Saturday, 14 November 2020 11:31

"ራምኑን"

Written by  በአፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(8 votes)

 ስትሄድ እንደማያት አታውቅም። አቅፊያት ናፍቃኝ እንደማስባት አታውቅም ... ሌንቦዋን የከንፈሬን ወዝ እየቀባሁ፣ የአንገቷን ምዑዝ ጠረን ስምግ፣  ከዚያ ካፌ ውስጥ ሰው ሁሉ እንደሚያየን ትረሳለች። በሃዘኔ ውስጥ ስትገኝ ሩሄን እንደምትኩል ይጠፋታል። በመከፋቴ ጉንጭ ላይ  ጨዋማ ፈሳሽዋን እንደ ምንጭ ስታፈስ ፍፁም እናትነት ያጠላባት ነች። ከራሴ በላይ እንደዋለች «እኔ» ነች። ከሷ  በላይ  እንደዋልኩ «እሷ» ግን አይደለሁም።
ያጮለቀችበት የኑረቴ ፉካ ፀሊም መሆኑን አታውቅም። ልቤ ከመቃብር ድንጋይ የከበደ መሆኑን ትክዳለች።  በፍቅር ሑረቷ ሳንካ እንደሆንኩ ልብ አትልም።  እንደ እሳት ከሚጋረፍ አካልዋ፣ እንደ ማንም ከማይሆን ሴትነቷ ውስጥ የሚፈልቅ ቅዱስ ማይ አለ።  ይህንንም አታውቅም። በዚያ ጠፍታ በቀረችበት ጥሻ ዝምተኛ ነች። ትኩረት ያቸልለች ናት። ህፃን በሚያስመስላት የዋህነቷ  እንደ መላዕክ ነጭ ልብ አላት። ትንቧቸርበት ልቤ ግን ጨለማ እንደሆነ አታውቅም።  አወቅኩ ባለችው ነገር ላይ ብዙ እንደማታውቅ በመረዳቷ ውስጥ፣ ውዥንብር ሃሳዊ ኅልዮ እንዳለ አታውቅም።
አንዳንዴ መውደዴን ሳላውቅ፣ አንዳንዴ ማፍቀሬ ሳይገባኝ ... ትላንቴ ላይ እንደተዘመረ፣ ንፋስ እንደነካው ጉም ጠይምነቷ ላይ ተበትኜ ህቡዕ እስክሆን ድረስ ... ፍቅርን እረሳለሁ። ያኔ ጥልቅ ሰላም ይሰማኛል።  ልማዴን እቀዳጃለሁ።
በዝምታ ታየኛለች። አጠገቤ ሆና ክንዴን ታቅፋው ዝም ስትል መናገር  የፈለገችውን እረዳለሁ።  ትውውቃችን ደርዝ  አልባ ነው። ዝምታችን ቋንቋችን ነው።  በቃላት ሽንቁር አምልጠው የሚሰሙ ስሜቶች አልነበሩም። ቃላት ደካማ ናቸው። ፍቅርን ለመግለፅ አይችሉምና ... እውነትን ለመንገር ምርኩዝ እንደ ’ሚሹ አይነት ናቸውና ... ዝምታ ብዙ እንደሚናገር አውቃለሁ። ቅንራቶች (1) ይህን ይክዳሉ።
ስትሄድ ግን አሁንም እንደማያት አታውቅም። በመውደዴ መስክ ላይ  ስውር እራስ ወዳድነቴን አታይም። እንደ ማንም መክፋቴን ክዳ ከመልካምነት  አምባ ስታውለኝ፣ ነገዬን መተንበይ  እንደማትችል እረዳለሁ። ያካሄድ ዳናዋን ተከትዬ ጥቁር ትውስታ ላይዋ እንደማደምቅ ... ጣፋጭ ማይ ያዘነበ ከንፈሯን ሃሞት ነው ብዬ እንደምክድ አታምንም።
ላወራ አፌን ስከፍት ክንዴን በእጆቿ ተጭና ዝም  እንድል ነገር ... ልናገር የምችለውን ስለምታውቅ እንድናገር እንዳልፈለገች ... በሃሳቤ ውስጥ ስለምትኖር መከፋቷ እንዳስከፋኝ  ብታውቅ...
ያልጎደለ ማወቅ እንደሌለ ብነግራት “ኩሸት” ነው ስትል ጣርያ ገንጣይ ሳቅ ትስቃለች። እውነቴን በሳቋ ክርታዝ እንደምትጠቀልለው ... ገመናዬን  ደባቂ ናት። እንከን አልባ አድርጋ ሰው ፊት ስታቀርበኝ ድክመቴን እያወቀች ነው።
አንገቴ አቀርቅሮ ማየት አትሻም። ሃዘኔ እንባዋን ከአይኗ ሲጨምቅ አይቻለሁ።  መሰበሬ አሽመድምዶ የሚጥላት ናት። አውቃታለሁ። ስከፋ፣ በዚያ በኖርኩበት ብቻነት ይሉት ጫካ ውስጥ ደብዝዤ ስማስን   መሄጃ እንደምታጣ አውቃለሁ።
ውጪ ሄዶ የመማር እድሏን እንደሰረዘች ነገረችኝ። ልንለያይ አንችልም አለች። ለሰከንድ ተራርቀን መቆም እንደማንችል ነገረችኝ። አንድ ጋት እንኳን ለየፊናችን የማንራመድ መሆናችንን  ልታሳየኝ  የፍቅሯ ግዛት ውስጥ ያለ መለየት ህግ ደነገገች።
ስህትት እንደሰራች ባውቅም ልወቅሳት አልፈለኩም። እንደዛሬው ተደብታ ስትመጣ እጄን ዘርግቼ እቀበላታለሁ። ብዙ ነገር ሲጦርፋት፣ ከእንባዋ  መታገል ሲያደክማት፣ ሲቃዋን አልችል ስትል  ትመጣለች። ዝም ብላ ታቅፋኝ በእንቅልፍ ሰመመን ለመጥፋት ትለፋለች። ቤተሰብ ወቅሷታል። እድሏን በመግፋቷ፣ ስንቱ ተስሎ ያጣውን እድል እንደ ቀልድ ይቅር ማለቷ . . .
...ደስታዋ የዝምታ ወሰን አይገታውም። የተዘጋ  ቤቴን በሳቋ እያንኳኳች . . . "ክፈት አንተ” ትላለች። የማነበውን መፅሐፍ  ወዲያ ከግድግዳ ጋር አላትማ፤ “ይሄን ዝብዝብ መፅሐፍ ማንበብ ብተውልኝስ"
ፍቅሯን የሚቀናቀን ይመስላታል።  በዚህ  ግዑዝ  የምታጣኝ ይመስላታል። መፅሐፎቼን እንደ ጣዉንት ስታያቸው እታዘባለሁ።
[ከእኔ ፍቅር የፕሌቶ ’ሪፐብሊክ’  ይበልጣል?] እንደ መሳቅ እየቃጣች።
[ከጂብራን ’ነብዩ’ የእኔ ከንፈር አይበልጥም]  አለንጋ ጣትዋን ላሁጭ ፀጉሬ ውስጥ  ልካ . . .
[የብርሃኑ ሶስቱ ማዕበሎች እኔን ይስተካከላሉ?]
[ከሆሄ አልበልጥም... ከቃል -  ከሃረግ - ከስነ- ፅሁፍ አልመጥቅም? ከፍልስፍና አልረቅም?]
“አቤት...”
“ምናባህ” ጉንጬን ትቆነጥራለች...
[እንዳንተ አይነት የፍቅር ጀዝባ ግን ይወደዳል]
ሃሃሃሃ.....
አሁንም ስትሄድ  በሃሳቤ ቃኘኋት። ከሌላው ቀን በበለጠ እንደተረበሽች ባውቅም “እቅፍህ ነው የሚያረጋኝ ጌትዬ” ስትል የንግግሯ እውነትነት በሚያረጋግጥ አይነት ፈገግ አልኹ። እውነት እንዳልሆነ ግን አውቅ ነበር።
ጠይም  ክብ ፊቷ ላይ ትልልቅ ዓይኖች አሉ። ወፋፍራም ከንፈሮቿን ገልጠው ብልጭ የሚሉት ጥርሶቿ፤  ኩል ከመሰለ ሰማይ ላይ እንደሚያበሩ ከዋክብት ናቸው። ፀጉሯን አሳጥራ ትቆረጣለች። ከጆሮዋ አልፈው እንዳይወርዱ የምትጠነቀቅ ትመስል ... ያን ጎራድ አፍንጫ አነፍንፋ ከሲጋራ ጠረኔ  ጋር ስትጋጠም “ለምናባህ ነው አልተው ያልከኝ...” አኩርፋ ጀርባዋን ስትሰጠኝ ነገር...
እየጎዳውኅት እንዳለ አሰብኹ። ለእኔ ብላ የተወችውና የቻለችው እልፍ ነው። ከጓደኞቿ  ሽሙጥ እስከ ትምህርት እድሏ ... ከቤተሰቧ ትዕዛዝ እስከ ምንትሷ . . .  ይህ ሁሉ የሚገባኝ አልነበርኩም።   እንደሚረብሸኝም አታውቅም። ቅር እንደሚያሰኘኝ ይጠፋታል። ለእኔ ብላ ያጣችው ነገር፣ እኔ የነጠቅኳት እንደሆነ ልነግራት እፈልግና ከዝምታ ውጪ የምተነፍሰው አይኖረኝም።
በቀስታ ስማኝ  ተነስታ ስትሄድ ጀርባዋን አያለሁ። ህብረ ቀለማት ነቁጥ ነቁጥ ሆነው አጭር ቀሚሷ ላይ ፈሰዋል።  ...ቦርሳዋን አንጠልጥላ ... ተረብሻለች! በአፏ ግን ስክነቷን ስትሰብክ ... ምናልባት መረበሿ አልገባት ይሆናል።
[•••]
ከአሳደገኝ ድርጅት ስወጣ በእንጨት ሞያ ሰልጥኜ ነበር። አንዳችም የምቀርበው ሰው አልነበረም። ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ጓደኛ ... በህይወቴ ውስጥ ምንም ናቸው። ከብቸኝነት ጠለል እራሴን  ገድቤና ከልክዬ ከምኖርበት ዓለመ-ፅልመት ውስጥ ደስታ ነበረኝ።  ጨለማዬን እወደዋለሁ፣ ባዶነቴ ማንም የማይነጥቀኝ ማንነቴ ነበር።  ደስታው ቀልጦ፣ ፅልመቱ  ደፍርሶ ብርሃን ሲሆን ... በራምኑን ተዓምረኛ ዓይን  ለፍቅር እጁን ሰጠ። የከንፈሯ ምትሃት እድሜዬን ከገነባሁት ቅጽር ጎትቶ እንዳወጣኝ ሃይል ነው። ማፍቀር ስጀምር መጥላትን ተማርኩ (በእርግጥ ማፍቀር ስለመቻሌም አላረጋገጥኩም)። በጥላቻ ያደጉ ሰዎች ከማንም በላይ ፍቅርን ያውቃሉ። አስከፊነቱን አይተዋልና፤ አጥፊነቱ ይረዳሉና ... ከጨለማ ውጪ ብርሃን እንዳለ ስረዳ፣ መረዳቴ ቅዠት መሆኑን ሳልመረምር በሙሉ ልብ ተቀበልኩት።  ሰላም ነበረኝ። ደስታም ነበረኝ። አሁን ግን ባለመድኩት ዓለም ውስጥ የምውተረተር   ፈሪ ሆኛለሁ።
ሰላሜን እንደነሳች አታውቅም። መውደዴ «እኔ» እንዳልሆነ አታውቅም።
• • •
ስትሄድ እንደማትመለስ አውቃለሁ። ከዚህ በላይ ልጎዳት እንደማልችል እያሰብኩ ነበር። እኔን በመውደዷ እኔን የመሆን፣ ኑሮዬንም የመምሰል ግዴታ የለባትም።  ከአርባ ቀን  የብቻነት እድሌ ጋር  ትግል ትገጥም ዘንድ  አልፈቅድም።
ጥሩ ኑሮ እንደሚገባት አውቃለሁ። ፀዳል ልቧ የተሻለ ልብ ይፈልጋል። የተሻለ ፍቅር፣ የተሻለ ሰው የሚገባት ነች። መለያየት እንዳለብን ስነግራት ከሷ በተሻለና በቀረበ መንገድ የምወደው እንዳለ ምክንያት አድርጌ ነው! አላመነችም። እንባ ባቀረረ አይኗ ፍዝዝ ብላ አየችኝ።  
“ዋሽተኸኛል!” አለች።
“ማንም የለህም እኮ...” ሳግ ተናነቃት...
ብዙ ልሰማት አልፈለኩም። ከንፈሯን ስሜ ተነሳሁ። ከተቀመጥንበት ካፌ ውስጥ ብቻዋን ተውኳት... ብቻዋን ለቀቅዃት...ብቻዋን! አዎ፤ በእርግጥም ብቻዋን ነበረች።
ከየአካባቢው የሚሰማው ጅግግታ የጆሮዬን ቆሬ ያደበያል። ከጭጋጋም ሰማይ ላይ ቂቢብ ያለች ግማሽ ጨረቃ የቀድሞው ውበቷ ደብዝዟል። ነፋሻማ አየር ይሰግራል። ጅስሜ ቅዝቅዝ እንዳለ ነው።
አስባለሁ!
ብቻዋን ጥያት ስሄድ ሰው መሃል እንደምታፍር፣ መራቄም እንደ ዝሆን ሀሞት መሪር እንደሚሆንባት  አውቃለሁ።
የዓይኗ ብርሃን ከልቤ እንዳጣበቃት ናጥራን ነው።
•••
አሁን አሁን  በቤቴ በኩል ስታልፍ ወደኔ ታማትራለች። በመስኮት በኩል  ከማዶ ሰፊው አውራ መንገድ ስቃኝ፣ አንገቷን  አዙራ ለሰከንድ ወደ ቤቴ ታያለች። አንዳንዴ  ወደ’ኔ ለመምጣት ትልና ተመልሳ የመጀመሪያ  መንገዷን ትቀጥላለች።
ልቧን እውነቷ ላይ  አንብራ አካልዋን እንዳራቀች ተረዳሁ። መለየት እስኪያጠጋጋን ተቀራርበናል ... መራቅ እስከማንችል መውደድ አያሻም።
...ብዙ ነገሮች እንደ ፉርጎ ተቀጣጥለው ይነጉዳሉ። ብዙም ነገሮች ይገታሉ። ሁሉም ነገሮች ማለቂያ አላቸው - ሁሉም ነገሮች ጅማሬ አላቸው።  ውልደታችን  ከሞት  ተዛንቋል። ፍቅር ከመለየት ተሰናስሏል።
አሁንም አንገቷን መልሳ፣ ከመንገዷ ተግ ብላ ቤቴን ትቃኛለች።
***
1 ኩራተኞች
[ቁርጥራጭ ገፆች]
[መልዕክተ ራምኑን ወደ ተባዕት (ዘመን)]
ካንቺ በበለጠ የምወደው አለ ሲለኝ ደማቅ ዋሾ መሆኑን አውቃለሁ። ከእኔ ውጪ ሰው እንደሌለው፣ የኔንም ያህል የሚቀርበው እንደሌለ አውቅ ነበር።  በሰው የተከበብኩ ብቸኛ ነኝ። በቤተሰብ፣ በዘመድ፣ በጓደኛ  ሽምጥ አጥር ውስጥ የምገኝ  ሰው አልባ። ችግሬን ያለ ቃል ይረዳል። ደስታዬ ያለ እሱ እንደማይሞላ ያውቃል። የእኔ የምላቸው ያለ እሱ የሉም። አፋራም ሴትነቴ  ሳይገድበኝ በግድ የቀረብኩት ነኝ። ለመጀመርያ ጊዜ ቀጥሬው ሲቀር፣ በሁለተኛም በሶስተኛም..ቤቱን አጠያይቄ ደፉ ላይ በሩን ስቆረቁር አላፈርኩም። ሁሌም በመፅሐፍ ገፅ መከለልን ይመርጣል - ዘመን። ፈሪ ነው። ገሃዱን ዓለም ስለሚፈራ በንባብ ይደበቃል።
ከ’ሱ በላይ የወደድኩት የለም። ከሱ ውጪም መውደድ የምችል አይመስለኝም። ደብዳቤ ልፅፍለት አስባለሁ። ወደ ስራ ስሄድ በበሩ በኩል ሳልፍ ገብቼ ላናግረው እሻለሁ...አንድ ነገር አንቆ የያዘኝ ይመስል አልቻልኩም። እንደ  በፊት ሲያቅፈኝ አልማለሁ። እንደ ድሮው እንዲስመኝ ’ፈልጋለሁ። እውኔም ቅዠቴም ሆነ።  መለየቴ አልገታኝም ይልቅ ይበልጥ እንድቀርበው አደረገኝ ... እሱን ብዬ ያላጣሁት ምን አለ? ለ’ሱ ብዬ ያልተውኩት፣ ለ’ሱ ብዬ ያልሰዋሁት ፍላጎቴ የለም።
የሃቅ ፍቅርን አያውቅም። የእውነት መውደድ አይገደውም። ከብቻነቱ ዋሻ ሲወጣ ከባህር እንደ ወጣ አሳ እስትንፋሱን የሚነጠቅ ይመስለዋል። እራስ ወዳድ ነው። ፈሪም ጭምር። አሁን ድረስ  ቤቱን አማትራለሁ። አሁን ድረስ እቅፉን እናፍቃለሁ። ከንፈሩን አልማለሁ። ቅዠቴም እውኔም ሆኗል።
አዎ፤ በእርግጥም ቅዠቴም እውኔም ነው።


Read 2232 times