Saturday, 14 November 2020 11:52

ማቆ እና አራት ጓደኞቹ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በአንድ ሀገር  በጣም ድሀ የሆኑ ባልና ሚስቶች ነበሩ፡፡ ማቆ የሚባል ልጅም ነበራቸው፡፡
ማቆ እናቱን በጣም ይወዳል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን እናቱ በጣም በጠና ታመሙ፡፡
ሀኪም ቤት ተወስደው የታዘዘላቸው መድሃኒት ዋጋ ደሞ አምስት መቶ ብር ይፈጅ ነበር፡፡
የአባቱ ደሞዝ ዝቅተኛ ስለሆነ ያንን ያክል ገንዘብ ማግኘት አልቻሉም፡፡ በየዘመድ ወዳጆቻቸው ቤት እየዞሩ እርዳታ በመጠየቅ ያጠራቀሙት  250 ብር ብቻ ሆነ፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ ማቆ ለእናቱ ህክምና ስለ ጎደለው 250 ብር አብዝቶ ይጨነቅ ጀመር፡፡
በእረፍት ሰዓት አራት ጓደኞቹ ኳስ ሲጫወቱ፣ እሱ ከዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብሎ የሚያስበው ስለ ሁለት መቶ ሀምሳ ብሩ ነው፡፡ ከጭንቀቱ  ብዛትም ወደ ፈጣሪው ቀና ብሎ በሚያሳዝን ዜማ…
“የጎደለን ገንዘብ ሁለት መቶ ሀምሳ
የፈጠርካት አምላክ እናቴ አትርሳ……” እያለ ይፀልይ ነበር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ትምህርት ቤት ሲማር…..ሲማር…..ሲማር…. ቆይቶ ወደ ቤቱ ሲመለስ አብረውት ከነበሩት ጓደኞቹ አንዱ መሬት የወደቀ ገንዘብ አገኘ፡፡ ገንዘቡን አንስተው ሲቆጥሩት 250 ብር ነው፡፡ ከመካከላቸው አንዱ፤ “እንግዲህ እኛ አምስት ስለሆንን ለመከፋፈል አያስቸግርም፡፡ ሃምሳ ሃምሳ ብር ይደርሰናል…..” አለ፡፡
ገንዘቡን ከተከፋፈሉም በኋላ “ዛሬ ደስ የሚል ቀን ነው….. በገንዘባችን አብረን እየዞርን የሚጣፍጡ ምግቦችን እንበላለን….በተረፈውም ፕለይ ስቴሽን የተባለውን የኮምፒውተር እግር ኳስ እንጫወታለን” ተባባሉ፡፡
ማቆ ግን በዚህ ሃሳብ አልተስማማም። “አይ እኔ መብላትም መጫወትም አልፈልግም፡፡ ድርሻዬን ወስጄ ለናቴ ብሰጣት ይሻላል!” አለ፡፡
ጓደኞቹም ማቆን በጣም ስለሚወዱት “ግዴለህም ያንተን ድርሻ ለእናትህ ውሰድላቸው …… እኛ ጓደኞችህ ግን ስለምንወድህ ጭንቀትህ እንዲቀልልህ ስለምንፈልግ … ከኛ ድርሻ አዋጥተን አብረኸን ጣፋጭ እንድትበላና ፕለይ ስቴሽን እንድትጫወት ጋብዘንሃል!” አሉት፡፡
ማቆ መጀመሪያ “ስለ ግብዣው አመሰግናለሁ ግን አሁኑኑ ሃምሳ ብሩን ይዤ  ወደ እናቴ ብሄድ እመርጣለሁ” ብሎ ሊለያቸው ፈልጎ ነበር፡፡ አራት ጓደኞቹ ግን “አይ….. ገና 200 ብር ስለሚጎድልህ አሁኑኑ ብትሄድ የምትፈጥረው ነገር የለም፡፡ ይልቅ ከኛ ጋር ተዝናና…..” ብለው አግባቡት፡፡
በዚህ ዓይነት አስደሳች ሁናቴ ገንዘቡን ከጨረሱ በኋላ ማቆ አራቱን ጓደኞቹን አመስግኖ ተለያቸው፡፡  ምንም ያልተነካችውን የሱን ሃምሳ ብር ይዞም እየሮጠ ወደ ቤቱ ገሰገሰ፡፡ ሃምሳ ብሩንም ከእናቱ አልጋ አጠገብ ትክዝ ብለው ለተቀመጡ አባቱ የሰጣቸው በከፍተኛ ደስታ ተሞልቶ ነበር፡፡
“ሃምሳ ብር ጨመረ - ሃምሳ ብር ጨመረ
ከእንግዲህ በኋላ ሁለት መቶ ብር ቀረ…..”  እያለ ብሩን ሰጣቸው፡፡
አባቱም ቅዝዝ ባለ ስሜት ገንዘቡን ከየት እንዳመጣ ጠየቁት፡፡ ማቆም ታሪኩን ከመነሻው እስከ መጨረሻው ተረከላቸው፡፡ አባቱም በጣም አዘኑ፡፡ ከሃዘናቸው ብዛትም በሚያሳዝን ዜማ፡-
“አምስት መቶስ ሞልቷል
አምስት መቶስ ሞልቷል
ምን ዋጋ አለው ታዲያ - ግማሹ ተበልቷል….”
ብለው አለቀሱ….
ማቆም በአባቱ ለቅሶ በጣም ከመረበሹ የተነሳ በሚያሳዝን ዜማ…
“የኛን 500 ፈጣሪ ከሞላው……
ንገረኝ አባዬ -  ግማሹን ማን በላው….”
ብሎ ጠየቃቸው፡፡
አባቱም የማቆን ራስ እያሻሹ እንዲህ አሉት፡-
"ልጄ ማቆ …. ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የእናትህ መታመም ከዚህ ቀደም የነገርኩህ አንድ ወዳጄ ትንሽ ገንዘብ አግኝቻለሁና … ወደፊት ሰርተህ የምትከፍለኝ ከሆነ …. የጎደለህን 250 ብር ላበድርህ እችላለሁ ብሎ ጠራኝ፡፡ እኔም ሄጄ ያንን ገንዘብ ተቀበልኩ፡፡
"ከደስታዬ ብዛትም ፈጣሪዬን እያመሰገንኩ እናትህን ቶሎ ሀኪም ቤት ለማድረስ ስጣደፍ …. ስሮጥ ስጣደፍ… ስሮጥ ለካስ ያንን 250 ብር መንገድ ላይ ጥዬው ኖሯል፡፡ አንተና ጓደኞችህ አግኝታችሁ ያጠፋችሁት ብርም የናትህ መታከሚያ ነው- ልጄ" ብለው  ነገሩት፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማቆ መሬት ወድቆ ያገኘውን ገንዘብ ለባለቤቱ መመለስ እንጂ የኔ ነው ብሎ ማጥፋት ትልቅ ጥፋት መሆኑን ተገነዘበ ይባላል፡፡
     (ከታገል ሰይፉ "የእንቅልፍ ዳር ወጎች" የልጆች መጽሐፍ፤ ሐምሌ 2012)

Read 1598 times