Friday, 27 November 2020 00:00

የአለማችን ከተሞች የኑሮ ውድነት ደረጃ ይፋ ተደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የአለማችንን ከተሞች የኑሮ ውድነት ሁኔታ በመገምገም በየአመቱ የአገራትን ደረጃ የሚያወጣው የኢኮኖሚስት መጽሄት የምርመራ ክፍል ከሰሞኑም የ2020 የፈረንጆች አመት ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የስዊዘርላንዷ ዙሪክ፣ የፈረንሳዩዋ ፓሪስ እና የቻይናዋ ሆንግ ኮንግ የአለማችን እጅግ ውድ ከተሞች በመሆን የአንደኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በከተሞች የሸቀጦችና አገልግሎቶች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በኑሮ ውድነት ሲንጋፖር የአራተኛ፣ ቴል አቪቭ እና ኦሳካ የአምስተኛ፣ ጄኔቫ እና ኒውዮርክ የሰባተኛ፣ ኮፐንሃገን እና ሎሳንጀለስ ደግሞ የዘጠነኛ ደረጃን መያዛቸውን አመልክቷል፡፡
ከ130 በላይ በሚሆኑ የአለማችን ከተሞች በአመቱ ያደረገውን ጥናት መሰረት አድርጎ ተቋሙ ይፋ ያደረገውን የ2020 አለማቀፍ የከተሞች የኑሮ ውድነት ሁኔታ ሪፖርት ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ የቻይና እና የአሜሪካ ፍጥጫ መባባሱን ተከትሎ በርካታ የቻይና ከተሞች በዝርዝሩ ውስጥ በቀዳሚነት መካተታቸውንና የሁለቱ አገራት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ፉክክር የተለያዩ ሸቀጦች ዋጋ እንዲንር ምክንያት መሆኑንም አስረድቷል፡፡
ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በአሜሪካ፣ አፍሪካና ምስራቅ አውሮፓ ከተሞች የኑሮ ውድነት ሁኔታው ዘንድሮ ቅናሽ ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው፣ በአንጻሩ በምዕራብ አውሮፓ አገራት ግን የኑሮ ውድነት መባባሱንና ከአስሩ የአመቱ ውድ ከተሞች መካከል አራቱ በምዕራብ አውሮፓ እንደሚገኙም  ገልጧል፡፡
በሌላ አለማቀፍ ዜና ደግሞ፣ በኢንተርኔት አማካይነት የሚፈጸሙ ወንጀሎች በአለማቀፍ ደረጃ እየተባባሱ መምጣታቸውንና በመጪው የፈረንጆች አመት 2021 አለማችን በመሰል ወንጀለኞች በያንዳንዱ ደቂቃ 11.4 ሚሊዮን ዶላር ያህል ታጣለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡
የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ከሰሞኑ ለንባብ ባበቃው መረጃ እንዳለው፣ አለማችን በኢንተርኔትና በቴክኖሎጂ ላይ ያላት ጥገኝነት እየጨመረ ከመሄዱ ጋር በተያያዘ በመስኩ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ከፍተኛ ኪሳራ የማድረስ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በቅርቡ በተከናወነ አንድ አለማቀፍ ጥናት፣ በኢንተርኔት አማካይነት ለሚፈጸሙ የመረጃ ምንተፋና ተያያዥ ወንጀሎች የሚጋለጡ ኩባንያዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ያስታወሰው መረጃው፤ ካለፈው ጥር ወር አንስቶ በኢንተርኔት የሚፈጸሙ ወንጀሎች በእጥፍ ያህል ማደጉንም አመልክቷል፡፡


Read 5653 times