Saturday, 21 November 2020 10:00

የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከ30 በላይ ተደራራቢ ክስ ይጠብቃቸዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

    • ህፃናትን ለጦርነት መጠቀም በአለማቀፍ የጦር ወንጀል ያስጠይቃል
       • እስረኞችን አፍኖ መውሰድ ሰዎችን የመሰወር አለማቀፍ ወንጀል ነው
       • መሰረተ ልማቶችን ማፈራረስ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው

                 ከ192 በላይ የህወኃት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከፍተኛ  የጦር መኮንኖችና የደህንነት አመራር አባላት የእስር መያዣ ወጥቶላቸው እየታደኑ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን እነዚህ ተጠርጣሪዎች ከ30 በላይ ተደራራቢ ክሶች እንደሚጠብቃቸው አንድ ታዋቂ የህግ ባለሙያ ለአዲስ አድማስ ተናገሩ፡፡
የፌደራል መንግስቱ በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ኦፕሬሽን ከጀመረ በኋላ እንኳን ተጨማሪ ማጣራት የሚፈልጉ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል የሚሉት የህግ ባለሙያው፤ በተለያየ ምክንያት በእስር ላይ የነበሩ ሰዎች ከእስር ቤት ታፍነው መወሰዳቸውን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ የህወሃት ሃይሎች ከ10 ሺህ በላይ ታሳሪዎችን ይዘው ወደ ኋላ አፈግፍገዋል የሚል መረጃ መውጣቱን የሚናገሩት ባለሙያው፤  ንጹሃንን አፍኖ መውሰድ ሰዎችን የመሰወር ትልቅ አለማቀፍ ወንጀል ነው ይላሉ፡፡ አሁን የሰዎቹ መሰወር ብቻ አይደለም የሚያሳስበው፤ ቀጣይ እጣ ፈንታቸው አለመታወቁም ጭምር  ነው፤ ብለዋል የሕግ ባለሙያው፡፡
ማይካድራ በተባለው ሥፍራ በህወሃት ልዩ ሃይል ተፈጽሟል የሚባለውን የጅምላ ጭፍጨፋንም ይጠቅሳሉ፡፡ ድርጊቱን በትክክል ልዩ ሃይሉ ስለ መፈጸሙ፣ እነማን እንደተጎዱ፣ የጉዳቱ መጠን ምን ያህል እንደሆነ በገለልተኛ ወገን ምርመራም መለየት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ "ይሄ ምርመራ ይዞ በሚመጣው ውጤት መሰረት ተጠያቂ የሚደረጉት በተግባሩ የተሳተፉና ተግባሩን ያቀዱ ይሆናሉ ማለት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የጦር ወንጀለኝነት ጉዳይም ይመጣል ማለት ነው።" ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በመቀሌ መግቢያዎች ላይ በህወሃት ሃይል መንገዶችና ድልድዮች እንዲፈራርሱም ተደርገዋል የሚል ውንጀላ በፌደራል መንግስቱ መቅረቡን በመጥቀስም፤ ይሄ በምርመራ ከተረጋገጠ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው ብለዋል፤ የህግ ባለሙያው፡፡ በሌላ በኩል፤ በትግራይ ክልል እንደታየው ህፃናትን ለጦርነት መጠቀም፣ መመልመልና ማሰልጠን በአለማቀፍ የጦር ወንጀል የሚያስጠይቁ መሆናቸውን የሚያስረዱት  ባለሙያው፤ ከኛ ህገ መንግስት ጀምሮ በሃገር ውስጥም ተጠያቂ የሚያደርጉ ህጎች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ እኛም በሚዲያ እንደምናየው፣ ምናልባትም 14 እና 15 አመት የሚሆናቸው በርካታ ህፃናት፣ ምንም በማያውቁት ጉዳይ ወደ ጦርነቱ እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡ ይህ ድርጊት ግን በሃገር ውስጥም በአለማቀፍ ህግም ያስጠይቃል ብለዋል።
ከፍተኛ አመራሮች  ከ30 በላይ ተደራራቢ ክስ ሊጠብቃቸው ይችላል የሚሉት የህግ ባለሙያው፤ እነዚህ ክሶች ደግሞ  ከ20 አመት እስከ ሞት የሚያስቀጡ ናቸው ብለዋል፡፡ "እስከ አሁን ባለው ክስ ብቻ ተጠርጣሪዎቹ ከ20 አመት በላይ ሊቀጡ ይችላሉ፤ ሁሉም ሲደማመሩ ምናልባት የ40 ዓመየሕወኃት ት ወይም የ50 ዓመት እስራት ሊሆን ይችላል። ያው የእድሜ ልክ እስራት ነው የሚሆነው።" ሲሉም ተጠርጣሪዎቹ ቅጣታቸው እስከምን ሊደርስ እንደሚችል ሙያዊ ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡


Read 13717 times