Saturday, 21 November 2020 09:47

በትግራይ ክልል የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም ክትትል እየተደረገ ነው ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

   በትግራይ ክልልና አጎራባች በሆኑ አካባቢዎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አስታወቀ።
ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም የተቋቋመውና በትግራይ ክልልና አጎራባች አካባቢዎች ውስጥ በሚኖሩ ዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም ቁጥጥርና ክትትል የማድረግ ኃላፊነት የተሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ከትናንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተለይም ከህዝብ ደህንነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ ነው።
የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ እንደተናገሩት፤ መርማሪ ቦርዱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል የተባሉ አካባቢዎች ድረስ በመሄድ የማጣራት ስራ እንደሚሰሩና የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል ለሚመለከታቸው አካላት ሃሳብ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል። ቦርዱ በሰብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ አካላት ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል::
በአዋጁ የተገለጸው የቦርዱ የስራ ወሰን በትግራይ ክልልና አጎራባች አካባቢዎች መሆኑን የገለጹት አቶ ለማ፤ የመርማሪ ቦርዱ ግብረ ሃይል የትግራይ ክልል አጎራባች በሆኑ የአማራና የአፋር ክልል አካባቢዎችም ተያያዥ የሆኑ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን የመቆጣጠርና የመከታተል ሃላፊነት እንደተሰጠው ጠቁመዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የሚወሰዱ እርምጃዎች ኢ-ሰብአዊ እንዳይሆኑ መቆጣጠር የቦርዱ ዋነኛ ተግባር መሆኑን የጠቆሙት ሰብሳቢው፤ የሚወሰዱት እርምጃዎች ኢ-ሰብአዊ መሆናቸውን ሊያምንበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሚኒስትሮች ም/ቤት እርምጃውን እንዲያስተካክሉ ሃሳብ መስጠትና  ኢ-ሰብአዊ ተግባር የፈፀሙትን ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ ለቦርዱ የተሰጡት ኃላፊነቶች እንደሆኑ ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን ተከትሎ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም መቋቋሙ ይታወሳል።


Read 904 times