Saturday, 21 November 2020 09:56

“በህወኃት የተፈጸመው ወንጀል በአለማቀፍ ህግ ያስቀጣል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ዶ/ር ደብረፅዮን ለትግራይ ህዝብ የክተት ጥሪ አስተላልፈዋል

             የማይካድራው የንጹሃን ጭፍጨፋን ጨምሮ በህወኃት ቡድን አቀናባሪነት ቀጥተኛ ተሳትፎ ባለፉት ሁለት አመታት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙ ጭፍጨፋዎችና ማፈናቀሎች በዓለም አቀፍ ህግ ጭምር ተጠያቂ የሚያስደርጉ እንደሆኑ የገለፀው  መንግስት እስካሁን 192  የህወኃት ባለስልጣናት፣ የመከላከያ መኮንኖችና የደህንነት አባላት በሃገር ክህደትና ሌሎች ተደራቢ ወንጀሎች ተጠርጥረው እየታደኑ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በማይካድራ የተፈፀመው የንጹሃን ጭፍጨፋ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ከተፈፀሙት   ወንጀሎች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ያስገነዘበው መንግስት፤ በሁሉም ጭፍጨፋዎች የህወሃት አመራሮች ተጠያቂዎች እንደሚሆኑ ገልጿል “በህዋኃት መሪነትና አቀናባሪነት የተፈፀሙት የንጹሃን ጭፍጨፋዎች በኢትዮጵያም ይሁን በዓለም አቀፍ ህግ የሚያስጠይቁ ከባድ ወንጀሎች ናቸው መንግስት የድርጊቱን ፈፃሚዎች በሙሉ ለፍርድ ከማቅረብ አያመነታም ብሏል፡፡  የእስር ማዘዣ የወጣባቸው የህዋኃት አመራሮች በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን እንዲሰጡና ተጨማሪ ግፍ ከመፈጸም በመታቀብ የመጨረሻዎቹን እድሎች  እንዲጠቀሙበት ጥሪ መቅረቡን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ማጣሪያ አመልክቷል፡፡
የሃገር ክህደት ወንጀልን ጨምሮ በተደራራቢ ወንጀሎች የሚፈለጉ የህወሃት ባለስልጣናት፣ የመከላከያ መኮንኖችን የደህንነት አባላት ቁጥር 192 የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 64 የህወኃት ባለስልጣናት፣ 108  ከሌተናል ጀነራል ጀምሮ እስከ ሻለቃ ያሉ ወታደራዊ መኮንኖች እንዲሁም 20 ያህል  የደህንነት አመራሮች  መሆናቸውም ታውቋል፡፡
 እስከ አሁን ለታጠቁ ሃይሎች ሚስጥር በማካፈልና ለመንግስት የተሳሳተ መረጃ በመስጠት በሀገር ላይ ክህደት በመፈፀም የተጠረጠሩ 20 የደህንነት አመራሮች መታሰራቸውም ታውቋል፡፡
ፅንፈኛው የህወሃት ቡድን በዜጎች ላይ በርካታ ግፎችን ፈፅሟል ያሉት የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቀነአ ያደታ፤ ቡድኑ የብሄር ግጭቶች ማስነሳቱንና በርካታ ህዝብ እንዲጨፈጨፍ ማድረጉን፣ የዜጎችን ሰብአዊ መብት መጣሱንና ጦርነቱንም ራሱ ሰሜን እዝን በማጥቃት መጀመሩን ሰሞኑን ለውጭ ሃገር ዲፕሎማቶችና ለወታደራዊ አዛዦች በሰጡት  ማብራሪያ አስገንዝበዋል፡፡ በመንግስት እየተከናወነ ያለው ኦፕሬሽንም የመጨረሻ ግቡ፣  ህግ የማስከበርና አጥፊዎችን ከያሉበት ለቃቅሞ ለህግ የማቅረብ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የብልጽግና ፓርቲ ሰሞኑን ለህወኃት አመራሮች ባቀረበው ጥሪ፤ በአስቸኳይ እጃቸውን  በመስጠት  ህዝብን ከእንግልት፣ ራሳቸውንም ከአጉል ውርደት እንዲያድኑ መክሯል፡፡
የህወኃት ቡድን እየደረሰበት ባለው ሽንፈት ከፍተኛ መዳከምና የመፈረካከስ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል ያለው የብልጽግና ፓርቲ፤ ቡድኑ ከተለያዩ የመግለጫ ጋጋታዎች ተቆጥቦ ህዝብ እንዳይንገላታ እጁን እንዲሰጥ ጥሪ አቅቧል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዞር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው፤የመከላከያ ሰራዊቱ በትግራይ እያከናወነ ያለው ኦፕሬሽን ወደ መጠናቀቁ መቃረቡን ጠቁመው የህወሃት ቡድን ቤተ ክርስቲያኖችን  ምሽግ አድርጎ እየተዋጋ መሆኑን ተናግረዋል ይህም መከላከያ ቤተክርስቲያንን በጥይት መታ ብሎ ለመክሰስ ታልሞ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ያለን ፕሮፌሽናል ሰራዊት በመሆኑ ይህን አያደርግም ወንጀለኛውን ቡድን በልዩ ተልዕኮ እንይዘዋል ብለዋል፡፡ ይህ በእዚህ እንዳለ የህወኃት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው በሰጡት መግለጫ፤ “የብልጽግና ሰራዊትና የኤርትራ ወታደሮች የትግራይን ህዝብ እየጨፈጨፉ ነው” ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጦርነቱ በልዩ ሃይል በሚሊሻ ብቻ ማድረግ የማይቻልበት ደረጃ ደርሷል ያሉት ዶ/ር ደብረፅዮን፤ የትግራይ ህዝብ ይህንን ወራሪ ሃይል በመዋጋት ነፃነትህን አስከብር የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የፌደራል መንግሰት በአየር ድብደባ በትግራይ ህዝብ ላይ ጭፍጨፋ እያካሄደ ነው ሲሉ ከሰዋል ዶ/ር ደብረፅዮን። በሌላ በኩል የአየር ሃይል አዛዥ  ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ፤“ በዚች ሰዓት የህወኃት ዋና አመራሮች ያሉበት ቦታ አየር ሃይሉ ያውቃል የዘገየው በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በመጠንቀቅ ነው፤አይጦች አሉ ብለን ቤት አናቃጥልም፤ትግራይ ቤታችን ነው”  ብለዋል፡፡


Read 8044 times