Print this page
Saturday, 21 November 2020 11:24

የእናት ሆድ ዥንጉርጉር

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  በተለይ ላፕቶፕ ካገኘሁ በኋላ ዓለሙን ሁሉ ረስቼዋለሁ፡፡ አንዳንዴ አሳሪዎቼ ቁርስ አምጥተውልኝ ለምሳ በሩን ሲከፍቱ ምግቡን አስቀምጠው በሄዱበት ቦታ እስከሚያገኙት ድረስ ሁሉን ነገር ረሳሁት፡፡
ዋናዎቹ መርማሪዎች ለወራት ይጠፋሉ። ግንኙነቴ ከጠባቂዎቼ ብቻ ጋር ሆኗል፡፡ እነዚያ ከመጀመሪያ ጀምረው የነበሩ አጭርና ደግ፣ ረጅምና ክፉ ጠባቂዎች አልተቀየሩም። አጭሩ ደግነቱ አልተጓደለም፡፡ ረዥሙ ክፋቱ አልቀነሰም፡፡ አሁንም ሽንት ቤት ስቀመጥ የሽንት ቤት በሩን ይዞ እንደቆመ ነው፡፡ በየወሩና በየሁለት ወሩ የሚቀያየሩ ደግ ከሚባሉ አንስቶ ክፉ የሚባሉ ያሉበት ነው፡፡ አንዳቸውም አማረውኝ አያውቁም። እንዲያውም አንዳንዶቹ ለእኔ ሲሉ አለቆቻቸው ቢያውቁ ሊያስጠይቃቸው የሚችል ስራ ደብቀው ሰርተዋል፡፡
አጭሩና ደጉ፤ መድሃኒት አላድን ያለው እከኬ በጣም ያሳስበው ነበር፡፡ በተለይ አንድ ማለዳ ሲከፍት እጄን በቱታ ገመድ አስሬ አይቶ፤
“ለምን?” ብሎ ጠየቀኝ፤
“ማታ ማታ እግሬን እያከኩ እንዳላደማው እጄን ማሰር መጀመሬን” ነገርኩት፡፡
መድሃኒት እንደ ተሰጠኝና እንደማይሰራ ስላወቀ የራሱን መፍትሄ ለመስጠት ወሰነ። ብቻዬን ስሆን በሬን ይከፍትና ያለ ምንም አይን መጋረጃ እነሱ ወደ ሚታጠቡበት ክፍል ይወስደኛል፡፡ እዛ ክፍል ውስጥ ፀሃይ በመስኮት ትገባለች፡፡ በመስኮቱ በኩል የሚታየው ትልቅ የግንብ አጥር ብቻ ነው፡፡ ሌላ ምንም አይታይም፡፡
“እዚህ ገንዳ ላይ ተቀምጠህ ይህን እግርህን ጸሃይ አስመታው፡፡ ጸሀይ ስለማታገኝ ይሆናል የሚያሳክክህ” ይለኛል፡፡
ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን ሌሎች ጠባቂዎች እስኪመጡ ወይም የሰው ድምፅ እስኪሰማ እዛው አጠገቤ ቆሞ ጸሃይ እንዲመታኝ ያደርጋል፡፡ ትንሽ ኮሽ የሚል ነገር ሲሰማ በጥድፊያ ወደ ክፍሌ መልሶ ይቆልፍብኛል፡፡
ይህ ሰው “አንድ ቀን የሚነበብ አመጣሁልህ”  ብሎ አንድ መጽሐፍ ደብቆ ሰጠኝ፡፡ እስር ቤት ያየሁት የመጀመሪያ መፅሐፍ ነው፡፡
“ሌሎች ጠባቂዎች እንዳያዩህ ደብቀህ አንብብ፡፡ ድንገት እንደው አንድ ነገር ቢመጣም፣ ለሽንት ስወጣ ሽንት ቤት ውስጥ ያለው ኮመዲኖ ላይ አገኘሁት በላቸው” አለኝ የመጽሐፉ ስም “ሮዛ” የሚል ነበር። ሽፋኑ፣ አንዲት ውበት ያላት ሴት፣ ረጅም እግሯንና ጭኗን ጨምሮ የሚያሳይ ክፍት ቀሚስ ለብሳ የተነሳችው ፎቶ ግራፍ ነው። “ሮዛ መሆኗ ነው” መሰለኝ፡፡ ስለ ከተማ የሴትና የወሲብ ንግድ የሚያወራ አስገራሚ መጽሐፍ ነው። የወሲብ ንግዱን ብቻ ሳይሆን ወሲብንም በግልጽ የሚያቀርብ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህንን መጽሐፍ ጠባቂው የሠጠኝ ላፕቶፕ ከመፈቀዱ በፊት ነበር፡፡ ስንት ጊዜ ደጋግሜ እንዳነበብኩት አላውቅም። ደግሞ በመነበብ ሪከርድ የሰበረ መፅሐፍ ይመስለኛል፡፡
በሌላም አጋጣሚ አጭሩ ደግ ሰው ያደረገውን ነገር ሳስታውስ የት አገኘዋለሁ እላለሁ፡፡ ታሪክ እንዲህ ነው፡፡ ለእኔ ምግብ እንድትሰራ የተመደበችው ሰራተኛ ከጠባቂዎቹ ጋር ተጣላች፡፡ ሲጨቃጨቁ ይሰማኛል፡፡ ያው በትግርኛ ነው፡፡ ምን እንዳደረጓት አላውቅም፡፡
“ለእናንተ ምግብ እንድሰራ አልመጣሁም፤ ከአሁን በኋላ እያንዳንድሽ የራስሽን ሰርተሽ ብይ” አለቻቸው፡፡ በዚህ የተነሳ እዛው የታሰርኩበት ቤት ውስጥ ምግብ መስራት ተጀመረ፡፡ ሲያቁላሉ ሲጠብሱ፤ ሽታው ወጥ ቤቱ ከነበረበት እያለፈ በበሩ ስር እኔ የታሰርኩበት ክፍል ይመጣል፡፡ አንድ ለት ታዲያ ደጉ ሰውዬ የእኔን ምሳ ይዞ መጣና፤
“ወንበር ላይ ተቀምጦ ምግብ መብላት አልናፈቀህም? ተነስ ዛሬ ሌላ ጋ ነው የምትበላው” አለኝ፡፡ ተያይዘን በኮሪደሩ አልፈን ሳሎን ቤቱን በቀኝ፤የነሱን ሽንት ቤት በግራ ትተን፤አንድ ትልቅ ወጥ ቤት ውስጥ ገባን፡፡ ወጥ ቤቱ ብዙ መስኮቶች ቢኖሩትም ሁሉም ተዘግተዋል፡፡ መብራት በርቷል፡፡ ቤቱ ማሰሪያ ከመሆኑ በፊት በደጉ ዘመን ዘመናዊ የነበረ ወጥ ቤት እንደነበረው የሚያሳዩ የተሰባበሩና ያረጁ ብዙ ነገሮች አሉት፡፡ አንድ ጥቂት ወንበሮች ያሉት ትንሽ ጠረጴዛም አለው፡፡
“እዚህ ተቀመጥና ብላ፡፡ እኔ ምሳዬን እሰራለሁ” ብሎ እዛው አጠገቤ ሽንኩርት መላጡን ተያያዘው፡፡ በአንድ ትንሽ መሬት ላይ በምትቀመጥ የኤሌክትሪክ ምድጃ ላይ ብረት ድስቱን  ጥዶ ሽንኩርቱን ማቁላላት ጀመረ፡፡ የሚሰራው ለራሱ ብቻ ነው፡፡ እኔ እየበላሁ እሱ ወጥ እየሰራ  ሞባይሉን አውጥቶ እንደ ቴሌቪዥን ግድግዳ አስደግፎ የቪድዮ ሙዚቃ ከፈተ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ  ስለ ራሱ ጥቂት ነገር ነገረኝ፡፡ የእናቱ ቤተሰቦች በሴት አያቱ በኩል ከጎንደር ወደ ትግራይ በትዳር የሄዱ ጎንደሬዎች እንደነበሩ አጫወተኝ።  እኔም “የዚህ ሰው የተለየ ደግነት በዚህ በቀጭን ክር ከአማራ ጋር በተሳሰረ ደሙ ይሆን?”  እያልኩ አዳመጥኩት፡፡
ይህንን እንዳልልም ደግሞ ሌላው ጠባቂ ምንም አይነት የጎንደር ደም የሌለው፣ በበአል ቀን ስለኔ የሚሰማው ጭንቀት የሚያስገርመኝ ሆኗል፡፡ በበአል ቀን ጠባቂዎቹ ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ስለ ሚፈቀድ ሁሌም ቤቱ ውስጥ አንድ ሰው ብቻ ነው የሚቀረው፡፡ አንዱ ደርሶ ሲመለስ አንዱ ይሄዳል፡፡
ይህ ከሁሉም ጠባቂዎች ጠቆር ያለ መልክና በጣም ስል አፍንጫ ያለው ወጣት፣ የበአል ቀን ተረኛ ከሆነ፣ ለኔ ብሎ ከቤቱ ይዞ የማያመጣው ምግብ አልነበረም፡፡ የተመደበችልኝ መጋቢ ከምትሰራው ውጪ ለኔ ምግብ መስጠት የተከለከለ መሆኑን እያወቀ፤ #ሚስቴ የሰራችው ነው፤ እባክህ ትንሽ ቅመስ” እያለ በተለያየ ጊዜዎች ጋብዞኛል፡፡ እኔም ደረቅ ከሆኑ ነገሮች ውጪ ሌላውን ለምን እንደማልበላ በመግለጽ በዳቦና በደረቅ ቂጣው ተወስኜ ግብዣውን ተቀብያለሁ፡፡ ጠባቂዬ ይህን እንዲያደርግ የሚያደርገው የራሱ ምክንያት አለው፡፡
ወጣቱ በጣም ኳስ ይወዳል፡፡ አንድ ቀን ምግብ ሲያመጣልኝ ጆሮው ላይ ማድመጫ ተክሎ ሬዲዮ  እያዳመጠ ነበር፡፡
“ምን እየሠማህ ነው?” አልኩት፡፡
“ኳስ ጨዋታ---የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ”አለኝ፡፡
“አ የዛሬን አያርገውና እኔም የአርሰናል ደጋፊ ነበርኩ” አልኩት፡፡
ለካ እሱም አርሰናልን ልቡ እስከሚጠፋ የሚደግፍ ሰው ነው፡፡ ከዛ ቀን በኋላ ሁሉም ነገር ቀርቶ ወዳጅ ሆንን፡፡ ብቻውን የሆነ እለትና አርሰናል የሚጫወት ከሆነ በሬን ይከፍታል፡፡ በር ላይ ይቆምና አንዱን የጆሮ ማዳመጫ አውጥቶ እኔ እንዳዳምጥ ይሰጠኛል፡፡
 ሁለታችንም ብስራት የሚባል የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ በአማርኛ የሚያስተላልፈውን ግጥሚያ እናዳምጣለን፡፡ የጋዜጠኞቹ አቀራረብ በጣም የሚያስደንቅ ነው። የሁለታችንንም ልብ ጉሮሯችን ስር ገብቶ እንዲቀራረብ የሚያደርግ ዘገባ ነው የሚያስተላልፉት፡፡ እኔና ጠባቂዬ አርሰናል ሲያሸንፍ ተደስተን፣ ሲሸነፍ ተኳርፈን እንለያያለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ካልተመቸው ሌሊትም ቢሆን በር ከፍቶ “አርሰናል በዚህ ውጤት አሸንፏል”  ይለኛል፡፡ ይህን ሲያደርግ አለቃው እንዳይጠራጠረው ድምጹን ከፍ አድርጎ “አንኳኳህ መሰለኝ” ይለኛል፡፡ እኔም አንዳንድ ቀን ለመተባበር “አዎ ሆዴን ጎርብጦኛል፤ ሽንት ቤት መሄድ እፈልጋለሁ” እላለሁ። ለማስመሰልም ሽንት ቤት እሄዳለሁ፡፡ አንዳንድ ቀን “ውጤት እነግርሃለሁ” ብሎ ቃል ገብቶ ይጠፋል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለምን እንደሚጠፋ ገባኝ። የሚጠፋው አርሰናል ሲሸነፍ ብቻ ነው፡፡
የዚህ ጠባቂ ድርጊት የሚያሳየው የሰው ልጅ የማንነቱ መገለጫ ብዙ መሆናቸውን ነው፡፡ ይህ ጠባቂ በሌሎች ጉዳዮች ከትግራዋይ ዝርያዎች ጋር በአንድ ላይ ሊቆም ይችላል፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ደግሞ ላይቆም ይችላል፡፡ በአርሰናል ጉዳይ ከመጡበት ከእኔ ጋር አንድ ሆኖ ትግራዮችን ግብ ግብ ሊገጥም እንደሚችል ነው፡፡ የዘር ፖለቲካ አራማጆች፣ ሰውን በዘሩ ብቻ ለመግለጽ የሚያደርጉትን የተሳሳተ ድርጊት ኪሳራ የሚያሳይ መረጃ ነው፡፡ ለኔ በሰዎች መካከል ዘርን አቋርጠው የሚሄዱ ተመሳሳይነቶች በዘር ላይ ከተመሰረቱ ተመሳሳይነቶች የሚበዙ መሆናቸውን ስለማውቅ በጠባቂዬ ድርጊት አልተገረምኩም፡፡
#አጭሩ ደጉና ይህ አርሰናልን ከልቡ የሚደግፈው ጠባቂ የት ደርሰው ይሆን?;
(ከአንዳርጋቸው ጽጌ "የታፋኙ ማስታወሻ" አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)


Read 1808 times
Administrator

Latest from Administrator