Monday, 16 November 2020 00:00

አለም የተስፋ አይኖቿን ፋይዘር ላይ ጥላለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለወራት ቁም ስቅሏን ስታይ የከረመቺው አለማችን ከሰሞኑ ከወደ አሜሪካ በሰማችው መልካም ዜና ተስፋ አድርጋ፣ ነገን በጉጉት መጠበቅ ጀምራለች፡፡
የአሜሪካው ፋይዘር እና የጀርመኑ ባዮንቴክ ኩባንያዎች በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ ባደረጉት መረጃ፣ 90 በመቶ ሰዎችን በኮሮና ቫይረስ ከመያዝ የሚታደግ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ማግኘታቸውን እንዳስታወቁ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ሁለቱ ኩባንያዎች ለወራት ምርምር ያደረጉበትን ክትባት በአሜሪካ፣ ጀርመን፣ ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ደቡብ አፍሪካና ቱርክ በሚገኙ 43 ሺህ 500 ሰዎች ላይ መሞከራቸውንና ውጤታማነቱን ማረጋገጣቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ እስካሁንም ክትባቱ በተሞከረባቸው ሰዎች ላይ ምንም አይነት አሳሳቢ የጤና ችግር አለመከሰቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
ክትባቱ እስከ መጪው ህዳር ወር መጨረሻ ጥቅም ላይ ይውላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ 50 ሚሊዮን ያህል ክትባት እንደሚያቀርቡ እና በ2021 የፈረንጆች አመት ደግሞ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ክትባቶችን እንደሚያመርቱ ኩባንያዎቹ ማስታወቃቸውንም አመልክቷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን 300 ሚሊዮን ክትባቶችን ለመግዛት ለኩባንያዎቹ ጥያቄ ማቅረቡን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ በቅድሚያ ክትባቱን የሚያገኙት እነማን እንደሆኑ የሚወሰነው ክትባቱ በሚቀርብበት ጊዜ የሚኖረውን የቫይረሱ ስርጭት ሁኔታ እና ክትባቱ የበለጠ ውጤታማ የሚሆነው ለማን ነው የሚለው ታይቶ እንደሚሆንም አመልክቷል፡፡
ፋይዘር ኩባንያ ተስፋ ሰጪውን ክትባት በተመለከተ በይፋ መግለጫ መስጠቱን ተከትሎ፣ ኩባንያው በአለም ገበያ ያለው ዋጋ በ9 በመቶ ያህል ከፍ ከማለቱ በተጨማሪ በወረርሽኙ ሳቢያ ለወራት ተቀዛቅዞ የቆየው የዓለም ገበያ እንደ አዲስ መነቃቃት መጀመሩም ተነግሯል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ አለማቀፉ የአክስዮን ገበያ ከአውሮፓውያኑ የ2008 የዓለም የገንዘብ ቀውስ ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ መቀነሱን ያስታወሰው የቢቢሲ ዘገባ፣ የክትባቱ መልካም ዜና መሰማቱን ተከትሎ ግን በተለያዩ የአለማችን ገበያዎች መነቃቃት መታየቱንና ተስፋ ሰጪ ክትባቶች መበራከታቸውን፣ በቀጣይም የአለም አቀፍ ገበያው ከዚህ በበለጠ ሊያድግ ይችላል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁሟል፡፡
ፋይዘር ባለፈው ሰኞ ስለክትባቱ መግለጫ መስጠቱን ተከትሎ፣ ሩስያ ደግሞ ስፑትኒክ 5 የተሰኘውና ሲያወዛግብ የነበረው ክትባቷ 92 በመቶ ውጤታማ መሆኑን ይፋ አድርጋለች፡፡


Read 4275 times