡ ምክንያቱም ጭካኔ የተሞላበት ድርጊትን ለመፈፀም ድፍረት አለው፤ ለሱ ያልሆነ ማንኛውም ነገር ለሌላው እንዳይሆን ያደርጋል፡፡
የህውሃት ጁንታ ሶስተኛው የሰይፉ ስለት  ወደ ኒኮሎ ማካቬሊ ይወስደናል፡- ኒኮሎ ማካቬሊ የፃፈው The Prince የተሰኘው መጽሐፍ፣ በዓለም ላይ ብዙ አምባገነኖችን አፍርቷል፡፡ ሥልጣን ላይ እንዴት መውጣት እንደሚቻልና ሥልጣንን ዝንተ ዓለም ተቆጣጥሮ መቆየት እንዴት እንደሚቻል የሚያስረዳ ትውልድ ገዳይ መፅሐፍ ነው፡፡ ለአብዛኞቹ የአፍሪካ መሪዎች ይህ መጽሐፍ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም እንደ ቁራን እለት ተእለት የሚያሰላስሉትና የሚተገብሩት ነው ይባላል፡፡ ከዚህ ትምህርትና እውቀት የሚመነጨው የአስተሳሰብ ብልሹነት ማካቬሊዝም ሲባል፣ የቀውሱ ሰለባ የሆኑት ሰዎች ማካቬሊያንስ ወይም ማካቬሊስትስ ይባላሉ፡፡ ባህርያቱን እንያቸው፡- የሚያደርጉት ነገር ለእነሱ የሚጠቅም መስሎ ከታያቸው አይናቸውን ሳያሹ ያደርጉታል፤ ውጤቱ ለእነሱ ሥልጣን መራዘም የሚጠቅም ከመሰላቸው ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፤ አንድን ሰው ለማጥፋት  ከፈለጉ ሰውየው የሚኖርበትን ሙሉ መንደር  ሊያወድሙ ይችላሉ፤ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” የሚለውን መርህ ይከተላሉ፡፡ ይህ ቀውስ ውጤትን እንጂ ሂደትን አያይም፤ ሂደቱ ለሚፈጥረው የሞራል ጉዳት፤ የህይወትና የንብረት ውድመት ደንታ የለውም፡፡ ይህ ቀውስ ድርጊቱ የሚፈጥረውን ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ሳይሆን ጉዳቱ ለግለሰቡ ወይም ለቡድኑ የሚያመጣለትን ጥቅም ብቻ የሚያይ ነው። ይህ የህውኃት ጁንታ ሶስተኛው የሰይፍ ስለት ማንንም አይምርም፡፡
ይህ በመቀሌ የመሸገው የህውኃት ጁንታ ሶስቱንም የተሳሉ ጫፎች በአንድነት ስለሚጠቀም “ውጤት ያስገኝልኛል” ብሎ ካሰበ “የራሴ” በሚላቸው ወገኖቹም ላይ ሳይቀር የማይጠበቅ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፤ እያደረሰም ነው፡፡
በአዲስ አበባ፣ በክልል ከተሞች (በመቀሌ ከተማ ጭምር) በሰው ልጅና በንብረት ላይ አሳፋሪ የሆነ ዘግናኝ ጥፋትና ውድመት ሊያደርስ እንደሚችል ግንዛቤ ተወስዶ፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አገሩንና ወገኑን ለመታደግ የሚችለውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ለምን ከተሞችን ይመርጣል? አንዱ ምክንያት ትኩረት ያለባቸው ስፍራዎች ስለሆኑ ነው (ናርሲስት መሆኑን ልብ ይሏል)! መንግስትም በጥንቃቄና በጥበብ ከጊዜ ጋር መሮጥ ይጠበቅበታል፡፡
በመጨረሻም ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ፣ የህውኃት ጁንታ ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ያደረሰውን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት በቴሌቪዥን መስኮት በገለፁበት ማክሰኞ ዕለት፣ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፌስ ቡክ ገፃቸው እንዲህ ብለዋል፡- “ስግብግቡና አረመኔው የመቀሌ ጁንታ በሰሜን ኮማንድ አባላት ያደረሰውን ኢ-ሰብአዊ ግድያ፣ ግፍና በደል መቼውንም አንረሳውም፡፡ ይህ ጁንታ ለፍትህ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት ሳያገኝ ለአፍታም ቢሆን አናርፍም፡፡
አሁንም ደግሜ ለኢትዮጵያውያን ላረጋግጥላችሁ የምወደው የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራችን ሳይጠናቀቅ ከዚህ ጁንታ ጋር ድርድር እንደማይኖር ነው።” ከጁንታው ባህርይ ወይም ጠባይ አንፃር ጠ/ሚኒስትራችን ትክክለኛውን መንገድ መርጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከጭካኔ አሰራርና ከኢ-ፍትሃዊነት፤ ከፖለቲካ አሻጥርና ከጎሳ ፖለቲካ ነፃ ሆና፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በነፃነትና በብዙ ተስፋ የሚያሳድጉባት አገር እንድትሆን ለማየት ከሚናፍቁት ወገን ነኝ!
ድል ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1701 times