Print this page
Saturday, 21 November 2020 10:28

ጦርነትና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች - በህግ ባለሙያ ዕይታ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)


          • ህፃናትን ለጦርነት መጠቀም በአለማቀፍ የጦር ወንጀል ያስጠይቃል
          • እስረኞችን አፍኖ መውሰድ ሰዎችን የመሰወር አለማቀፍ ወንጀል ነው
          • መሰረተ ልማቶችን ማፈራረስ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው

           የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል የጀመረው ህግ የማስከበር ኦፕሬሽን ከተጀመረ ከሁለት ሳምንት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በጦርነት ወቅት ሁለት ተፋላሚዎች በሰብአዊ ፍጡር፣ በቅርሶችና በመሰረተ ልማቶች ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳይደርስ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለባቸው ዓለም አቀፍ ህጎች ይደነግጋሉ። የተባበሩት መንግስታት አበይት የሰብአዊ መብት ጥበቃ ድንጋጌዎች፣ አለማቀፍ የህግ ተጠያቂነት የሚያስከትሉ በጦርነት ወቅት የሚፈፀሙ ጥሰቶችን በዝርዝር አስቀምጧል።
ከእነዚህ አለም አቀፍ ድንጋጌዎች አንጻር፣ በፌደራል መንግስትና ትግራይን በሚያስተዳድረው ህወኃት መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዴት ይታያሉ? የሰብአዊ መብት ተቋማት የመብት ጥሰቶችን በቦታው ላይ ተገኝተው መከታተል ይችላሉ? ማይካድራ በተባለው ሥፍራ የተፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋ በተመለከተ በቂ መረጃ ማግኘት ይቻላል? ድርጊቱን የፈጸሙትን ወገኖች እንዴት ነው ተጠያቂ ማድረግ የሚቻለው? በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች  ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ የኢትዮጵያ የሠብአዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ዳይሬክተር እና የህግ ባለሙያ አቶ መሱኡድ ገበየሁን  እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡


               በጦርነት ወቅት የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምንድን ናቸው?
 ጦርነት በተከሰተ ጊዜ ሁለት ተፋላሚ ወገኖች ይኖራሉ፡፡ ጦርነቱ በመሳሪያ የታገዘ ሃይልን የማሳየት ሁኔታ ነው። በእንደዚህ ዓይነት  ወቅት ከመደበኛ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ህግ ይልቅ የጦርነት ህግ ነው ተግባራዊ የሚሆነው። ይህ ማለት ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ማክበር የሚገባቸው ህጎች አሉ፤ የራሱ የሆነ የአሰራር ዲስፒሊን አለው፤ በዚህ ይገዛሉ። በተለይ ንጹሃንና የንጹሃን ዜጎች መገልገያ የሆኑ መሰረተ ልማቶች፣ ተቋማት፣ ቤተ እምነቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ መገበያያ ስፍራዎችና ማንኛውም የህዝብ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ተቋማት የመሳሰሉትን በማናቸውም መልኩ የጥቃት ኢላማ እንዳያደርጉ ይገደዳሉ። ይህ በጄኔቭ ስምምነትም የተቀመጠ ነው። በሁለተኛ ደረጃ በተለይ በጦርነቱ ሂደት የሚማረኩ ሰዎች የጦር ምርኮኞች ናቸው። የእነዚህ የጦር ምርኮኞች አያያዝ ፍጹም ሰብአዊነታቸውን ያስከበረ መሆን አለበት። ጉዳት የደረሰባቸው በአስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ማግኘት አለባቸው፡፡ ቀይ መስቀልም ከሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ምንም አይነት እንቅፋት ሳያገኘው የሰብአዊ መብት ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡ ሌሎች አለማቀፋዊ ተቋማትም ሙሉ የሰብአዊ መብት ድጋፍ የማድረግ መብት አላቸው፡፡
ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች እነዚህ ገለልተኛ ሰብአዊ ተቋማት አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ ማድረግ አለባቸው፡፡ አሁን ትግራይን በሚያስተዳድረው ህወሃትና በፌደራል መንግስት መካከል ያለው ሁኔታ፣ መጀመሪያ አካባቢ ፌደራል መንግስት ራሱ “ጦርነት” ነው ብሎት  ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ጦርነት ሳይሆን ህግ የማስከበር ሂደት ነው እያለ ነው፡፡ ህግን ለማስከበርም በክልሉ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቷል፡፡ የፌደራል መንግስቱ ደግሞ በክልሎች የውስጥ ሁኔታ ጣልቃ እንዲገባ የሚፈቅድለትን አዋጅ ምክንያት  በማድረግ  ጣልቃ ገብቶ፣ ህግ የማስከበር ሂደት መጀመሩ ይታወቃል፡፡ አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራ እየተሰራ ባለበት ጎን ለጎን፣ ጊዜያዊ የክልል አስተዳደር ተቋቁሟል፡፡
 ከህግ ማስከበር ጎን ለጎን፣ ግን ጦርነት አለና፣ ንጹሃን በማናቸውም መልኩ ሊጠበቁ ይገባል፡፡ ይሄኛው በባህሪው ትንሽ ለየት የሚያደርገው፣ ልዩ ሀይሉ የራሱ መለዮ ያለው አይደለም፡፡ ሚሊሻው የራሱ መለዮ ያለው አይደለም፡፡ በጦርነት ጊዜ  የሚዋጋ በሰላም ጊዜ ስራ የሚሰራ ነው፤ ዩኒፎርም ያለው አይደለም፡፡ ሚሊሻዎች ራሳቸው መለዮ አይለብሱም፡፡ በጦርነት ህግ ደግሞ አንዱ መመዘኛ፤ ተፋላሚ ወገኖች ራሳቸውን የሚለዩበት አርማ ወይም ዩኒፎርም መልበስ አለባቸው፡፡ ይህ ከንጹሃን ጋር እንዳይቀላቀሉ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ ንጹሃን በመሃሉ እንዳይሞቱ ወይም ወታደሮቹ ንጹሃን መስለው ጥቃት እንዳይፈፅሙ ለመከላከል የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ አሁን በተደረገው ጦርነት እነዚህ ሁኔታዎች በትክክል ተግባራዊ ስለመደረጋቸው ምንም የታወቀ ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ሁለቱም ተፋላሚ እነዚህን የጦር ዲስፒሊኖች መተግበር አለባቸው ማለት ነው፡፡
 አሁን እየተካሄደ ባለው ህግ የማስከበር ኦፕሬሽን (ጦርነት) መሃል የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈፀሙ ለመከታተል እድል አግኝተዋል ማለት ይቻላል?
የሰብአዊ መብት ድርጅቶች አንዱ ኃላፊነት፣ የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን መርምሮ ማጋለጥ ነው፡፡ ጦርነትም ሆነ ሌሎች ግጭቶች ሰብአዊ ቀውስ እንዳያስከትሉ ሁሉንም ወገኖች ማስጠንቀቅና ግፊት ማድረግን የመሳሰሉትን መስራት አለባቸው። በቅርቡ ለምሳሌ ማይካድራ በተባለው ቦታ በርካታ ንጹሃን በማንነታቸው ተለይተው መገደላቸውን የተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት ይፋ አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለሙያዎች ልኮ በማጣራት ላይ ነው ያለው፡፡ እኛም እንደዚሁ መረጃዎችን በማጣራት ላይ ነው ያለነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊ ምርመራ አድርገን ይፋ እናደርጋለን፡፡ አሁን ግን ሁኔታውን አስቸጋሪ እያደረገው ያለው አለማቀፍ የቀይ መስቀል ማህበር ወይም ቀይ ጨረቃ ማህበር፣ በግጭቶቹ ቦታ ላይ የመግባት እድል የላቸውም፡፡ ግጭቱ አለማቀፍ ወይም አንድ አገር ከሌላው አገር ጋር  የሚያደርገው ጦርነት አይደለም፡፡ የውስጥ ግጭት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ተቋማት ከለላ አግኝተው ሁኔታውን ለመከታተል አይችሉም፡፡ በሌላ በኩል፤ አሁንም ግጭቱ ባለባቸው አካባቢዎች የስልክ አገልግሎት ተቋርጧል፣ኢንተርኔት የለም፤ ምንም አይነት ግንኙነት የለም፡፡ መረጃ እያገኘን ያለነው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ በኩል ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የተወሰኑ ሚዲያዎች እዚያው ቦታው ላይ ተገኝተው የሚዘግቡትን እንከታተላለን፡፡ ነገር ግን ከህወሃት በኩል የሚወጡ መረጃዎች ግልፅ አይደሉም፡፡ የጦርነት ፕሮፓጋንዳ ነው የሚመስሉት፡፡ ስለዚህ የሰብአዊ መበት ጥበቃን በተመለከተ የተጨበጠ ነገር ማግኘት እየተቻለ አይደለም፡፡ አሁን ከሚመለከታቸው ሰዎች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ መርማሪዎቻችን ወደ ቦታው ሄደው እንዲመረምሩ ጥረት እያደረግን ነው፡፡
ውጊያው በሚካሄድበት ትግራይ የኤርትራ ስደተኞች እንዳሉ ይታወቃል። በሌላ በኩል፤ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች ግጭቱ በመሸሽ ወደ ሱዳን እየተሰደዱ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብት ተቋማት በቂ መረጃ አላቸው?
የኤርትራ ስደተኞችን በተመለከተ አለማቀፍ የስደተኞች ተቋማት መረጃዎችን እያወጡ ነው፡፡ ስደተኞቹ ችግር ውስጥ እንዳሉ እየተሰማ ነው፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም። በተለያየ ምክንያት በእስር ላይ የነበሩ ሰዎች ከእስር ቤት ታፍነው ስለ መወሰዳቸው መረጃዎች አሉ፡፡ የህወሃት ሃይሎች ከ10 ሺህ በላይ ታሳሪዎች ይዘው ወደ ኋላ አፈግፍገዋል የሚል መረጃም ሰምተናል፡፡ ይህን በሚመለከት ተጨማሪ ማጣሪያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ከኤርትራ የመጡትን ስደተኞች ሁኔታ አስቸጋሪ የሚያደርገው፣ ህወሃት “የኤርትራ ወታደሮች እየወጉን ነው” በሚል እየከሰሰ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ላልተገባ አላማ ሊጠቀምባቸው ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡ ምርኮኛም ናቸው ሊሉም ይችላሉ። እነዚህን ስደተኞች ህወሃት እንደ መያዣ ሊጠቀምባቸውና ከፍተኛ የሠብአዊ መብት ጥሠት ሊፈጽምባቸው ይችላሉ የሚል ስጋት አለ። ይህን ስጋት የሚያጠናክረው የህወሃት መሪዎች በተደጋጋሚ በሚሰጡት መግለጫ፣ "በኤርትራ በኩል የኤርትራ ጦር እየወጋን ነው" እያሉ የሚያሰሙት ክስ ነው። ይህን ለማረጋገጥ ሲሉ ስደተኞቹ ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሊፈጽሙ ይችላሉ ተብሎ ይፈራል። በሌላ በኩል፤ እስከዚህ ሰዓት ድረስ ወደ 30 ሺ የሚደርሱ ሰዎች ግጭቱን በመፍራት ወደ ሱዳን ተሰደዋል። በአጠቃላይ የሰብአዊ ቀውሱን በሚመለከት ግን እስካሁን ምንም የተጨበጠ ነገር የለም።
ታሳሪዎችን  አፍኖ መውሰድ ከሰብአዊ መብቶች ጥሰት አንጻር እንዴት ይታያል?
እነዚህ ሰዎች ለምሳሌ የተለያየ ወንጀል ሰርታችኋል ተብለው ይሆናል የታሰሩት፡፡ አብዛኛው በራያ አካባቢ ያሉ ሰዎች ደግሞ የሚታሰሩት የማንነት ጥያቄ አንስታችኋል በሚል ፖለቲካዊ ምክንያት ነው። እነዚህን ሰዎች አፍኖ መውሰድ ሰዎችን የመሰወር ትልቅ አለማቀፍ ወንጀል ነው። አሁን መሰወሩ ብቻ አይደለም የሚያሳስበው፤ ቀጣይ እጣ ፈንታቸው አለመታወቁም ነው፡፡ አስገድደው ወታደር ያድርጓቸው፣ ይረሽኗቸው ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። ይህ እጅግ የሚያሳስብ ነው። በአለማቀፍ ህጐችም ንፁሃንን አፍኖ መሰወር ወይም እንደ መያዣ መጠቀም ወንጀል ነው፡፡ የፌደራል መንግስቱ ይሄን የህግ ማስከበር ስራ ሲሰራ፣ እነዚህ ሰዎች ከተሰወሩበት ስፍራ ተለቀው በሰላም ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚቀላቀሉበትን ሁኔታ መፍጠር አለበት። ቶሎ ህይወታቸውን ማትረፍ የሚቻልበትን ማንኛውንም የተመጣጠነ አካሄድ መከተል አለበት።
ማይካድራ ላይ በርካታ ንጹሃን ዜጐች ስለመጨፍጨፋቸውን መንግስትም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት አስታውቀዋል። በጦርነት ወቅት ንጹሃንን በዚህ መንገድ ማጥቃት በምን ህግ ነው የሚያስጠይቀው? ማንስ ነው ተጠያቂ የሚሆነው?  
እንዲህ ያሉ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ማድረግና የጦርነት ህጎችን ማክበር ያለባቸው ሁለቱም ወገኖች ናቸው። ከጦርነቱ ጋር ያልተገናኙ ንፁሃን ላይ ጥቃት መፈጸም በዋናነት የሚያስጠይቀው ጥቃቱን የፈፀመውን ወገን ነው፡፡ አሁን የማይካድራውን ጥቃት የህወሃት ሃይሎች እንደፈጸሙት እየተነገረ ነው። ይህ በትክክል በእነሱ ስለመፈጸሙ፣ እነማን እንደተጎዱ፣ የጉዳቱ መጠን ምን ያህል ነው ወዘተ…. በምርመራ መለየት አለበት። ይሄ ምርመራ ይዞ በሚመጣው ውጤት መሰረት ተጠያቂ የሚደረጉት በተግባሩ የተሳተፉ፣ ተግባሩን ያቀዱ ይሆናሉ ማለት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የጦር ወንጀለኝነት ይመጣል ማለት ነው። አሁን ጦርነት ነው ወይስ ህግ የማስከበር ነው? የሚለው ግልፅ ባለመሆኑ፣ የጦር ወንጀል ተፈጽሟል ብሎ ለመደምደም አስቸጋሪ ነው፡፡ መንግስት እየሆነ ያለው ምንድን ነው የሚለውን ግልፅ አላደረገም። ይፈለጋሉ ተብለው  ዝርዝራቸው ይፋ የተደረጉት ለክስ የተጠረጠሩበት ምክንያት  በጦር ወንጀል አይነት አይደለም። በሰው ልጅ ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ነው ተጠርጣሪ እየተደረጉ ያለው። አሁን ተማርከው የተያዙ የጦር ምርኮኛ አይደለም እየተባሉ ያሉት። ህገ-ወጥ ተግባር እየፈጸሙ የነበሩ ሰዎች ተደርገው ነው እየታሰቡ ያለው። ለምሳሌ መከላከያ ውስጥ ሆነው ከከዱ ራሱን በቻለ የጦር ወንጀል ፍ/ቤት ነው ጉዳያቸው መታየት ያለበት። ለዚህ በቂ የህግ ማዕቀፍ በሃገራችን አለ። ግን አሁን እንደ መደበኛ ወንጀል የታየ ነው የሚመስለው። ለሁሉም ወንጀሎች ግን በቂ ህግ አለ። ወንጀሉ የሚደራጅበት መንገድ ነው እነዚህ ሰዎች በምን ተከሰሱ የሚለውን የሚመለከተው እንጂ ሃገሪቱ በቂ ህጎች አሏት።
በአየር ድብደባ ወቅት የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችስ እንዴት ይታያሉ?
አንድ ተፋላሚ የአየር ድብደባ በሚፈጽምበት ወቅት ለሰብአዊ ግልጋሎት የሚውሉ ተቋማትን ዒላማ ማድረግ የለበትም። ድልድዮችን፣ መንገዶችን፣ መስጊዶችን ወዘተ የመሳሰሉትን ኢላማ ማድረግ የለበትም። እነዚህ ኢላማ ከተደረጉ የጦር ወንጀል ተፈጽሟል ማለት ነው፡፡ ንፁሃንን ኢላማ ያደረገ ጥቃት የጦር ወንጀል ይሆናል። እስከአሁን ግን እነዚህ ተግባራት ስለመፈጸማቸው ተጨባጭ መረጃ የለም፤ ማስረጃም አልቀረበም፡፡ በቪዲዮ፣ በሞባይል የቀረበ ነገር የለም፡፡ እንዲሁ ከመናገር በዘለለ። ስለዚህ አሁን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ተፈጽሟል ብሎ ለመናገር የሚያስችል መረጃ  የለም። በሌላ በኩል፤ በህወሃት ሃይል ድልድዮች ተመተዋል፤ እንዲፈራርሱ ተደርገዋል የሚል አቤቱታ በፌደራል መንግስት ቀርቧል። ይሄ እውነት ከሆነ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ይሆናል። ይሄ ስለመፈፀሙ ግን በገለልተኛ አካል በደንብ መጣራት አለበት።
ህወኃት ዕድሜያቸው ያልደረሰ ህፃናትን ለጦርነት መልምሎ አሰማርቷል የሚል ክስም ይቀርብበታል፡፡ በዚህ ዙሪያ መረጃ አሰባስባችኋል? ድርጊቱ ከሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች አንፃር እንዴት ይታያል?
ህፃናትን ለጦርነት መጠቀም፣ መመልመል፣ ማሰልጠን ወዘተ…. እነዚህ ሁሉ በአለማቀፍ የጦር ወንጀል የሚያስጠይቁ ናቸው። ከኛ ህገ መንግስት ጀምሮ በሃገር ውስጥም ህጎች አሉ። ድርጊቱ በባህሪው አለማቀፍ የጦር ወንጀለኝነት ነው፡፡ የኛም ህግ ድርጊቱን ወንጀል ያደርገዋል። ያ ሲሆን ደግሞ በዚህ ሂደት ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች ሙሉ በሙሉ የህግ ተጠያቂነት አለባቸው። እኛም በሚዲያ እንደምናየው፣ ምናልባትም 14 እና 15 አመት የሚሆናቸው በርካታ ህፃናት፣ ምንም በማያውቁት ጉዳይ ትምህርታቸውን አቋርጠው፣ ወደ ጦርነቱ እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡ በእርግጥ ተጨማሪ ማጣራት ይፈልጋል። ይህ ድርጊት ግን በሃገር ውስጥም በአለማቀፍ ህግም ያስጠይቃል።
ወንጀሉ ምን ያህል ከባድ ነው?
አሁን የተፈጸሙት ድርጊቶች ህፃናትን ለጦርነት መመልመል ብቻ አይደለም። ይህ አንዱ የወንጀል ፍሬ ነው። ሌሎች ተደራራቢ ጥፋቶችም አሉ። እነዚህ ሰዎች ከ30 በላይ ተደራራቢ ክስ ሊጠብቃቸው ይችላል። እነዚህ ክሶች ደግሞ  ከ20 አመት እስከ ሞት የሚያስቀጡ ይሆናሉ። እስከ አሁን ባለው ክስ ብቻ ተጠርጣሪዎቹ ከ20 አመት በላይ ሊቀጡ ይችላሉ። በሌሎችም እንደዚያው። እነዚህ ሲደመሩ ምናልባት  የ40 ዓመት ወይም  የ50 ዓመት እስራት ሊሆን ይችላል። በእርግጥ እንደዚያ ሲሆን የእድሜ ልክ እስራት ነው የሚሆነው፡፡ ግን ወንጀሎቹ በጣም ጥብቅ በመሆናቸው እስከ ሞት የሚያስወስኑ ክሶች ናቸው ሊቀርቡ የሚችሉት።
በጦርነት ወቅት የሚፈጸሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በየትኛው ሸንጎ ይታያሉ?
በጦርነት ጊዜ ብዙ አይነት ተግባራት ይፈፀማሉ። አለማቀፍ የጦርነት ህግ አለ። ተፋላሚዎች ማክበር ስላለባቸው ነገሮች በሰፊው ያትታል። ያንን ካላከበሩ አለማቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍ/ቤት አለ። በዚያ በኩል ተጠያቂ ይደረጋሉ። እንደምናውቀው አልበሽርን ጨምሮ የተለያዩ አምባገነን መሪዎች አለማቀፍ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ሲታደኑ ነበር። በድርጊቱ የተሳተፈ ማንኛውም አካል አለማቀፍ የጦር ወንጀል ፍ/ቤት ይቀርባል ማለት ነው። መንግስታት ለእንደዚህ አይነት ስምምነት ፈቃደኛ መሆን ይገባቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ግን እንዲህ ያለው ሂደት ፖለቲካዊ ሲደረግ ነው የሚታየው። ተቋሙ አሁን ካለው ቁመና አንጻር ትክክለኛ ፍትህ ይሰጣል ተብሎም የሚታመን አይደለም። በኛ በሃገር ውስጥ ያሉ ህጎችም አሉ፡፡ በእነሱ በኩልም ሊዳኙ ይችላሉ፡፡


Read 4226 times