Saturday, 21 November 2020 09:59

ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በአገር ክህደት ተወነጀሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

 “እኔ ውግንናዬ ከማንም ሳይሆን ከሰላም ነው”

           የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ከፌደራል መንግስት ጋር ጦርነት የገጠመውን የህወሃት ቡድን ደግፈው በመንግሰት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማሳደር የማግባባትና የጦር መሳሪያ የማፈላለግ ተግባር ላይ ተጠምደው መሰንበታቸው የተገለፀ ሲሆን ይህ ድርጊታቸው በአገር ክህደት ወንጀል ሊያስጠይቃቸው ይችላል ተብሏል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ በበኩላቸው፤ “ውግንናዬ ለህወሃት ቡድንም ሆነ ለፌደራል መንግስቱ አይደለም፤ የኔ ውግንና ከሰላም ነው” ብለዋል።  ከፌደራል መንግስት ጋር ጦርነት ገጥሞ የሚገኘው ህወሃት፤ የጦር መሳሪያ እንዲያገኝ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር እንዲሁም  የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታትና የተለያዩ ሃገራት በፌደራል መንግስት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዳያደርጉ ሲያግባቡ መሰንበታቸውን የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም  ጀነራል ብርሃኑ ጁላ አስታውቀዋል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስና ጎረቤት ሃገራት፣ የፌደራል መንግስትን ህግ የማስከበር እርምጃ እንዲያወግዙ ሲቀሰቅሱ ከመሰንበታቸው ጎን ለጎን፣ ህወሃቶች የጦር መሳሪያ የሚያገኙበትን መንገድ ሲያፈላልጉ መቆየታቸውም ተመልክቷል፡፡
የዶ/ር ቴድሮስ ድርጊት ሀገሪቱን የካደ መሆኑን የሚገልፁት የህግ ፕሮፌሰሩ አለማየሁ ገ/ማርያም በበኩላቸው፤ በዚሁ ድርጊታቸው የተባበሩት መንግስታትንም ሆነ የዓለም ጤና ድርጅትን የስነ-ምግባር መርሆ መጣሳቸውን ያስረዳሉ፡፡
መንግስት የአካባቢውን ሰላም የሚያደፈርስ ነገር ሲያጋጥመው ህግ የማስከበር ሃላፊነትም መብትም አለው ያሉት ፕ/ር አለማየሁ ገ/ማርያም፤ ጦርነትንም ማወጅ የሚችለው የክልል መንግስት ነኝ የሚል ሳይሆን የፌደራል መንግስት ነው ብለዋል።
አንድ የክልሉ መንግስት ነኝ የሚል አካል ጦርነትን ለማወጅ መብት የለውም፤ ድርጊቱ የሚታየው  በአሸባሪነትና በአጥፊነት ደረጃ ነው  ብለዋል። አለማቀፍ የህግ ፕሮፌሰሩ።
ከዚህ አንጻር የአለም ጤና ድርጅትን የሚመሩት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የህወኃትን ድርጊት መደገፋቸውና የጦር  መሳሪያ ለማቅረብ ጥረት ማድረጋቸው አሸባሪነትን የመደገፍ ወንጀል ሆኖ ሊታይ ይችላል ያሉት ፕ/ር አለማየሁ፤ የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ የተባበሩት መንግስታት ያስቀመጧቸውን የባለሙያነት መርሆች የተቃረነ አካሄድ መከተላቸውንም አስረድተዋል። አንድ የአለም ጤና  ድርጅት መሪ በምንም መንገድ በአንድ ሃገር  የፖለቲካ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አይችልም ያሉት ፕሮፌሰሩ ከአለም ጤና ድርጅት ጥቅም ውጪ የሌላ አካል ጥቅም ለማስጠበቅ በምንም መልኩ መንቀሳቀስ የድርጅቱ የስነ-ምግባር መርሆ እንደማይፈቅድም አብራርተዋል፡፡
እነዚህን የስነ-ምግባር መርሆዎች  መጣሳቸውን ተከትሎም የህግ አንቀጾችንና  ድንጋጌዎችን በመጥቀስ፣ በዓለም ጤና ድርጅትና ዳሬክተር    ዶ/ር  ቴድሮስ አድሃኖም ላይ ክስ  ለመመስረት መዘጋጀታቸውን ነው ፕ/ር አለማየሁ  ያስገነዘቡት።
ከሃላፊነታቸው ውጪ በተንቀሳቀሱት ዶ/ር ቴድሮስ ላይ ክስ ለማቅረብ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ትብብር  እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የአለም ጤና ድርጅት አምስት መርሆችን ማለትም ህግ ማስከበር፣ ተጠያቂነት፣ ገለልተኝነት፣  አክብሮትንና የባለሙያነት መርሆችን መጣሳቸውን በማስረጃ ማረጋገጥ እንደሚቻል ነው ፕ/ር አለማየሁ ያስገነዘቡት። ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የቅሬታ ደብዳቤ መፃፉን ጠቁመው፣ የኢትዮጵያ መንግስትም በዶ/ር ቴድሮስ ላይ በወንጀል ተጠርጣሪነት ክስ ከመሰረተባቸው ከዓለም ጤና ድርጅት ሃላፊነታቸውን የሚነሱበት ሁኔታም እንደሚፈጠር ገልጸዋል ፕ/ሩ አለማየሁ ገ/ማርያም፡፡

Read 12878 times