Print this page
Saturday, 14 November 2020 11:06

ካርል በም እና ዘምዘም ገርቢ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

ጀርመናዊው ሕፃን ካርል ሀይንትዝ በም በመጋቢት ወር 1921 ዓ.ም ሲወለድ፤ ካርልን በ19 ዓመት የምትበልጠው ኢትዮጵያዊቷ ጉብል ዘምዘም ገርቢ፤ በአዲስ አበባ አራዳ ገበያ፣ አረቦች ከውጭ ሀገራት የሚያስመጡትን ሰሀንና መሰል ሸቀጣ ሸቀጥ ተቀብላ በመቸርቸር ትተዳደር ነበር። ልጅ ካርል ሀይንትዝ በም ዕድሜው ለትምህርት ደርሶ ሥነ ጥበብ፣ ታሪክና ትወና ከተማረ በኋላ በፊልም ተዋናይነት ሥራ ላይ ተሰማራ፡፡ በልጅነቷ የመማር ዕድል ያላገኘችው ዘምዘም ገርቢ፤ትዳር መሥርታ በተሰማራችበት የንግድ ሥራ ቀጠለች፡፡
ወጣቱ ካርል የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶችን እያማረጠ ሲማር፤ የዘምዘም ሀገር ኢትዮጵያ፣ ዘመናዊ ትምህርትን በማስተዋወቅ ላይ ነበረች፡፡ በስዊስ ተወላጁ በአልፈሬድ ኤልግ .ቤት የተጀመረው ዘመናዊ ትምህርት፤ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተሻግሮ፣ ዘርፉ ለማደግ ዳዴ እያለ ነበር። ባለፉት 110 ዓመታት ዘመናዊ ትምህርትን ለሕብረተሰቡ ለማዳረስ መንግሥት ካደረገው ጥረት ጎን ለጎን፣ የተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና የግለሰቦችም ሚና ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ ለዚህ እውነታ ካርል ሀይንትዝ በም እና ዘምዘም ገርቢ አንዱ ማሳያ ናቸው፡፡        
ካርል በተሰማራበት ሙያ በበርካታ ፊልሞች ላይ ተሳትፏል፡፡ በመቀጠል ወደ በጎ አድራጎት ሥራ ገባ፡፡ የ‹‹ሰዎች ለሰዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት›› መሥራችና ባለቤት የሆነው ካርል ሀይንትዝ በም (በጤናና ትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ)፤ ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ  ከ400 በላይ ትምህርት ቤቶችን በመሥራት የሀገርና የሕዝብ ባለውለታ ነው፡፡
መንግሥት ያስጀመረውን ዘመናዊ ትምህርት፣ ታች ወዳለው የሕብረተሰብ ክፍል ለማድረስ አቅደው ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉት ኢትዮጵያዊያን መሐል ዘምዘም ገርቢ ተጠቃሽ ናት፡፡ በአራዳ ገበያ በችርቻሮ ንግድ ሥራ የጀመረችው ዘምዘም ገርቢ፤ በመርካቶም በንግድ ሥራዋ በመቀጠል ከቀድሞ ዘመን የመርካቶ ባለሀብቶች አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ ዘምዘም በነጋዴነት ብቻ ሳትወሰን ዘመን ተሻጋሪ ተግባርም አከውናለች፡፡ የትውልድ መንደሯ የክስታኔ ጉራጌ ልጆች ዘመናዊ ትምህርት የሚያገኙበት ትምህርት ቤት የመሥራት እቅድ ነድፋ፣ አማውቴ በሚባለው አካባቢ በ1964 ዓ.ም ምኞቷ እውን ሆኗል፡፡
*    *     *
ጀርመናዊው ካርል ሀይንትዝ በም (ከ1928 – 2014 እ.ኤ.አ) እና ኢትዮጵያዊቷ ዘምዘም ገርቢ (ከ1902 – 1992 ዓ.ም)፤ የምድር የኮንትራት ቆይታቸውን አጠናቀው አልፈዋል፡፡ በሕይወት ዘመናቸው ያኖሩት አሻራ ግን እነሱ ባይኖሩም ሥምና ታሪካቸውን እያስጠራ፣ ትውልዱንም እያስተሳሰረ ከትላንት ወደ ዛሬ ተሻግሯል። ባለፈው እሁድ ጥቅምት 29 ሁለቱ ባለታሪኮች በሌሉበት ሥምና ገድላቸው የታወሰበት መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡      
‹‹ሰዎች ለሰዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት›› 7 ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ ብር በማውጣት ለዘምዘም ገርጎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሰራቸው የመመሪያ ክፍሎች በተመረቀበት መርሐ ግብር ላይ፣ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ወክለው የተገኙት ዶ/ር አስናቀ ወርቁ ባደረጉት ንግግር፤ ‹‹ሰዎች ለሰዎች›› በ1981 ዓ.ም መመሥረቱን፣ ከበጎ አድራጎት ሥራዎቻቸው ውስጥ ሰባ ከመቶ (70%) የሚሆነውን ለትምህርት እንደሚያውሉ፣ እስካሁን 450 ትምህርት ቤቶችን መሥራታቸውን አመልክተው፤ ‹‹በዚህ ዘርፍ ከመንግሥት ቀጥሎ ትልቁ የእኛ ሥራ ነው፡፡ እኛ ይህን ሠርተን ስናስረክባችሁ ጠብቆና ተንከባክቦ ወደተሻለ ደረጃ የማድረሱ ኃላፊነት የመንግሥት፣ የባለሀብቱና የሕብረተሰቡ ነው›› ብለዋል፡፡
መርሐ ግብሩን በምርቃት ካስጀመሩ የሀገር ሽማግሌዎች አንደኛው፣ የልማት ሥራን በተመለከተ የአካባቢው ተወላጆች ያደረጉትን አስተዋጽኦ ሲገልጹ፤ ‹‹እኛ ተጠቃሚ የሆንነው  የዓለም ገና ወላይታ ሶዶ መንገድ ከተሠራ ዕለት ጀምሮ ነው፡፡ በመንገድ የተጀመረው ሥራ ወደ ትምህርት አድጎ፣እማሆይ ዘምዘም ይህንን ትምህርት ቤት አቋቋሙ›› በማለት ሲያመሰግኑ፣ ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ ትላንትን ከዛሬ ጋር በማነጻጸር፤ ‹‹የድሮ ሰዎች ያለ ብዙ ገንዘብ፣ ያለ ብዙ ዕውቀት፣ ያለ ምንም ክልከላና ገደብ … መንገድና ትምህርት ቤት እንደሠሩልን ሁሉ፤ ዛሬ የተሻለ ዕውቀትና ገንዘብ ስላለ፣ ከተማራችሁና ባለሀብት ከሆናችሁ ልጆቻችን ከፍ ያለ ትብብርና የልማት ሥራዎችን እንጠብቃለን›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ አደረጃጀት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሺሸማ ገብረሥላሴ፣ የጉራጌ ባህልና ልማት ኮሚቴን በመወከል ባደረጉት ንግግር፣ ከጉራጌ ዞን ከወጡ ታላላቅ ሴቶች አንዷ እማሆይ ዘምዘም ገርቢ መሆናቸውን በአድናቆት ገልጸው፣ በ1950ዎቹ የጉራጌ ተወላጆች ለልማት ሥራ በአንድነት ተሰልፈው ያስመዘገቡትን ታሪክ አንስተዋል፡፡ ‹‹በጄነራል ይልማ ሽበሺ የሚመራው ኮሜቴ ከዓለም ገና ወላይታ ሶዶ፤ በጄነራል ወልደሥላሴ በረካ የሚመራው ደግሞ ከዓለም ገና ሆሳዕና በሁለት አቅጣጫ የተሠራው የልማት ሥራ፣ አባቶቻችን እርስ በእርስ በመደጋገፍና በመፎካከርም ትልቅ ውጤት ያስገኙበት ነበር፡፡ ጅምሩን ማሳደግ የሚያስችል አወቃቀርና ሀብትም ማፍራት ጀምረው ነበር፡፡ … የጉራጌ ባህልና ልማት ማኅበር፣ የአባቶቻችንን ጅማሬና ምኞት ማስፈጸም ዓላማ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው›› ብለዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል በበኩላቸው፤ የጉራጌ ማሕበረሰብ ለኢትዮጵያ አንድነት ትልቅ ዋጋ የከፈለ መሆኑን፣ ይህ ትግልና ምኞቱ እውን ሊሆን የሚችለው ትልቅ ሀገርና ሕዝብ ሲኖር ነው ብሎ እንደሚያምን፣ የጉራጌ ሕዝብ ያሉበትን ችግሮች መቅረፍ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ እንዳሉ፣ ለዚህም ተግባራዊነት ትምህርት ቁልፉ ጉዳይ መሆኑን … በንግግራቸው አመለከቱ፡፡ የሶዶ ወረዳ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይ ፈንታ ደግሞ፤ ለዘምዘም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን ሠርቶ ያስረከበው ‹‹ሰዎች ለሰዎች በጎ አድራጎት ድርጅት››ን አመስግነው፤ ቢሯቸው ሊሰራ  ካሰባቸው በርካታ እቅዶች አንዱና ዋነኛው የትምህርት ዘርፉን ማስፋፋትና ማሻሻል መሆኑን ገለጹ፡፡
የክስታኔ ጉራጌ ሕዝብ ልማት ማኅበርን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ ቦጋለ ደምሴ በበኩላቸው፤ ማኅበራቸው ከተመሠረተ 27 ዓመታት ቢያስቆጥርም በአዲስ መልክ መንቀሳቀስ ከጀመረ 13 ዓመት እንደሆነው ጠቁመው፤ ልማት ማኅበሩ የቡኢ ሪፈራል ሆስፒታል፣ ቴክኒካል ኮሌጅ፣ የጢያ ባህል ማዕከልን በማሰራት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን፣ ከዚህም በተጨማሪ የክስታኔ ጉራጌ ጎርደና ሥርዓትን የማስጠናት፣ ክስታንኛ-አማርኛ- እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት አዘጋጅቶ የማሳተም፣ በጉራጌ ዞን በየዓመቱ ዘላቂ መሆን የቻለው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንዲጀመር ምክንያት መሆኑን ገለጹ፡፡
በአካባቢው ዛሬም ብዙ ልጆች የትምህርት ዕድል እንዳላገኙ ያመለከቱት አቶ ቦጋለ ደምሴ፤ ዕድል ያገኙትም በተለያየ ምክንያት የሚያቋርጡ መሆናቸውን ሲገልጹ፤ ‹‹ጥቂት ለማይባሉ ልጆች ምን መሆን ትፈልጋላችሁ የሚል ጥያቄ አቅርቤላቸው፣ ብዙዎቹ ኢንጅነርና ዶክተር የመሆን ፍላጎት እንዳላቸው ነግረውኛል፡፡ እንዲህ ዓይነት ምኞት ያላቸው ልጆች የሚረዳቸው በማጣትና በልጅነት ወደ ትዳር እንዲገቡ በመደረጉ ምክንያት ትምህርታቸውን እያቋረጡ በመሆኑ ከተባበርን የልጆቹን ችግር ልንቀርፍላቸው እንችላለን›› ብለዋል፡፡
‹‹ሰዎች ለሰዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት››፣ ለዘምዘም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን እንዲሠራ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ የሚነገርላቸው ደጃዝማች ግዛው ቢራቱ ባደረጉት ንግግር፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቱን አመስግነው፣ ከተባበርን ከዚህም በላይ መሥራት እንችላለን ብለዋል፡፡
ዘምዘም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገኝበት አማውቴ ግፍትጌ አካባቢ፣ በቅርቡ የታዳጊ ከተማነት ዕውቅና ማግኘቱን የጠቆሙት ከንቲባው አቶ ሙሉነህ ፈቃዱ፤ ከተማውን ለማሳደግ ለመኖሪያ፣ ለንግድና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውል ቦታ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ጀርመናዊው ካርል ሀይንትዝ በም እና ኢትዮጵያዊቷ ዘምዘም፣ በተዘከሩበት በዚህ መርሐ ግብር ላይ በዕለቱ ለተመረቀው ትምህርት ቤት 22 ሰዎች በጋራ 25 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ የገዟቸውን መጻሕፍት አበርክተዋል፡፡ ደብተሮችና ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶችም በስጦታ ቀርበዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ 50ኛ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን ለሚያከብረው ዘምዘም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ የቀድሞ ተማሪዎች ከወዲሁ ዝግጅት መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡
ዛሬ በህይወት የሌሉት ሁለቱ ባለታሪኮች (ካርልና ዘምዘም)፤ አኑረው ባለፉት ሥራ፣ ሀገርና ሕዝብን አስተሳስረው፣ ትውልድና ሀገር ቀጣይ መሆን የሚያስችላቸውን ጡብ ማኖራቸው የተመሰከረበት መርሃ ግብር ነበር - ያለፈው እሁድ ዝክር፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1790 times