Saturday, 21 November 2020 09:55

ለእጩ ተወዳዳሪዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ የአየር ሰአትና አምድ ድልድል ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  - የግል መገናኛ ብዙኃን ብሮድካስት በሚያወጣው መመሪያ ይመራሉ- ተብሏል።
          - ማንኛውም መገናኛ ብዙኃን የምርጫ ዴስክ የማቋቋም ግዴታ አለበት

                የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩ ተወዳዳሪዎች የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምና ድልድል ረቂቅ መመሪያ ያዘጋጀ ሲሆን መመሪያው ለፖለቲካና እጩ ተወዳዳሪዎች የአየር  ሰዓትና  የጋዜጣ አምድ የሚደለደልበትን ዝርዝር መስፈርት አስቀምጧል።
ማንኛውም የህዝብ መገናኛ ብዙኃን ለእጩ ተወዳዳሪዎች የአየር ሰአት ወይም የጋዜጣ አምድ መስጠት ግዴታው ነው የሚለው መመሪያው፤ በክፍያ ማስታወቂያ መልዕክታቸውን ማስተላለፍ የሚፈልጉ  ፓርቲዎችም የሚስተናገዱበት ሁኔታም ተደንግጓል በረቂቅ መመሪያው።
ቦርዱ የአየር ጊዜና የጋዜጣ  አምድ የሚደለደለው ፓርቲም በሚወዳደሩበት የፌደራልና የክልል ም/ቤቶች  የሚያቀርባቸውን የእጩዎች ብዛት፣  በስራ ላይ ባሉት የፌደራልና ክልል ም/ቤት ፓርቲዎች በያዙት የመቀመጫ ፣ብዛት ፓርቲዎች  በሚያቀርቡት የሴት እጩ ተወዳዳሪዎች ብዛት እንዲሁም  የአካል ጉዳተኞች እጩዎች ብዛት መሰረት በማድረግ  መሆኑን በረቂቅ መመሪያው አመልክቷል። ለሁሉም በእኩል የሚደላደልበት ሁኔታም እንደሚኖር በረቂቁ መመሪያ ተመልክቷል።
በዚህ መሰረት ለምርጫ የሚወዳደሩ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተመደበው ጠቅላላ የአየር ጊዜ እንዲሁም የጋዜጣ አምድ  ሃያ አምስት በመቶውን በእኩል ይከፋፍላሉ ተብሏል።
በፌደራልና በክልል ም/ቤቶች  በያዙት መቀመጫዎች ብዛት ደግሞ  5 በመቶውን  ይከፋፈላሉ ይላል ረቂቅ መመሪያው። በሴቶች እጩ ተሳትፎ  ውስጥ  20 በመቶ እንዲሁም በአካል ጉዳተኞች  ተሳትፎ ደግሞ 10 በመቶ የሚከፋፈሉ ሲሆን ትልቁ የአየር ሰአትና አምድ ክፍፍል  የሚያቀርባቸውን እጩዎች ብዛት ታሳቢ ያደረገው ነው። በዚህ መስፈርት መሰረት 40 በመቶውን የአየር ሰአትና አምድ ይከፋፈላሉ ይላል - ረቂቅ መመሪያው።
የአየር ሰአትና የአምድ ድልድሉም ቦርዱ በሚያወጣው እጣ ይከፋፈላል ተብሏል። አንድ ተወዳዳሪ የተመደበለትን የአየር ሰአትም ሆነ አምድ ካልተጠቀመው ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ተወዳዳሪ ሊጠቀምበት  እንደማይችል የሚደነግገው አንቀጽም ተጠቃሽ ነው። ተወዳዳሪው ባልተጠቀመው የአየር ሰአት ወይም አምድ መገናኛ ብዙሃኑ የራሱን ፕሮግራም ሊያስተላልፍ ይችላል ተብሏል።
በግል ባለቤትነት የሚተዳደሩ  መገናኛ ብዙሃን ምርጫ ነክ መልዕክት  ለማስተላለፍ ስለሚመድቡት የአየር ሰአትና የጋዜጣ አምድ ድልድልና አጠቃቀምን በሚመለከት  የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ልዩ መስፈርቶችን በማውጣት ይወስናል ተብሏል።
የድምጽ መስጫው ቀን አራት ቀን ሲቀረው በመገናኛ ብዙሃን የሚደረገው የምረጡኝ ቅስቀሳ እንደሚቆምም ተገልጿል።
ማንኛውም መገናኛ ብዙሃን በተቋሙ የምርጫ ዴስክ ማቋቋም እንዳለበት የሚደነግገው ረቂቁ መመሪያ፣ የምርጫ ዴስኩም የምርጫ ነክ መልዕክቶችን ተቀብሎ ማሳተም ወይም ማሰራጨት እንዴት የተወዳዳሪዎች መልዕክት እንደሚያስተላልፍ የቴክኒክ መስፈርቶችን አውጥቶ የሚያሳውቅ፣ ከተወዳዳሪዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ተቀብሎ በመመርመር ውሳኔ የሚሰጥ እንዲሁም በሪፖርተሮችም በእጩዎች የሚቀርቡ መልእክቶች ይዘት ግጭት ቀስቃሽ አለመሆናቸውን ገምግሞ የማስተላለፍ ሃላፊነቶች ይኖሩታል ተብሏል።


Read 6818 times