Saturday, 21 November 2020 09:54

በኮንሶ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ዜጎች ለከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ተዳርገዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

7 ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል

            በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞንና በአካባቢው ባሉ ወረዳዎች ታጣቂዎች ባደረሷቸው ተከታታይ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና 7 ቀበሌዎች መቃጠላቸውን ለአዲስ አድማስ የጠቆሙ ምንጮች፤ ሲሆን በደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ፤ ጥቃት አድራሾቹን ለመያዝና ሁኔታውን ለመቆጣጠር የፀጥታ ሃይል በአካባቢው መሰማራቱን አስታውቋል፡፡
በኮንሶ ዞን ስለተፈጠረው ሁኔታ ለአዲስ አድማስ የገለጹት ነዋሪዎች፤ ከአንድ  ሳምንት በፊት ጀምሮ በአካባቢው ማንነታቸው በውል የማይታወቅ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃቶች መፈጸማቸውን በጥቃቱም በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን 7 ቀበሌዎች ሙሉ መንደር መውደሙንና ነዋሪዎች ወደ ጫካ ለመሸሽ መገደዳቸውን  እንዲሁም  ጥቃቱ ወደ ተፈጸመባቸው  አካባቢዎች መግባት ባለመቻሉ የበርካታ ሰዎች አስክሬን ቀባሪ ማጣቱንና ገሚሱ መቃጠሉን አስረድተዋል።
ተከታታይነት ባለው ጥቃት  የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸው የተጠቆመ ሲሆን የመንግስት ተቋማት መዘረፋቸውንና መቃጠላቸውን፣ ባንኮችም መዘረፋቸውን  ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡
የጥቃቱ መነሻ አዲስ በተዘረጋው መዋቅር የመገን ህዝቦች  ዞን ተብሎ ይጠራው ፈርሶ ኮንሶ ራሱን የቻለ ዞን ከመሆኑና ከወሰን ጉዳይ ጋር  ሊይዝ እንደሚችል ግምታቸውን  እንዳላቸው የገለፁት ምንጮች፤ በአካባቢው  መሰል ችግር መከሰት ከጀመረ መሰንበቱንና በመከላከያ ጣልቃ  ገብነት ሰከን ብሎ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡
 የመከላከያ ሰራዊት ከሰሞኑ ከአካባቢው መውጣቱን ተከትሎ ግን ታጣቂዎች   ወደ ዞኑ ዘልቀው ጥቃት መፈጸማቸውንና እስከ ሀሙስ ድረስ ይኸው ጥቃት በተለያዩ ቀበሌዎች  ቀጥሎ  መዋሉን አስረድተዋል።   በአካባቢው ያለው የክልሉ ልዩ ሃይልና የፌደራል ፖሊስ ጥቃቱን ለማስቆም ጥረት እያደረጉ መሆኑን ያመለከቱት  ምንጮች፤ ጠቁመዋል፡፡ መንግስት ጥቃቱን እንዲያስቆምላቸው መማጸናቸውን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ  በበኩሉ፤ ችግሩ መከሰቱን አረጋግጠናል፤ የፀጥታ አካላት ሁኔታውን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው ብሏል፡፡

Read 1095 times