Monday, 23 November 2020 00:00

በርቸ፤ አገራዊ የሞራል እሴት

Written by  (አበበ ብሩ፤ በጅማ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(4 votes)

  "በጉራጌ ወግና ባህል ውስጥ አንድ ግለሰብ መጥፎ ነገር ገጥሞት በመጥፎው ነገር ላይ የሚያፌዝና የሚያላግጥ ሰው ካለ፣ በርቸ ይሁንብህ መባሉ አይቀሬ ነው፡፡ ምከንያቱም የሰው ልጅ ማህበረሰባዊ እንስሳ እንደመሆኑ መጠን የሌላ ሰው ችግርና መከራ አብሮ በመጋራት አብሮ ይሰለፋል እንጂ በወገኑ ላይ በደረሰው ችግር የሚሳለቅ አይሆንም፡፡"
              
          የሰው ልጅ ማህበረሰባዊ እንስሳ መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ማህበረሰባዊ እንስሳ ከመሆኑ የተነሳ ማህበራዊነቱን ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ ግብረገባዊ መርሆች ሚናቸው በአንድም በሌላ የጎላ ነው፡፡ በግብረገብ አስተምህሮ ውስጥ የዕለት ተዕለት ሥራችን የምንመዝንባቸው ግብረገባዊ መርሆችና እሴቶች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ይህም ማለት እያንዳንዱ ማህበረሰብ የራሱ የሆነ የግብረገብ (Moral) መርሆች አሉት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ ማህበረሰብ አንድ አይነት ወይም ተመሳሳይ ግብረገባዊ ህጎች አሉት ማለት አይደለም፡፡ በግብረገብ ፍልሥፍና (Moral Philosophy) ከሚነሱ ወሳኝ ጥያቄዎች ውስጥ ሥለ ግብረገብ ህጎች አለም አቀፋዊና አንፃራዊነታቸው ብዙ የሚያከራክር ጉዳይ ነው፡፡ አለምአቀፋዊነት (Universalism) የሚያራምድ ሰዎች የሚነግሩን ነገር ቢኖር የግብረገብ ህጎች ሁሉም ቦታ አንድ አይነት ይዘት እንዳላቸው ነው፡፡ ነገር ግን አንፃራዊነትን (Relativism) የሚቀበሉ ሰዎች የሚነግሩን ነገር ቢኖር የግብረገብ ህጎች ከማህበረሰብ ማህበረሰብ፣ ከቦታ ቦታ፣ እንዲሁም በጊዜ ሂደት ውስጥ እንደሚለያዩ ነው፡፡
በዓለም ላይ ብዙ ቋንቋዎች ከመነገራቸው፣ ብዙ ባህሎች ከመኖራቸው፣ የተለያዩ ሀይማኖቶች ከመፈጠራቸው፡ የተለያዩ ፖለቲካዊና የምጣኔ ሀብት ዘይቤ (idelology) ከመፈብረካቸው የተነሳ አንፃራዊነትን ተመራጭ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በዚህም ፅሑፍ ውሰጥ ግብረገባዊ ህጎች አንፃራዊ መሆናቸውን ከሚያሳዩን የግብረገብ መተዳደሪያ መርሆች ውስጥ በርቸ የተሰኘ ብርቱ ግብረገባዊ ቃል የምንዳስስ ይሆናል፡፡
የጉራጌ ማህበረሰብ የራሱ የሆነ ግብረገባዊ መርሆችና ዕሴቶች አሉት፡፡ በጉራጌ ማህበረሰብ ውስጥ ከፖለቲካ ህግ በላይ ማህበረሰቡ የሚተዳደረውና የሚዳኘው በታነፁ ግብረገባዊ በሆኑ መመርያዎች ነው፡፡ በሀገራችን ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸው የሆነ፣ አንዱ ከሌላው የሚለይ ነገር ግን በዓላማ የሚቆራኙ ግበረገባዊ ዕሴቶች አሏቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ የጉራጌ ማህበረሰብ የራሱ የሆነ ማራኪና መሳጭ የግብረገብ መርሆች አሉት፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ ሁሉንም ዳስሼ ስለማልጨርስ ለዛሬ በርቸ የተሰኘ ግብረገባዊ ይዘት ያለው ብርቱ ወግ የምንፈትሽ ይሆናል፡፡
በርቸ ምንድን ነው? በርቸ ብዙ ትርጉም አለው፡፡ ትርጉሙ ይህ ነው ተብሎ  ሊገለፅ አይችልም፡፡ ምክንያቱም በርቸ ከሁሉም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ጋ የተዛመድ ጠንካራ ቃል ነው፡፡ በርቸ ማለት እኔ ያየሁት አንተም፣ አንቺም፣ እንዲሁም እናንተም እዩት የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ በሌላ አገላለፁ በርቸ የሚያመላክተው፤ እኔ ላይ የደረሰው በእናንተም ላይ ይድረስ እንደ ማለት ነው። እዚህ ጋ ልንመረምራቸውና ልንፈትሻቸው የሚገቡ ቃላት አሉ፡፡ ይድረስ ወይም እየው የሚሉት ቃላት ይሆናሉ፡፡ ይህን በርቸ የሚል ሰው "እኔ የደረሰብኝ አንተም ይድረስብህ፣ እኔ የገጠመኝ እናንተም ይግጠማችሁ" ማለቱ በመልካም ነገር ነው ወይስ በመጥፌ ነገር ነው?
በአጭሩ አንድ ሰው ሌላ ወገን በመጥፎም ሆነ በጥሩም ነገር በርቸ ሊለው ይችላል። እዚህ ጋ እንዴት አንድ ችግር የገጠመው አካል፣ ለሌላው አካል በርቸን በመጥፎ ይሁንብህ ብሎ መጥፎ ምኞት ይመኝለታል የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ አዎ በርቸ ይድረስብህ በማለት ለሌላው ወገን አሉታዊ ምኞት ይመኝ ይሆናል፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ ተቃራኒ በሆኑ ነገሮች ግራና ቀኝ፣ ላይና ታች፣ ማግኘትና ማጣት፣ መደሰትና መከፋት በመሳሰሉ ውጥረቶች ተጠምዶ ይስተዋላል፡፡
በዚህም መሠረት፤ በጉራጌ ወግና ባህል ውስጥ አንድ ግለሰብ መጥፎ ነገር ገጥሞት በመጥፎው ነገር ላይ የሚያፌዝና የሚያላግጥ ሰው ካለ፣ በርቸ ይሁንብህ መባሉ አይቀሬ ነው፡፡ ምከንያቱም የሰው ልጅ ማህበረሰባዊ እንስሳ እንደመሆኑ መጠን የሌላ ሰው ችግርና መከራ አብሮ በመጋራት አብሮ ይሰለፋል እንጂ በወገኑ ላይ በደረሰው ችግር የሚሳለቅ አይሆንም፡፡ በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ማንም ሰው በክፉ ነገር በርቸ እንዳይባል፣ የሌላውን ችግር ለመካፈል ብዙም አያንገራግርም፡፡  ነገር ግን የወገኑ ችግር ነገ በእኔ ላይ አይደርስም ብሎ የእምቢተኝነት ስሜት የሚያሸንፈው ሰው በርቸ ይሁንብህ ከመባል አያመልጥም፡፡ በዚህም ግብረገባዊ በሆነ ቃል ውስጥ ማህበረሰባዊ ፍልስፍና (Social philosophy) እንዲዳብርና እንዲጐለብት የራሱ የሆነ ሚና አለው፡፡
እንደዚህ አይነት ያሉ ጠቃሚ የሆኑ ግብረገባዊ መርሆች የተለየ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በተለይም ደግሞ አሁን ካለንበት ሀገራዊ አለመረጋጋትና እዛም እዚም ለሚፈጠሩ ችግሮች ፖለቲካዊ ውሳኔን ወይም መንግስታዊ ህጎችን ብቻ መፍትሔ አድርጎ ማቅረብ በቂ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉትም ከሆነ፣ ሀገርን ለመምራትም ሆነ ችግሮቻችንን ለመፍታት ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ ህግ ብቻ መሠረት አድርጎ መንቀሳቀስ ለውጥ ላያስገኝ ይችላል፡፡ ይልቁንም ችግር ባለበት አካባቢ፣ ችግሩን ለማስተካከል የሚሞክር ማንኛውም አካል ቅድምያ መስጠት ያለበት አካባቢያዊ ለሆነ ህጎች መሆን አለበት፡፡ ምከንያቱም የዚያ አካባቢ ማህበረሰብ ከፖለቲካ ህጎች በተሻለ በውስጡ ስለሚገኙት የግብረገብና የሥነምግባር ዕወቀቶቹ የላቀ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ደራሲ የተናገረውን እንደሚከተለው እንመረምራለን፡፡
ደራሲ እንዳለ ጌታ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ደራሲው የሚከተለውን ብሏል። ለምሳሌ ሰዎች ቢጣሉ፣ ተጣልተውም በፖለቲካ ህግ ቢዳኙ፣ አንዱ ከሳሽ ሌላው ተከሳሽ መሆናቸው ብዙም አያጠራጥርም፡፡ በዚህም መሰረት ከሳሹ ተከሳሹን ቢረታ፣ ተከሳሹ ወህኒ  በማስገባት ወይም ደግሞ በገንዘብ አልያም በቁስ በመቅጣት ከሳሹን ለመካስ ይሞከራል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ባህላዊና ግብረገባዊ በሆኑ የግጭት አፈታት ዘዴ ከተመራ የተሻለ ነው፡፡ በዳይም ተበዳይም ጉዳያቸው ታይቶ በስተመጨረሻ ሁለቱም እንዲታረቁና ወደ ቀድሟቸው እንዲመለሱ ይደረጋል እንጂ እንደ ፖለቲካ ህግ፣ አንዱ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማው ተደርጎ ሌላኛው ምንም እንዳላጠፋ ተደርጎ አይሸኙም፡፡
ግፍ የማይፈራና በደል የሚፈጽም ሰው በማህበረሰቡ ዘንድ በርቸ ይሁንብህ/ሽ መባሉ አያጠራጥርም፡፡ ግፍ የሚሰራ ሰው እንደ ውግዘትም አለያም የጥፋቱ ልክ አግባብ አለመሆኑን ለመግለፅ በርቸ ይደረስብህ/ሽ ይባላል፡፡ ለአንድ ሰው በርቸ ይሁንብህ/ሽ ሲባል የሰማ ሰው በአዕምሮው ቀድሞ የሚታወሰው ነገር ቢኖር፣ እንዴት በርቸ ይሁንብህ/ሽ ሊያስብል የሚችል በደል ይፈፀማል የሚል ጥያቄ መጠየቁ የግድ ነው።
ስለዚህ ማህበረሰቡ በየትኛውም አጋጣሚ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ በደልን ላለመፈፀም፣ ሰውን ላለመጉዳት፣ ለመጥፎ ነገር ምክንያት ላለመሆን እንዲሁም በርቸን አጥብቆ ስለሚፈራ የመጥፎ ሥራ ተባባሪ ከመሆን ይጠነቀቃል፡፡
ማህበረሰቡ በርቸ ይሁንብህ/ሽ የሚለው በደልን ለፈፀመ ሰው ብቻ አይደለም፡፡ በተቃራኒ በርቸ ጥሩም ሥራ ለሰራ ሰው፤ በርቸ ይሁንብህ/ሽ ይባላል፡፡ ሥለዚህ ይህ ሀገራዊ የግብረገብ እሴት እዚህ ላይ ከምንቋጨው፣ በቀጣይ ካለንበት ሀገራዊ ሁኔታ ጋር በማቆራኘት በሥፋት ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
ከአዘጋጁ፡ ጸኃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.   ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 10582 times