Print this page
Saturday, 21 November 2020 10:36

‘የዕድሜ ጥያቄና ኮረንቲ በሩቁ!’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

መልካም፣ መልካሙ ነገር ሁሉ ለ‘ፈረንጅ’ ተሰጥቶ እኛን እኮ “ሁሉም ዜሮ፣ ዜሮ” አድርገውናል፡፡ ያ ማነው የሚሉት ፈረንጅ “የጤፍ የባለቤትነት መብት ለእኔ ካልተሰጠኝ፣” ሲል የነበረው እኮ ከመሬት ተነስቶ አይደለም፡፡ ‘በር ሳይቆልፉ፣ ሰውን ሌባ ይላሉ’ እንደሚባለው ነው፡፡ እንደውም “ለጤፉ ሲገርማቸው ገና የቆጭቆጫውንም የባለቤትነት መብት እወስድላቸዋለሁ፣” ሳይል  አይቀርም.... ለዚህ፣ ለዚህ አይነት ነገሮች በጣም እንመቻለና! (ለዛኛው ወገን ‘አሳልፎ በመስጠት’ማ፣ ችሎታችንን ለሌላውም ‘ኤክስፖርት’ ማድረግ እንችላለን።) በነገራችን ላይ፣ ይሄ ‘ፈረንጅ፣ ፈረንጅ’ የሚለው ነገር ምንም ሊለቀን ያልቻለ ነገር ነው፡፡ ትንሽ ጊዜ ቆይቶ “ከውጪ በመጡ ጀርመናውያንና አሜሪካውያን አማካይነት በሳምንት ሦስት ቀን የግእዝና የቅኔ ትምህርት ይሰጣል፣” አይነት ማስታወቂያ ብንሰማ የሚገርም አይሆንም፡፡
                
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንግዲህ ሁሉንም ነገር ጥሎ የማይጥለን ፈጣሪ ይመልሰው ማለት ነው እንጂ ምን ማለት ይቻላል!
የቢሮ ባልደረባችሁ ለተወሰነ ቀናት ቆይታ ትመጣለች፡፡
“ሰሞኑን አላየሁሽም፡፡ የት ጠፍተሽ ነው?”
“አዎ፤ ምን እባክህ የበርዝዴይ ዝግጅት ውጥር አድርጎ ይዞኝ ነበር”
“በርዝዴይሽን እንደምታከብሪ ገና መስማቴ ነው፡፡ ምነው እኛን ረሳሽን?” ይቺ እንኳን ዝም ብላ ከአፍ የምታመልጥ ጨዋታ ማሟሟቂያ ነች እንጂ ከልብ አይደለችም። ልክ ነዋ... አይደለም ቤቷ ድረስ ግብዣ ልትጠራችሁ ቢሮ ውስጥ እኮ አብራችሁ ሻይ ጠጥታችሁ አታውቁም!
“ማን ነው የእኔ ልደት ነው ያለህ! ማህሌት አሥራ ስምንት ዓመት ሞላት፤ ደስ አይልም!” ምኑ!? ለእናንተ ምኑ ነው ደስ የሚለው! የሆነች ማህሌት አሥራ ምናምን ዓመት ሞላትና ምን ይጠበስ! ልክ እኮ ኦፊሴላዊ እድሜዋ አሥራ ስምንት ዓመት የሞላትን ማህሌት የምትባለውን እናንተ ራሳችሁ ፎጣና ውሀ ይዛችሁ ያዋለዳችሁ ነው የሚመስለው፡፡ (ቤት ውስጥ ምናምን ሲሆን እንደዛ የሚመሳስሉ ነገሮች አሉ አይደል እንዴ!) የወለደችው እሷ! በሌላ ሰው የሥራ ውጤት የምን ኮንግራጁሌሽን ምናምን ነው!
“በነገራችን ላይ ስንተኛ ልጅሽ ነች?”
ምን! ልክ እኮ በየቀኑ ስንት መከራ የሚታይበትን ጸጉር...አለ አይደል... “አንቺ፣ ምንድነው ነጫጩ እዚህ ብቅ፣ ብቅ ያለው!” ያላችኋት ነው የሚመለሰው፡፡ ስሙኝማ...ጨዋታ የማያውቅ ሰው ልኩን አውቆ እንደ እኛ ጭጭ ነው፡፡ ግፋ ቢል “ምን አይነቱ ደባሪ ምናምን ነው! አፉን በኤክስካቬተር ቢፈለቅቁት ትንፍሽ የማይል እኮ ነው!” ብትባሉ ነው፡፡ ስንተኛ ልጅሽ ናት?
“ምን ማለትህ ነው?”
“እ..አይ..ምን መሰለሽ፣ ከልጆችሽ አንዷ ትሆናለች ብዬ ነው”
“የማን የእኔ? አንተ ሰውዬ ዛሬ በተዋቲ አሽሙር ነው እንዴ የያዝከኝ!”
‘ሴትዮዋ እንዴት ነው ነገር የምትተረጉመው!’ የጨዋታ ህጉን ሳያውቁ ጨዋታ ውስጥ መግባት ይሄንን ያስከትላል፡፡
“ኸረ እኔ እንደዛ አይነት ነገር አላሰብኩም!”
ይሄ ‘ውሀ የማያነሳ መከራከሪያ’ የሚሉት ነው፡፡ ልክ እኮ የእግር ኳስ ህጎችን ሳያውቅ ሜዳ ገብቶ ከጨዋታ ውጪ ፊሽካ ሲነፋበት...“ቀድሜያቸው ባለፍኩ ይጨበጨብልኛል እንጂ እንዴት ቅጣት ይሰጥብኛል!” እንደሚል ኳሰኛ ማለት ነው፡፡
“አባክህ ይቺን፣ ይቺን ጨዋታማ እናውቃታለን፡፡ አንተም እንደ መሥሪያ ቤቱ ሰዎች ልትሆን ነው እንዴ!” ይሄም በዛ! ይሄም በጣም በዛ!
“በቃ ይቅርታ፣ ሳላውቅ ነው”
“አንተ እኔ ስጫወት ነው፣ እንዲህ ታመራለህ እንዴ!” ስሚኝማ....እኛም ይቺን፣ ይቺን ጨዋታ እናውቃታለን፡፡ “በአራት እግሩ እየዳኸ ባይለምነኝ ምን አለች በሉኝ!” የተባለለት እሱዬው...አለ አይደል... “ቻዎ፣ ቻዎ ሲኞሪና...” ነገር ማለት ሲጀምር... “አንተ ታመራለህ እንዴ!” አይነት ነገር ትመጣለች። (እንደ ፕሬሚየር ሊግ እንቅሰቃሴውን ቫር ላይ አይታ ውሳኔዋን የለወጠች አይነት፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...)
“ማህሌት የእህቴ ልጅ ነች፡፡ ደግሞ አንተ እኔ ነኝ የአስራ ስምንት ዓመት ልጅ የማደርሰው?”
አሁን ሌላ ጨዋታ ሊመጣ ነው... ‘ገብስ፣ ገብሷ’፡፡ እናማ ‘ገብስ፣ ገብሷ’ተብሎ ግን ‘ፈረንጅ፣ ፈረንጅ’ ነገር እንዳያደርጋችሁ፡፡ (ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...እዚህ ሀገር እንደው ‘ዘመናዊ’ የሚባል ወይም መልካም ባህሪይ ነገር ስታሳዩ፣ መልካም ነገር ስትሠሩ “እሱ እኮ ፈረንጅ ነው፣” ምናምን የሚባለው ነገር አይገርማችሁም! ቀጠሮ አክብራችሁ ስትገኙ...“እሱ እኮ ፈረንጅ ነው፡፡ አንዲት ደቂቃ ዝንፍ አይልም፡፡” የሆነ ሰብአዊ የሚባል ድርጊት ስትፈጽሙ... “እሷ እኮ ፈረንጅ ነች፡፡ እሷ የሁለት ወር ኪራይ ባትሸፍንላቸው ኖሮ ይሄኔ ጎዳና ላይ ወጥተው ነበር፡፡”
እናላችሁ... መልካም፣ መልካሙ ነገር ሁሉ ለ‘ፈረንጅ’ ተሰጥቶ እኛን እኮ “ሁሉም ዜሮ፣ ዜሮ” አድርገውናል፡፡ ያ ማነው የሚሉት ፈረንጅ “የጤፍ የባለቤትነት መብት ለእኔ ካልተሰጠኝ፣” ሲል የነበረው እኮ ከመሬት ተነስቶ አይደለም፡፡ ‘በር ሳይቆልፉ፣ ሰውን ሌባ ይላሉ’ እንደሚባለው ነው፡፡ እንደውም “ለጤፉ ሲገርማቸው ገና የቆጭቆጫውንም የባለቤትነት መብት እወስድላቸዋለሁ፣” ሳይል  አይቀርም.... ለዚህ፣ ለዚህ አይነት ነገሮች በጣም እንመቻለና! (ለዛኛው ወገን ‘አሳልፎ በመስጠት’ማ፣ ችሎታችንን ለሌላውም ‘ኤክስፖርት’ ማድረግ እንችላለን።) በነገራችን ላይ፣ ይሄ ‘ፈረንጅ፣ ፈረንጅ’ የሚለው ነገር ምንም ሊለቀን ያልቻለ ነገር ነው፡፡ ትንሽ ጊዜ ቆይቶ “ከውጪ በመጡ ጀርመናውያንና አሜሪካውያን አማካይነት በሳምንት ሦስት ቀን የግእዝና የቅኔ ትምህርት ይሰጣል፣” አይነት ማስታወቂያ ብንሰማ የሚገርም አይሆንም፡፡
እናላችሁ... እናንተ ነገር ረገበ ካላችሁ በኋላ እሷዬዋ ገና አምስተኛ ማርሽ ላይ ነች፡፡
“ስማ አንተ፣ ስንተኛ ልጅሽ ነች ያልከኝ ስንት የሚሆነኝ መስሎህ ነው!”
ይሄ ገር የመሰለ ‘አደገኛ ቁልቁለት’ አይነት ጥያቄ ነው፡፡ ነገርዬው ወደ እናንተ ሊዞር ይችላል፡፡ እንዳይከፋት ብላችሁ ቀነስ ያደረጋችሁት እንደሁ ልክ ከመሥሪያ ቤት የግማሽ ቀን ፈቃድ ወስዳችሁ እንትን ሆስፒታል ቆማችሁ ያዋለዳችሁ ሊመስል ይችላል፡፡ ስለዚህ የመሚስላችሁን ባይሆንም ቀረብ ያለውን ተናግራችሁ የመሸበት ማደር ነው፡፡ እናማ...አለ አይደል... ስንት ልበላት እያላችሁ ስታሰላስሉ እሷዬዋ መተንፈሻ ሴኮንዶች አታስተርፍላችሁም፡፡ እናላችሁ... የብዙዎቻችን ነገር እንዲህ እየሆነም ነው መግባባት ያቃተን፡፡...አለ አይደል...እዛው ፈላ እዛው ሞላ አይነት ነገር፡፡
“በላ አሮጊት ነሽ በለኛ!... አንደኛውን እማሆይ አትለኝም!” ‘ይህን ያህል ያዙኝ ልቀቁኝ የሚያሰኝ ነገር ተናግሬያለሁ እንዴ!’...“እኮ ንገረኛ፣ ስንት የሚሆነኝ ይመስልሀል?”  እንግዲህ የቁርጧ ደቂቃ ከመጣች ተናግሮ መገላገል ነው፡፡
“ካላበዛሁት ወይ ወደ ሠላሳ ማለቂያ፣ ወደ አርባ መጀመሪያ...”
“ምን? ሠላሳ!... አርባ! እማዬ ድረሽ!”
እንዴ... አርባ ስላላችሁ እናቷን ድረሺልኝ ያለች ‘ካልኩሌት’ አድርጋችሁ የደረሳችሁበትን  ‘ፎርቲ ሰቨን’ን ብትጠቅሱ ከከተማም፣ ከገጠርም ያሉ ዘመዶቿን ሁሉ ልትሰበስብ ነበር ማለት ነው! ለነገሩ እናንተም ብትሆኑ... የፈለገው ቢሆን... ካልጠፋ ቁጥር አርባ ድረስ ያዘለላችሁ የተጣመመውን  የሚያቃና ‘ስፒች ራይተር’ እንደሌላችሁ የሚያሳይ ነው፡፡ (ቂ...ቂ...ቂ...እንደዛ የሚመሳስሉ ብዙ ነገሮች ስለምንሰማ ነው፡፡) ይሄኔ እኮ “እነ እንትናን ሊነካ ፈልጎ ነው...” የሚሉ ወዳጆች ይኖራሉ!)
“አንተ፣ እኔ ገና ሀያ አራተኛ ዓመቴን ካከበርኩ ስድስት ወር እንኳን መች ሞላኝ! እስቲ ጸጉሬ ላይ አንዲት ነጭ ጸጉር ታገኛለህ?”
እሱን እንኳን ተዪው! የምን ተናግሮ ማናገር ነው! በሀያ አራቱ ላይ ልንተሳሰብ እንችላለን ...አለ አይደል... ‘በድምር ይስተካከል ወይስ በብዜት’ በሚለው ማለት ነው፡፡ የነጯን ጸጉር ነገር ግን ተዪንማ! ይሄን ያህል ከሰብአዊ መብት ረገጣ የማይተናነስ ጥቃትማ አይደርስብንም። ሰውየው “ለልደቴ ሠላሳ ምናምን ሻማ አበራሁ፣” ሲል “ሻማውን በሁለት በኩል ነው ወይ የለኮስከው?” ያለው ጓደኛው ወይ የወዳጅ ‘ምቁ’ ነው ወይም ደግሞ የሂሳብ ‘ጂኒየስ’ ነው። እናማ... ሠላሳና አርባን በመጥቀሳችሁ ወይ የሥራ ባልደረባ ‘ምቁ’ ናችሁ፣ ወይ የሂሳብ ችሎታችሁ እየተሻሻለ ነው ማለት ነው፡፡ እናማ... ሰዉ “ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ፣” እንደሚለው” አይነት ‘የዕድሜ ጥያቄና ኮረንቲ በሩቁ!’ ተብሎ አሜንድመንት ምናምን ይካተተልንማ!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...እግረ መንገዴን፣ አንዳንዴ የ‘ቦሊተከኞቻችን’ ነገር ምኑንም፣ ምናምኑንም መንገድ ላይ አንጥፎ “ሀያ ብር የነበረው አስር ብር…” የሚባለው አይነት አይመስላችሁም! የአንዳንዶቹን ሀሳብ ስንሰማ እኮ ጎዳና ላይ አቧራ ከሚጠጣ  የቅናሽ እቃ አልሻል አለን! (እንትና፣ ስማኝማ... ሰፈራችሁ “መቶ ብር የነበረው ቦተሊካ አስራ አምስት ብር...” የሚል ነገር ከሰማህ ደውልልኝማ! በደርዘን እሸምተውና የማደርገውን አውቃለሁ። አሀ...ምንያለሽ ተራማ የምርቶች እጥረት ሊገጥመው አይገባማ! ቂ...ቂ...ቂ...)
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1638 times